እጅግ አዝናኝ በነበረው የ18ኛው ሳምንት ቀዳሚ ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና በመጨረሻ አስር ደቂቃዎች ሦስት ግቦችን በማስቆጠር ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ነጥብ መጋራት ችሏል።
ሀዲያ ሆሳዕና ከባህር ዳሩ ድል አጥቂ ክፍል ላይ ዑመድ ዑኩሪን በሀብታሙ ታደሰ በመተካት በ3-6-1 ሲጀምር አርባምንጮች አዲስ አበባን በረቱበት ስብስብ ላይ ለውጥ ሳያደረጉ 3-4-3 አሰላለፍን ጥቅም ላይ አውለዋል።
ሦስት ግቦችን ያስመለከተን ቀዳሚው አጋማሽ ጥሩ ፉክክር የታየበት ነበር። የሀዲያ ሆሳዕናን የኳስ ምስረታ ሦስቱን ተከላካዮች በሦስት አጥቂዎች ጫና ውስጥ በመክተት ከጅምሩ ለማፈን የተንቀሳቀሱት አርባምንጮች አደጋን ከግብ ክልላቸው ማራቅ ችለዋል። ወደ ቀኝ ያመዘነው የሆሳዕና ጥቃት 4ኛው ደቂቃ ላይ ብርሀኑ በቀለ ወደ ውስጥ አሻግሮት ሳምሶን አሰፋ ከዑመድ ዑኩሪ እርምጃ በፊት ካወጣው ኳስ ውጪ ንፁህ የግብ ዕድል ሳይፈጥር ቆይቷል።
13ኛው ደቂቃ ላይ እንደተለመደው ከሙና በቀለ የቅጣት ምት ኳስ አደጋ መፍጠር የጀመሩት አርባምንጮች ከአራት ደቂቃ በኋላ ከዚሁ የሙከራ ምንጭ ግብ አግኝተዋል። የሙና የርቀት ቅጣት ምት ሲሻማ ፀጋዬ አበራ በግንባር ገጭቶት ያሬድ በቀለ እንደምንም ቢያድነውም ኦቼና ማርቲን እና አሸናፊ ፊዳ የነካኩትን አህመድ ሁሴን 17ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አድርጎታል።
ሀዲያ ሆሳዕናዎች አቻ ለመሆን ከቀኝ ወደ መሀል ለመሀል ጥቃት ፊታቸውን ሲያዞሩ 21ኛው ደቂቃ ላይ ግርማ በቀለ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታውን ሳምሶን አሰፋ አድኖታል። ሆኖም 23ኛው ደቂቃ ላይ ከኋላ የተላከውን ረጅም ኳስ ሳጥን ውስጥ የተቆጣጠረው አህመድ ፍሬዘር ካሳን አታሎ ያመቻቸውን ፀጋዬ አበራ ደርሶ በሆሳዕና መረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል።
2-0 የተመሩት ነብሮቹ ዑመድን ትኩረት ባደረጉ ኳሶች ለማጥቃት ባደረጉት ጥረት ልዩነቱን በቶሎ ያጠበበበት አጋጣሚ ተፈጥሯል። ዑመድ በረጅሙ በደረሰው ኳስ ማርቲን ኦኮሮን ለማለፍ ባደረገው ጥረት ኬኒያዊው ተከላካይ በእጅ በመንካቱ በተሰጠው ፍፁም ቅጣት ምት ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን 30ኛው ደቂቃ ላይ ውጤቱን 2-1 አድርጎታል።
በቀሪው የአጋማሹ ደቂቃዎች አዞዎቹ ከኳስ ውጪ የሆሳዕናን የኳስ ቁጥጥር በመቆጣጠር በቀጥተኛ ፈጣን ሽግግሮች ወደ ግብ ለመሄድ ጥረዋል። በዚህ ረገድ 39ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ሻሚል እና አህመድ ሁሴን ከሳጥን ውጪ አከታትለው ያደረጓቸው ሙከራዎች ይጠቀሳሉ። የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን የያዙት ነብሮቹ 33ኛው ደቂቃ ላይ ፍቅረየሱስ ከዑመድ ጋር አንድ ሁለት በመቀባበል ከሳጥን ውስጥ ያደረገው ሙከራ ወደ ውጪ የወጣበትን የግብ ዕድል ፈጥረዋል። በተመሳሳይ አካኋን መሀል ለመሀል ሰብረው መግባት ቀላል ባሆንላቸውም ለዑመድ ቀጥተኛ ካሶችን ለማድረስ ጥረት እያደረጉ አጋማሹ ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ በተመሳሳይ የሀዲያ ሆሳዕና የኳስ ምስረታ ሂደት ለአርባምንጭ ከተማ መልሶ ማጥቃት በር ሲከፍት የታየበት ነበር። ሆሳዕናዎች ለማጥቃት ኃይል ጨምረው ቢንቀሳቀሱም ሙሉ ለሙሉ ወደ መከላከል ያላመዘኑት አርባምጮች ምላሽ ተከታታይ ግቦችን አስገኝቷል። 54ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋዬ አበራ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የሞከረውን ኳስ ያሬድ ሲያድንበት በቅርብ ርቀት የነበረው አህመድ ሦስተኛ ግብ አድርጎታል። በተመሳሳይ 62ኛው ደቂቃ ላይ ከረጅም ርቀት ቅጣት ምት ፍሬዘር በግንባር በሚገባ ያላራቀውን በላይ ገዛኸኝ ከቅርብ ርቀት ሞክሮ ያሬድ ሲያድነው በድጋሚ አህመድ ደርሶ ሀት-ትሪኩን ያጠናቀቀበትን ግብ አስቆጥሯል። ሆኖም አጥቂው 72ኛው ደቂቃ ላይ ጉዳት አስተናግዶ በፍቃዱ መኮንን ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል።
ቀጣዮቹ ደቂቃዎች ድራማዊ ሆነዋል። አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ቅያሪዎችን በማድረግ ባዬ ገዛኸኝ እና ሀብታሙ ታደሰን ከፊት ከዑመድ ጋር ያጣመሩበት ሂደት 80ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስገኝቶላቸዋል። ተቀያሪው ሀብታሙ ከቀኝ ከብርሀኑ የደረሰውን ኳስ ከጠባብ አንግል ከመረብ ማገናኘት ሲችል ግቡን በረዳት ዳኛው ለዓለም ዋሲሁን ቢሽሩትም ዋና ዳኛው ኤፍሬም ደበሌ አፅድቀውታል።
በዚህ የተነሳሱት ነብሮቹ ባላቸው ኃይል ሁሉ በማጥቃት ያሳለፉባቸው የመጨረሻ ደቂቃዎች ከፍለዋቸው ሁለት ግቦችን አክለዋል። ቡድኑ በግራ መስመር ከፈጠረው ጫና በተደረጉ ንክኪዎች ሄኖክ አርፌጮ ሳጥን ውስጥ ተገኝቶ 88ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥሯል። ቡድኑ በዚሁ አቅጣጫ በጭማሪ ደቂቃዎች ጫናውን አጠናክሮ ሲቀጥል ወደ ቀኝ የሳጥኑ ክፍል ያሻገረውን ኳስ ብርሀኑ በቀለ ሮጦ እንደደረሰ በቀጥታ በመምታት በአስገራሚ ሁኔታ ነብሮቹን አቻ አድርጓል። አርባምንጭ ከተማ በመጨረሻ ደቂቃ በሀቢብ ከማል የቅጣት ምት ሌላ ግብ ለማከል ያደረገው ጥረት በያሬድ በቀለ ድኖ ጨዋታው 4-4 ተጠናቋል።