ቅዱስ ጊዮርጊስ በምሽቱ ጨዋታ ድሬደዋን ድል ካደረገ በኋላ አሰልጣኞቹ ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ስለዋንጫው ስሜት
“አሁንም እኔ ስለዋንጫው አይደለም ማውራት የምፈልገው በየዕለቱ ስለሚኖሩ ጨዋታዎች ያሉንን አቀራረብ እየሄድንበት ስላለው ነገር ነው የማስበው ፤ ተጋጣሚዎቻችን የተለያዩ ናቸው። ለዛ ነው ሁሌ እየተዘጋጀን የምንመጣው።
ከአስረኛው ደቂቃ በኋላ ስለመቀዛቀዛቸው
“እንደቡድን እነርሱ የራሳቸው ታክቲክ አላቸው ያንን ለመተግበር ነው የመጡት። እኛ ደግሞ ተረጋግተን የተሻለ ነገር ማድረግ እንደምንችል እናቀዋለን። ተረጋግተን ማድረግ የምንፈልገውን እንደምናደርግ ተነጋገርን ጊዜውን ጠብቀን አደረግን ከፈጣሪ ጋር ጥሩ ውጤት ይዘን ወጥተናል።
ስለቡድኑ የማጥቃት እና የመከላከል ሂደት መመጣጠን
“አዎ በጣም እየጠበቀ ነው። እንደ ቡድን ተከላካይ ፣ አማካይና አጥቂዎቹ ሁሉ በጋራ ነው የሚሰሩት። ከዚህም በኋላ አቅማቸውን ካወጡ የተሻለ ነገር ይሰራሉ። ማንም ተጫዋች ገባም ወጣ ቡድናችን እንደ ቡድን እየሰራን ስለሆነ ውጤቱ ራሱ ይገልፀዋል።”
አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ – ድሬደዋ ከተማ
የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮችን ለማቆም ያቀዱት ስላልተሳካበት ምክንያት
“ቀደም ሲል እንደተናገርኩት የቆመ ኳስ የመጠበቅ አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ እዚህ ላይ ተዘጋጅተን ነበር። ያው በሰጋነው ልክ አልቀረም ያገኙትን በአግባቡ ተጠቅመው ነጥባቸውን አግኝተው ወጥተዋል። እንደ አጠቃላይ ጥሩ ነበሩ ማሸነፉ ይገባቸዋል።
ድሬደዋ ከመጀመርያው አስራ አምስት ደቂቃ በኋላ ያሳየውን ጥሩ እንቅስቃሴ ስላለመቀጠሉ
“አዎ ይሄ ነው ፤ ከአስር ደቂቃ በኋላ ማስቀጠል አልቻልንም። ኳሶች ይቆራረጡ ነበር ፤ ኳሶቹ ሲሄዱ የእግጠኝነት ችግር ይጎላቸው ነበር። እነዚህ ላይ በቀጣይ ሰርተን እንመጣለን እንጂ በግልፅ የሚታይ ችግር ነው። ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያደረግናቸው ጥረቶች ነበሩ ፤ በቀጣይ አስተካክለን እንመጣለን።
በመሐመድ አብዱለጢፍ ላይ ያሳዩት ትዕግስተኝነት ዋጋ ስለማስከፈሉ
“ተነጋግረናል ፤ ሊቆጣጠር አልቻለም። ቢጫ ያየበት ሁኔታ ግን ትንሽ ችግር ነበረበት ፤ ሆን ብሎ የሄደበት አይደለም። ነገር ግን ትንሽ ራሱን መቆጣጠር ነበረበት። ምንአልባት እርሱ ባይወጣ ኖሮ ጨዋታው ይህ መልክ አይኖረውም የሚል ግምት አለኝ።”