[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ነገ አመሻሽ በሚደረገው ጨዋታ ዙሪያ ተከታዩን ቅድመ ዳሰሳ አጠናክረናል።
በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኙት ሰበታ ከተማዎች ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት ያገኙትን ሦስት ነጥብ ለመድገም እና ከአስጊው ቀጠና ለመውጣት የሚያደርጉትን ጥረት ለማፋጠን ድል ለማግኘት እንደሚጫወቱ እሙን ነው። በተቃራኒው ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በሸገር ደርቢ መርሐ-ግብር አራት ጎሎች ተቆጥሮባቸው የተረቱት ኢትዮጵያ ቡናዎች በበኩላቸው ከከባዱ ሽንፈት ለማገገም እንዲሁም ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ዳግም ከድል ጋር ታርቀው የደረጃ መሻሻል ለማምጣት ሦስት ነጥብን ተቀዳሚ ዓላማ አድርገው መጫወታቸው የማይቀር ነው።
በጊዜያዊ አሠልጣኙ ብርሃን ደበሌ የሚመራው ሰበታ ከተማ ተጋጣሚ ቡድኖችን ከልክ በላይ የሚያከብረውን መከላከያ ገጥሞ ባለቀ ሰዓት በተገኘ ግን ባሸነፈበት ፍልሚያ ከወትሮ የተለየ ፍላጎት እና ረሀብ ይታይበት ነበር። ይህ ተነሳሽነት ደግሞ ከተጋጣሚው በኳስ ቁጥጥርም ሆነ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር እጅግ ተሽሎ እንዲገኝ አድርጎታል። በሁለት የአራት ተጫዋቾች ስብጥር የተከላካይ እና አማካይ እንዲሁም ሁለት አጥቂ ወደ ሜዳ የገባው ቡድኑ ከዚህ ቀደም የነበረበትን ከኳስ ውጪ ያለ አደረጃጀት በመጠኑ አርሞ ለመከላከያዎች አልመች ብሎ ነበር። ከኳስ ጋርም በወሳኝ ቦታዎች ብልጫ እየወሰደ ለመጫወት ጥሯል። በዋናነት ደግሞ ዱሬሳ ሹቢሳ እና ኃይለሚካኤል አደፍርስ በተሰለፉበት የግራ መስመር በኩል የጥቃት ምንጩን በማድረግ ሲንቀሳቀስ ታይቷል።
ከላይ እንደገለፅነው ሰበታ በነገውም ጨዋታም የግራ መስመሩን በደንብ ለመጠቀም እንደሚያስብ ይገመታል። ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንደ መከላከያው ጨዋታ ኳስ ለመንሸራሸር ፍላጎት እንደማያሳይ የሚገመት ሲሆን ሽግግሮችን በጥሩ ስኬት በመፈፀም ከጨዋታው አንዳች ነገር ይዞ ለመውጣት እንደሚጥርም ይታሰባል። ከዚህ ውጪ ቡናን የሚገጥሙ አብዛኞቹ ቡድኖች እንደሚያደርጉት በላይኛው የሜዳ ክፍል የሚኖርን የተጋጣሚ የኳስ ምስረታ ለማበላሸት እና ዕድሎችን ብዙም ሳይርቁ ለመፍጠር መታተራቸው የማይቀር ነው። በተቃራኒው ግን በ17 የሊጉ ጨዋታዎች በርካታ ግቦችን በማስተናገድ ግንባር ቀደም የሆነው ቡድኑ የቡናን ፈጣን የወገብ በላይ ተጫዋቾች እንዴት ይቆጣጠራል የሚለው ጉዳይ የሚጠበቅ ነው።
ዓምና ሁለተኘ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ኢትዮጵያ ቡና ዘንድሮ ከወራጅ ቀጠናው የሚለየው ሁለት ደረጃዎች ብቻ ናቸው። በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እጅግ የተዳከመው ቡድኑ ባሳለፍነውም ሳምንት በታላቁ ሸገር ደርቢ አራት ለምንም ተረቶ የሜዳ ላይ ክፍተቶቹ በግልፅ ጎልተው ታይተዋል። በተለይ በመከላለል እና ኳስ እንደተነጠቁ ባለ የሜዳ ላይ ቅርፅ ቡድኑ ከፍተኛ ክፍተት እንዳለበት ተስተውሏል። በዚህም በድምሩ 20 የግብ ማግባት ዕድሎች ተፈጥረውበት አራቱን አስተናግዷል። ከወገብ በላይም አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ተስኗቸው ከሜዳ ወተዋል። ምናልባት የነገው ተጋጣሚያቸው በአንፃራዊነት ቀለል ያለ በመሆኑ ያን ያህል ይቸገራሉ ብሎ መናገር ባይቻልም ስህተቶችን ካልቀነሱ ግን አደጋ ላይ መውደቃቸው የማይቀር ነው።
የካሣዬ ቡድን ወደ ሪትም እንዲገባ የሚያስችለው ሦስት ነጥብን ለማግኘት ከሰበታ የቀለለ ተጋጣሚ የሚያገኝ አይመስልም። ከላይ እንደገለፅነው ሰበታ አንፃራዊ የእንቅስቃሴ መሻሻል እያሳየ ቢመስልም አሁንም በሁሉም የሜዳ ክፍሎች ችግሮች ይታዩበያል። ከምንም በላይ ደግሞ በመከላከሉ ረገድ ያለው መዋቅር መላላት ካልተቀረፈ የቡና የአጥቂዎች እምብዛም ላይቸገሩ ይችላሉ። በቡድናዊ መዋቅር እና በግለሰብ ስህተት የሚፈጠረውን የኋላ መስመር ሽንቁር ለመድፈን ደግሞ ከኳስ ጀርባ በርከት ብለው ለመጫወት እንደሚያስቡ ይገመታል። ቡና በተቃራነው እንደተለመደው ኳሱን በትዕግስት በማንሸራሸር ክፍተቶችን ለማግኘት እንደሚያስብ ቀድሞ መናገር ይቻላል። አቡበከር ናስር ደግሞ የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት መሰረት በመሆን ለተከላካዮች የፈተና ጊዜን ሊሰጥ ይችላል።
ቡናማዎቹ በነገው ጨዋታ በቅጣት ምክንያት የሚያጡት ተጫዋች ባይኖርም አራት ተጫዋቾቻቸው ግን ጉዳት ላይ መሆናቸው ተሰምቷል። በዚህም ወንድሜነህ ደረጄ፣ ኃይሌ ገብረትንሣኤ፣ አቤል እንዳለ እና የአብቃል ፈረጃ ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆናቸውን አውቀናል።
እርስ በርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለዘጠኝ ጊዜያት ተገናኝተዋል። በእነኚህ ግንኙነቶች ኢትዮጵያ ቡና ሦስት ሰበታ ከተማ ደግሞ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፉ ቀሪዎቹን አራት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ፈፅመዋል። በዘጠኙ ጨዋታዎች 16 ጎሎች ሲቆጠሩ ዘጠኙን ቡና ሰባቱን ሰበታ አስመዝግበዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሰበታ ከተማ (4-4-2)
ምንተስኖት አሎ
ጌቱ ኃይለማርያም – በረከት ሳሙኤል – አንተነህ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ
ሳሙኤል ሳሊሶ – በኃይሉ ግርማ – ቢያድግልኝ ኤሊያስ – ዱሬሳ ሹቢሳ
ቢስማርክ አፒያ – ዴሪክ ኒስባምቢ
ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)
አቤል ማሞ
አስራት ቱንጆ – አበበ ጥላሁን – ገዛኸኝ ደሳለኝ – ሥዩም ተስፋዬ
ሮቤል ተክለሚካኤል – አማኑኤል ዮሐንስ – ዊሊያም ሰለሞን
ሚኪያስ መኮንን – አቡበከር ናስር – ተመስገን ገብረፃዲቅ