ሪፖርት| የቅዱስ ጊዮርጊስ ሩጫ እንደቀጠለ ነው

ምሽቱ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማን የገጠሙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 3-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በሊጉ አናት ማስደመማቸውን ቀጥለዋል። 

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″] ቅዱስ ጊዮርጊስ በደርቢው ኢትዮጵያ ቡናን የረታውን ስብስብ ሳይለውጥ ለዛሬው ጨዋታ ሲቀርብ በድሬዳዋ ከተማ በኩል ደግሞ ከሲዳማ ቡና ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ሥስት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም አቤል አሰበ ፣ መሳይ ጳውሎስ እና አቤል ከበደን አስወጥተው በምትካቸው ከድር ኸይረዲን ፣ ዳንኤል ኃይሉ እና አብዱረህማን ሙባረክን በመጀመሪያ ተሰላፊነት አስጀምረዋል።

ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ በረጃጅም ኳሶች የማጥቃት ፍላጎት የነበራቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተለይ አቤል ያለው በተሰለፈበት የቀኝ መስመር ተደጋጋሚ ኳሶችን በመጣል በጨዋታው በድሬዳዋ ከተማ በኩል የግራ መስመር ተከላካይነት የጀመረውን አብዱለጢፍ መሀመድ እንዲነጠል በማድረግ በቁጥር ብልጫ እየወሰዱ ሲፈትኑት አስተውለናል። በዚህም በ10ኛው ደቂቃ ሄኖክ አዱኛ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ አማኑኤል ገ/ሚካኤል የገጨበት እና ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣችበት ሙከራ አደገኛ አጋጣሚ ነበረች።

ጨዋታውን በተሻለ ተነሳሽነት የጀመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ17ኛው ደቂቃ ቀዳሚ መሆን ችለዋል ፤ ሄኖክ አዱኛ ወደ ግራ ካደላ አቋቋም በቀጥታ ያሻማውን የቅጣት ምት ኳስ ምኞት ደበበ እንዳይጠቀም ለማድረግ ጥረት ያደረገው አብዱልጢፍ መሀመድ የሸረፋት ኳስ ፍሪምፖንግ ሜንሱ በግንባሩ በመግጨት ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።

በአንፃሩ በመካከለኛ የመከላከል መስመር ሲጫወቱ የተመለከትናቸው ድሬዳዋ ከተማዎች መከላከሉን ሆነ ማጥቃቱን በሚገባው ልክ መከወን ያልቻሉበት አጋማሽ ነበር። በአጋማሹ በመከላከሉ ረገድ ስስ የነበረው ቡድኑ በማጥቃቱ ደግሞ እንየው ካሳሁን በተሰለፈበት የቀኝ መስመር በንፅፅር ተስፋ ሰጪን እንቅስቃሴ ማድረግ ችሏል። ከ30ኛው ደቂቃ አንስቶ ግን በተሻለ ኳሶችን በመቆጣጠር ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ አጋማሽ ለመድረስ ጥረት ማድረግ የጀመሩት ድሬዎች የጠሩ የግብ ዕድሎችን ባይፈጥሩም በሚታይ መልኩ በጨዋታው አድገው አስተውለናል።

ሁለተኛውን አጋማሽ በግራ መስመር በኩል የነበረባቸውን ተጋላጭነት ለመቀነስ አማረ በቀለን በጋዲሳ መብራቴ ምትክ ያስገቡት አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ ፤ አብዱለጢፍ መሀመድን ወደ ፊት በመግፋት አማራ በቀለን በግራ መስመር ተከላይነት ተጠቅመዋል። ታድያ በአጋማሹ ድሬዳዋ ከተማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች የነበራቸውን መነቃቃት ማስቀጠል ሳይችሉ የቀሩ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽም ቅዱስ ጊዮርጊሶች አንፃራዊ የበላይነት ነበራቸው።
በ55ኛው ደቂቃ ላይ ግን ዳንኤል ደምሴ በድሬዳዋ ሳጥን አቅራቢያ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተነሳ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ያገኙትን የቅጣት ምት ፍሪምፖንግ ሜንሱ በግሩም ሁኔታ በማስቆጠር የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት አሳድጓል።

ከግቧ መቆጠር ጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሦስተኛ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። በፈጣን መልሶ ማጥቃት የፈጠሩትን ዕድል አማኑኤል ገ/ሚካኤል በግሩም ሁኔታ ቢሞክርም ፍሬው ጌታነህ በተመሳሳይ በአስደናቂ ሁኔታ በማዳን ልዮነቱ እንዳይሰፋ ማድረግ ችሏል።
በ66ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ጥሩ ቀን ለማሳለፍ የተቸገረው የድሬዳዋ ከተማው አብዱለጢፍ መሀመድ ሀይደር ሸረፋ ላይ በሰራው ጥፋት መነሻነት በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል።

ይህም ድሬዳዋ ከተማዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ የነበራቸው ተስፋ ላይ ውሃን የቸለሰ አጋጣሚ ነበር። በ75ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ያለው በሳጥኑ ጠርዝ ከነአን ማርክነህ እና የዓብስራ ተስፋዬ በግሩም ቅብብል ያደረሱትን ኳስ ተጠቅሞ በድንቅ አጨራረስ የቡድኑን ሦስተኛ ግብ በማስቆጠር የጊዮርጊስን አሸናፊነት ማረጋገጥ ችሏል።

በቀሪው ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊሶች ይበል አጥቅተው ለመጫወት በማሰብ በቁጥር በዝተው በማጥቃት የድሬዳዋን የመከላከል አወቃቀር መፈተን የቻሉ ሲሆን በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ አሳፋሪ ሽንፈትን ላለማስተናገድ ጥረት ሲያደርጉ አስተውለናል።

በሁለተኛው ዙር ሦስተኛ ተከታታይ ድል ማስመዝገብ የቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ40 ነጥብ ሊጉን መምራታቸውን ሲቀጥሉ ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ በ17 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ያጋሩ