የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዲያ ሆሳዕና 4-4 አርባምንጭ ከተማ

ድራማዊ ከነበረው ጨዋታ በኋላ ተጋጣሚ አሰልጣኞች ይህንን ብለዋል።

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ሀዲያ ሆሳዕና

ስለጨዋታው

“እንደ አጀማመራችን ወይንም እንደ አርባምንጭ ሳይሆን በራሳችን ስህተት ግቦች ተቆጥረውብናል ፤ እንደምንፈልገው መሄድ አልቻልንም። አርባምንጭ ጠንካራ እና አስቸጋሪ ከሚባሉ ቡድኖች ውስጥ ነው። ይህ እንደሚገጥመን እናውቅ ነበር። በዛ ላይ ደግሞ የእኛ ስህተት ታክሎበት ጎሎች ተቆጥረውብናል። ግን ደግሞ ራሳችን አርመነው አቻ ለማውጣት ተገደናል።

በቶሎ ስለመመራታቸው

“በእርግጥ ጎሎች ሲገቡ የሚከሰቱ ነገሮች አሉ። ራስህን ከመመራት ወደ ማሸነፍ ለመምጣት የሚያወርዱ ነገሮች አሉ። ቢያንስ የእኔ ልጆች በዛ መንፈስ ውስጥ አልነበሩም። ቢመሩም አጥቅተው ለመሄድ የሚያደርጉት ጥረት የሚያስደስት ነበር ፤ ተሳክቶላቸውም አይተናን። በዛሬው ጨዋታ ከሚባለው በላይ ብዙ ዋጋ ከፍለውበታል። እያንዳንዱ ተጫዋች ጥረቱ የሚደነቅ ነበር። በመጨረሻም ተሳክቶልናል።

ስለተቀያሪዎች ጨዋታ ቀያሪነት

“ባለፈው ሀብታሙ ነበር የመጀመሪያ አጥቂያችን ግን ዑመድም ባዬም መጀመር ይችላሉ ፤ አቅሙ አላቸው። ግን እኛ ባሰብነው መንገድ አልሄድንም። ጎሎች ቀድመው ስለገቡብን ያሉንን አጥቂዎች ጨምረን አስገብተን በምንፈልገው መንገድ ተቀይረው የገቡ ልጆች ቡድኑን ታድገውታል።”

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ – አርባምንጭ ከተማ

ስለጨዋታ ቁጥጥራቸው

“ተጨማሪ ጎሎች ለማግባት የሄድንበት ጠንካራ ነገር አለ ፤ ለተመልካች አዝናኝ ነው። 4-1 መርተን በዚህ ደረጃ ውጤት ማጣት አልነበረብንም። መሳይ መከላከል ላይ ደህና ነው ይባላል ዛሬ ግን በምንፈልገው ደረጃ በጥንቃቄ አስጠብቀን መውጣት ነበረብን። ትኩረት አጥተናል ፤ ምንአልባት ለምን ጎሎች እንደተቆጠሩ ቪዲዮውን አያለሁ። እንደፈለግነው ጨዋታውን ተቆጣጥረናል ማለት አልችልም ፤ የሦስት ልዩነቱን ማስጠበቅ ነበረብን።

ስለማጥቃት እና መከላከል አፈፃፀማቸው

“ወደ 3-4-3 የተጠጋ የአጥቂ ዞናችንን ከፍ አድርገን ነው የገባነው ፤ በተደጋጋሚ የግብ አጋጣሚዎችን ስንፈጥር ነበር። ጎሎች ሲገቡብን ተደራጅቶ መከላከሉን ማሳደግ አለብን። አንዱ ሲወጣ ሌላው ክፍተቱን እየሸፈነ በቀላሉ መከላከል መቻል ነበረብን። በተወሰነ መልኩ የዞን መከላከላችንን ማሳደግ አለብን።

ጎሎች ስላገኙበት መንገድ

“ጎሎችን ስናስቆጥር የባላጋራም ነገር የእኛም ጥንካሬዎች አሉ። ቶሎ ቶሎ ወደ ሦስተኛው ሜዳ ክፍል እየገባን ስናጠቃ ነበር። የእኛ ድክመት እንዳለ ሆኖ የባላጋራንም ድክመት የእኛንም ጥንካሬ ተጠቅመን ነው አራት ጎሎች ያስቆጠርነው።

ስለአህመድ ሁሴን ዝውውር

“አጠቃላይ የውድድሩ ጥሩ ዝውውር ነው ብዬ አስባለሁ። ብዙ አቅም ያለው ልጅ ነው።

ስለውጤቱ ተገቢነት

“እግዚአብሔር ይመስገን። አንዳንዴ እኛም እንደዚህ ባለቀ ሰዓት ድሎችን እናገኛለን ፤ ይሳካል። ስለዚህ ውጤቱን ተቀብለን ለሌላ ጊዜ ማረም የሚገባንን በሰከነ መንገድ አይተን ነው መሄድ ያለብን።”