ሪፖርት | አዲስ አበባ ከወራጅ ቀጠናው ቀና ብሏል

መከላከያን 2-0 በማሸነፍ ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር የተገናኘው አዲስ አበባ ወደ 13ኛ ደረጃ መጥቷል።

በ4-1-3-2 የጀመረው አዲስ አበባ ከተማ ከአርባምንጩ ጨዋታ ከኋላ አዲስ ፈራሚው አዩብ በቀታ እና ሮቤል ግርማን በዘሪሁን አንሼቦ እና ሳሙኤል አስፈሪ ምትክ ሲያሰልፍ መሀል ላይ የሙሉቀን አዲሱ ቦታ በመሀመድ አበራ ተሸፍኗል። ወደ 4-2-3-1 የተመለሱት መከላከያዎች ከሰበታው ሽንፈት ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ አዲሱ አጥቂያቸው ባዳራ ሲይላን በእስራኤል እሸቱ ተክተዋል።

ቀዝቀዝ ያለ እና የጉልበት አጨዋወት ያመዘነበት አጀማመር በነበረው ጨዋታ ሁለቱም በድኖች ኳስ መስርተው ለማጥቃት ተንቀሳቅሰዋል። የኳስ የቁጥጥር ብልጫ የነበራቸው መከላከያዎች የጠራ የግብ ዕድል ባይፈጥሩም የተሻለ ፍሰት ያለው ጥቃት ሲያሳዩ ቆይተዋል። አመዛኙን ጊዜ ከኳስ ውጪ ወደ ራሳቸው ሜዳ የተገፉት አዲስ አበባዎች በአንፃሩ በቅብብል ዕድል መፍጠር ቢከብዳቸውም ከቆመ ኳስ በሙከራም በግብም ቀዳሚ ሆነዋል።

17ኛው ደቂቃ ላይ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ከግራ በቀጥታ ወደ ግብ የላከው የርቀት ቅጣት ምት በክሌመንት ቦዬ ጥረት የዳነ ነበር። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ግን ከዳንኤል ተሾመ የተለጋ የመልስ ምት ኳስ ሲነጥር የመከላከያ ተከላካዮች መቆጣጠር ሳይችሉ ሪችሞንድ ኦዶንጎ በሩጫ ከጀርባ በመግባት አጋጣሚውን ወደ ግብነት ቀይሮታል።

ጨዋታው ወደ ውሃ ዕረፍት ሊያመራ ሲል የቢኒያም በላይን የቅጣት ምት ምንተስኖት አዳነ በግንባሩ ሞክሮ ኢላማውን ሳይጠብቅ ከቀረበት ሙከራ ውጪ ጦሩ በአጋማሹ ምላሽ መስጠት አልቻለም። ይበልጥ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የተወሰደባቸው አዲስ አበባዎችም በቀጥተኛ ኳሶች አደጋ ሊፈጥሩ የሚችሉባቸው ቅፅበቶች አልፎ አልፎ ቢታዩም ሙከራዎችን ሳያደርጉ ጨዋታው ተጋምሷል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ይበልጥ ተቀዛቅዞ በተጨዋቾች መሀል የሚፈጠሩ ግጭቶች እና እነሱን ተከትለው የሚሰጡ የርቀት ቅጣት ምቶች ተበራክተው ታይተዋል። የጦሩ የኳስ ቅብብል በተሻለ ሁኔታ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ሲደርስ ቢታይም ወደ ሙከራዎች በመቀየሩ ፍሬያማ መሆን አልቻሉም። የአዲስ አበባዎች መልሶ ማጥቃትም እንዲሁ አስፈሪ ሆኖ አልታየም።

ደካማው ጨዋታ የአጋማሹን ቀዳሚ ሙከራ 81ኛው ደቂቃ ላይ ሲያሳየን ተቀያሪው ቢኒያም ጌታቸው የፍፁም ጥላሁንን ከግራ የተነሳ ኳስ በግንባሩ ሞክሮ ክሌመንት ቦዬ አድኖበታል። 90ኛው ደቂቃ ላይ ጦሩ ከቢኒያም በላይ ቅጣት ምት ያደረገውን የግብ ጥረት ያከሸፉት አዲስ አበባዎች በመልሶ ማጥቃት ጦሩ ደጃፍ ደርሰው ሪችሞንድ ኦዶንጎ ለማስቆጠር ያደረገውን ጥረት ዳዊት ማሞ ሲያቋርጥ በሰራው ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። አጋጣሚውንም ራሱ ኦዶንጎ አስቆጥሮ ጨዋታው በአዲስ አበባ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ አዲስ አበባ ነጥቡን 18 አድርሶ 13ኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ መከላከያ በአንድ ነጥብ እና በአንድ ደረጃ ከፍ ብሎ ተቀምጧል።