ቅድመ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ድሬዳዋ ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ለዋንጫ እና ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ውስጥ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ድሬዳዋ ከተማ የሚያደርጉትን የነገ አመሻሽ ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰናል።

እስካሁን አንድም ሽንፈት ያላስተናገደው የወቅቱ የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ አሁንም በአሸናፊነት ጎዳና በመዝለቅ እና ከበታቾቹ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት እያሳደገ ለመምጣት በሸገር ደርቢ ያሳየውን ጠንካራ ብቃት ነገም ይደግማል ተብሎ ይታሰባል። በተቃራኒው በወራጅ ቀጠናው አፋፍ ላይ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች በበኩላቸው ለሰባት ተከታታይ ጨዋታዎች ያላገኙትን ድል በማሳካት ከአስጊው ቀጠና ለመሸሽ የሚያደርጉትን ሩጫ አጠናክረው ለመቀጠል ሦስት ነጥብን አልመው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይታመናል።

በአሁኑ ሰዓት በብዙ መስፈርቶች የሊጉ ምርጥ ቡድን የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኳስ ጋርም ሆነ ከኳስ ውጪ ያለው መታተር ዋጋ እያስገኘው ነው። ባሳለፍነው ሳምንት በተደረገው የሸገር ደርቢም የተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡናን ስልት ለማምከን እና የራሱን ጠንካራ ጎን ለማጉላት የጣረበት መንገድ በብዙዎች አድናቆት አስችሮታል። በዋናነትም የቡና ተጫዋቾች ኳስ በምቾት እንዳይመሰርቱ በማድረግ በላይኛው ሜዳ ለተጋጣሚ ግብ ብዙም ሳይርቁ የሚረከቡትን ኳሶች በቶሎ ወደ አደጋነት ሲቀይሩ ታይቷል። በቡድናዊም ሆነ በግል አጨዋወት የተዋጣለት ቡድኑ በነገው ጨዋታ ግን እንደ ኢትዮጵያ ቡና ኳስ ለመያዝ እምብዛም ፍላጎት የሌለውን ድሬዳዋን ስለሚገጥም የስልት ለውጥ ማድረግ የግድ ይለዋል። ይህንን ተከትሎም ዘለግ ያለውን ጊዜ ወደ ራሳቸው ሜዳ ወረድ ብለው እንደሚከላከሉ የሚታሰበውን የድሬ ተጫዋቾች ለማስከፈት የኳስ ቅብብሎቹ ፈጣን እንዲሁም የሜዳ አጠቃቀሙ ስፋት እና ጥልቀት ሊኖረው የግድ ይላል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ የቡድኑ የፊት የሦስትዮሽ ጥምረት (ቸርነት፣ አማኑኤል እና አቤል) ቅልጥፍና፣ ፍጥነት እና ሥልነት ለድሬ የኋላ መስመር ፈተናን እንደሚሰጥ ይጠበቃል። ከሦስቱ አጥቂዎች በተጨማሪ ደግሞ ከአማካይ መስመር እየተነሳ ዘግየት ያሉ ሩጫዎችን በማድረግ ለቡድኑ አማራጭ የሚሰጠው የአብስራን ጨምሮ ረጃጅም እና ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶቻቸው ድንቅ የሆነው ሀይደር እና ጋቶችም ብቃትም ጨዋታውን በጊዮርጊስ በኩል የሚወስኑ ይሆናል።

ሜዳ ላይ እጅግ የታመመ የሚመስለው ድሬዳዋ ከተማ በውድድር ዓመቱ ሦስት አሠልጣኞችን እና 25 ተጫዋቾችን አፈራርቆ ቢጠቀምም ጠንካራ እና የተዋሀደውን ምርጥ ስብስብ እስካሁን ማግኘት አልቻለም። ከምንም በላይ ቡድኑ በሁለቱ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች ኮስታራ አይመስልም። ለማሳያም ቡድኑ በሊጉ ሦስተኛው ብዙ ግቦችን ያስተናገደ (22) እንዲሁም ሦስተኛው ጥቂት ግቦችን ያገባ (12) ነው። በዋናነት ደግሞ ቡድኑ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር መሀን የመሆኑ ነገር እስካሁን መፍትሔ ያላገኘ ጉዳይ ነው። በሲዳማው ጨዋታ ቡድኑ ከወገብ በላይ ተጫዋቾችን ለመቀያየር ጥረት ቢያደርግም ሁነኛ ሰው አጥቶ ከሜዳው ወጥቷል። እርግጥ በሲዳማው ጨዋታ አሠልጣኙ እንዳመኑት ጥንቃቄ ተኮር አጨዋወት በመከተል የተጋጣሚን ጥቃት መመከት ላይ ተቀዳሚ እቅድ አውጥተው ወደ ሜዳ መግባታቸው በላይኛው ሜዳ የቁጥር መሳሳት ቢያስከትልባቸውም በአንዳንድ አጋጣሚዎች በሚገኙ የሽግግር ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር እጅግ ሲቸገሩ አይተናል። በነገው ጨዋታ ደግሞ የሊጉን ምርጥ የተከላካይ መስመር መግጠማቸው በእንቅርት ላይ አይነት ነገር እንዳይሆንባቸው ያሰጋል። ምናልባት ግን ፈጣኖቹን የመስመር አጥቂዎቻቸውን መሐከል ያደረገ አጨዋወት በመከተል ሽግግሮችን በትኩረት ለመጠቀም ሊያስቡ እንደሚችሉ ይገመታል። በመከላከል ላይ ግን በሲዳማው ጨዋታም ቡድኑ ግብ ላለማስተናገድ ከኳስ ኋላ በመሆን ቢንቀሳቀስም በግብ ጠባቂው ድንቅ ብቃት ከጨዋታው አንድ ነጥብ ማግኘቱ የማይዘነጋ ስለሆነ በመከላከሉም ረገድ አደረጃጀቱን አሻሽሎ መቅረብ ይጠበቅበታል።

ሁለቱም ቡድኖች እየተጓዙበት ካለው መንገድ መነሻነት ሦስት ነጥቡ ለሁለቱም እጅግ አስፈላጊ ነው። በተለይ ድሬዳዋ ካለበት አስጊ ደረጃ በትንሹም ቢሆን ፈቅ ለማለት ድል ማግኘት የግድ ይለዋል። ምናልባት ይህ ሀሳብ በመዋለል እንዲጫወት አድርጎት ዋጋ ካላስከፈለው ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚደረጉ ሽግግሮች፣ የቆሙ እና ቀጥተኛ ኳሶችን በአንኩሮ ትኩረት ሰጥቶ መጠቀም ያስፈልገዋል። እንስካሁን በ10 ጨዋታዎች ግቡን ያላስደፈረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ ጨዋታዎችን የሚጀምርበት ከፍተኛ ፍጥነት እና ፍላጎት ለቡድኖች አደጋን ይዞ እየመጣ ስለሆነ ነገም በተመሳሳይ ሰዓት በሁለቱ አጋማሾች ጅማሮ ጨዋታውን ለመወሰን እንደሚጥር ይጠበቃል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋቹ እስማኤል ኦሮ-አጎሮ አሁንም ከጉዳቱ ባለማገገሙ ነገ አይጠቀምበትም። ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ በርካታ ደቂቃዎችን (1518) ያገለገለውን የመሐል ተከላካይ መሳይ ጻውሎስን በአምስት ቢጫ ምክንያት አያገኝም። ምናልባት ባለፉት ጨዋታዎች ጉዳት ላይ የነበረው ሌላኛው ተከላካይ ሚኪያስ ካሣሁን ከጉዳቱ ማገገሙ ደግሞ በቦታው አማራጭ የሚሰጥ ይመስላል። የቡድኑ አምበል ዳንኤል ደምሱ እና ጋዲሳ መብራቴ በበኩላቸው ቀለል ያለ ጉዳት ላይ በመሆናቸው በጨዋታው ያላቸው ተሳትፎ እርግጥ አልሆነም።

ይህንን ጨዋታ ሚካኤል ጣዕመ ከረዳታቸው ትግል ግዛው እና ሲራጅ ኑርበገን እንዲሁም ከአራተኛ ዳኛው ተከተል ተሾመ ጋር በመሆን እንደሚመሩት አውቀናል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ19 ጊዜያት ተገናኝተዋል። በእነዚህ ግንኙነቶች ቅዱስ ጊዮርጊስ 12ቱን በመርታት ቀዳሚ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 3ቱን አሸንፏል። ቀሪዎቹ አራት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ፍፃሜያቸውን አግኝተዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ


ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ቻርለስ ሉክዋጎ

ሱሌይማን ሀሚድ – ምኞት ደበበ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ሔኖክ አዱኛ

የአብስራ ተስፋዬ – ጋቶች ፓኖም – ሀይደር ሸረፋ

አቤል ያለው – አማኑኤል ገብረሚካኤል – ቸርነት ጉግሳ

ድሬዳዋ ከተማ (4-3-3)

ፍሬው ጌታሁን

እንየው ካሣሁን – ሚኪያስ ካሣሁን – አውዱ ናፊዩ – አማረ በቀለ

አቤል ከበደ – ብሩክ ቃልቦሬ – ዳንኤል ኃይሉ

አብዱረህማን ሙባረክ – ማማዱ ሲዲቤ – አብዱለጢፍ መሐመድ