[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ምቾት ላይ የማይገኙት የዘንድሮው አዳጊዎች በሚያደርጉት ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።
እስካሁን ያለው የሊጉ ጉዞ ከከፍተኛ ሊግ ማደግ ለቻሉት አዲስ አበባ እና መከላከያ ከወራጅ ቀጠና የተላቀቀ ቦታ ሊሰጣቸው አልቻለም። ካለፉት አራት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያሳኩት ቡድኖቹ ከሽንፈት መልስ ነገ የሚያደርጉት ጨዋታ በሰንጠረዡ የመጨረሻ ክፍል ላይ ለውጦችን ሊያሳይ ይችላል። አዲስ አበባዎች የዓመቱን የመጀመሪያ ድል ባስመዘገቡበት መከላከያ ላይ ዳግም ሙሉ ውጤት ይዘው መውጣት ከቻሉ ቢያንስ ከበላያቸው ያለው ድሬዳዋ ከተማን ደረጃ መቀየር ይችላሉ። ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ስያሜውን ወደ ‘መቻል’ ለመቀየር የወሰነው መከላከያ ደግሞ ከወራጅ ቀጠናው ያላውን ርቀት ሰባት የማድረስ ዕድልን ይዞ ይገባል።
ከ17ኛው ሳምንት ሽንፈታቸው በኋላ አሰልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ እና አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በተከላካይ መስመር ላይ ስላለባቸው ችግር አፅዕኖት ሰጥተው ሀሳብ ሲሰነዝሩ ተስምቷል። በእርግጥ አዲስ አበባዎች በአርባምንጭ በቆሙ ኳሶች ግብ ማስተናገዳቸው እንዲሁም ያለአሌክስ ተስማ ጨዋታውን ያደረገው መከላከያ በሰበታ ያስተናገደው ግብ ለአሰልጣኞቹ ሀሳብ መነሻ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ይህ ነጥብ የቡድኖቻቸው የማጥቃት ወረዳ ላይ ነገ ማስተካከል የሚገባቸውን ጉዳዮች የሚሸፍን መሆን የለበትም። ቡድኖቹ ካሉበት ደረጃ እና ማሸነፍ ከሚያመጣው ፀጋ አንፃር አጥቅተው ሊጫወቱ ይችላሉ የሚለው ግምትም ይሄንን ያጠናክራል።
ቡድኖቹ ከግብ ፊት ያለባቸው ችግር መልክ የተለያየ ነው። አዲስ አበባ ከተማ የፊት መስመር ተሰላፊዎቹ የመጨረሻ ውሳኔ አሁንም በድክመት የሚነሳ ነው። በጨዋታ ሂደት ውስጥ በተለይም መካከለኛ ርቀት ባላቸው ቅብብሎች ቡድኑ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን የሚደርስባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች 28 ሙከራዎቹን ማድረጉ ለዚህ ማሳያ ሲሆን አጥቂዎቹ ኢላማቸውን የጠበቁት ግን 1/3ኛ በሆኑ አጋጣሚዎች ብቻ ነበር። ከዚህ አንፃር በመጨረሻው ጨዋታ ተቀይረው በመግባት የተሻለ ጫና ፈጥረው የታዩት መሀመድ አበራ እና ቢኒያም ጌታቸው ከቡድኑ የእንዳለ ፣ ፍፁም እና ኦዶንጎ ጥምረት ውስጥ ዕድል ሊሰጣቸው እንደሚችል ይገመታል።
ወደ መከላከያ ስንመጣ ግን ዕድል የመፍጠር ችግሩ ይበልጥ የጎላ ሆኖ እናገኘዋለን። በሁለት የመጨረሻ ጨዋታዎች ሁለት ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ብቻ ያደረጉት መከላከያዎች ዝርግ 4-4-2ን ቢጠቀሙም የማጥቃት መነሻቸው ቀጥተኛነትን ከኮሪደሮች ተሻጋሪ ኳሶች ጋር ቀላቅሎ ከማድረግ ይልቅ ወደ ግራ ካደላ የኳስ ቁጥጥር ለማግኘት ሲጥሩ ይታያል። ይህም ቡድኑን ያለቅጥ በቦታው ተሰላፊ ቢኒያም በላይ ላይ እንዲመረኮዝ እና ለተጋጣሚዎች ግምት ቀላል እንዲሆን አድርጎታል። በመሆኑም ከግቡ ክልሉ ብዙ ሳይርቅ ከሚከላከለው የኋላ ክፍሉ ፊት ባሉ ቦታዎች ላይ ከሚቋረጡ ኳሶች በፍጥነት ወደ ፊት የመጣል አማራጭን ቢወስዱ ከፊት ሲነጠሉ ለሚታዩት አጥቂዎች የተሻሉ ዕድሎችን የመፍጠር ዕድል ይኖራቸዋል።
ከዚህ ውጪ አዲስ አበባ የአርባምንጭን የማጥቃት እሳቤ ዝቅ አድርጎ በመግባት በመከላከል ሽግግሮች የአንድ ለአንድ ግንኙነት ላይ ያሳይ የነበረው የትኩረት ችግር በመከላከያው ጨዋታም ከተደገመ ዋጋ መክፈሉ የሚቀር አይመስልም። መከላከያም እንደ አርባምንጭ ሁሉ በቆሙ ኳሶች የማይታማ መሆኑም መረሳት የለበትም። በጦሩ በኩል ለመከላካል ከፍ ያለ ትኩረት በሰጠበት የሰበታው ጨዋታ ላይ ከትኩረት ማጣት ግብ ሲያስተናግድ መታየቱ ተደጋጋሚ የግብ ዕድል ለሚፈጥሩት አዲስ አበባዎች በር ሊከፍት ይችላል።
አዲስ አበባ ከተማ ምንም ጉዳት እና ቅጣት ዜና የሌለበት ሲሆን በመከላከያ በኩል ሠመረ ሀፍተይ እና አሌክስ ተሰማ ከጉዳታቸው ቢያገግሙም በነገው ጨዋታ የመሰለፍ ዕድላቸው የጠበበ ነው ፤ አዲሱ አቱላ ግን ለጨዋታው ዝግጁ ነው። በተጨማሪም አዲሱ ጊኒያዊ አጥቂ ባዳራ ናቢ ሲላ የወረቀት ጉዳዩን ጨርሶ የመጀመሪያ ጨዋታውን እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– በ2009 የውድድር ዓመት የተገናኙባቸው ጨዋታዎች በመከላከያ 2-1 እና 1-0 አሸናፊነት ሲጠናቀቁ ዘንድሮ ግን አዲስ አበባ ከተማ የ3-0 ድልን አሳክቷል።
ግምታዊ አሰላለፍ
አዲስ አበባ ከተማ (4-3-3)
ዳንኤል ተሾመ
አሰጋኸኝ ጴጥሮስ – ዘሪሁን አንሼቦ – ኢዮብ በቀታ – ሳሙኤል አስፈሪ
ሙሉቀን አዲሱ – ቻርለስ ሩባኑ – ኤሊያስ አህመድ
እንዳለ ከበደ – ሪችሞንድ ኦዶንጎ – ፍፁም ጥላሁን
መከላከያ (4-4-2)
ክሌመንት ቦዬ
ግሩም ሀጎስ – ኢብራሂም ሁሴን – አሚን ነስሩ – ዳዊት ማሞ
አዲሱ አቱላ – ኢማኑኤል ላርዬ – ምንተስኖት አዳነ – ቢኒያም በላይ
እስራኤል እሸቱ – ባዳራ ናቢ ሲላ