በአዲስ አበባ አሸናፊነት ከተጠናቀቀው የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ – አዲስ አበባ ከተማ
ጨዋታውን ስላሸነፉበት መንገድ
“በእርግጥ ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት ወራጅ ቀጠና ውስጥ ስላለን ማሸነፍ በጣም ያስፈልገናል። ለዛም ነው የአጨዋወት መንገዳችንን ቀይረን ማጥቃቱ ላይ ትኩረት አድርገን የሰራነው። በእርግጥ መከላከያ ቀላል የሚባል ቡድን አይደለም ውጤቱ ለሁላችንም ስለሚያስፈልግ ፤ የፈለግነውን ነገር አሳክተናል።
በሁለት ጨዋታ አምስት ጎል ማስቆጠራቸው መከላከያን ቀላል ተጋጣሚ ስለማስባሉ
“መከላከያ ቀላል ተጋጣሚ አይደለም። ጠንካራ ቡድን ነው ፤ ስብስቡም ጠንካራ ነው። ግን እኛ ለምሳሌ መሀል ላይ የተወሰደብንን ብልጫ አይተን ለማረም ሞክረናል። ያንን ስናደርግ ማጥቃቱ ደግሞ ስለሳሳ ወደ ማጥቃቱ ሄደናል። ምክንያቱም ማጥቃት መከላከልም ስለሆነ ያን ለማረም ሞክረናል።
ስለ እንዳለ ከበደ ቅያሪ
“ሁል ጊዜ የታክቲክ ለውጥ ሲኖር ጥሩዉንም ተጫዋች ልታስወጣ ትችላለህ። እንጂ እንዳለ ጥሩ ነበር ፤ ይንቀሳቀሳል። ከዚህ በፊትም እንዲህ ነው። ግን የሲስተም ለውጥ ስታደርግ የግድ አንዱ ላይ መወሰን አለብህ። ያን መሰረት አድርጌ እንጂ እንዳለ ጥሩ ልጅ ነው።
ቡድኑ ግብ ለማግኘት ሪችሞንድ ኦዶንጎ ላይ ስለመንጠልጠሉ
“እሱ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ አይደለም። አንዱ ጥሩ አስቆጣሪያችን ፍፁም ነው። ፍፁም ትንሽ ማስተካከል የሚባው ነገር አለ። ያን ከስተካከለ ፍፁምም እንዳለም ያስቆጥራሉ።”
አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ – መከላከያ
ብልጫ እንዲወሰድባቸው ስላደረገው ምክንያት
“የመጀመሪያዋ ጎል ነች። በአቋቋም የሰራነው ስህተት ፤ በሁለት ልጆች መካከል ተጫዋቹ አምልጦ ያገባው ጎል። ከዛ በፊት ደህና እንቅስቃሴ ላይ ነበርን። ጎሉ ከገባ በኋላ መውረድ ጀመርን ማለት ነው። ከዛ በኋላ እነሱ ብልጫ እያሳዩ መጡ።
ግቦች ስለማስቆጠር ድክመታቸው
“በመጀመሪያው ዙር ላይም ብዙ ጎሎች አላገባንም ፤ ብዙ በመከላከል ነበር ጥሩ ነገር የነበረን። አሁን ደግሞ በሦስት ጨዋታ ጎሎች እያገባን አይደለም። ጎል ማግባት ማለት ነጥብ ማግኘት ማለት ነው ስለዚህ ጎል ማግባት ወሳኝነት አለው።
ስለቀጣይ ጨዋታዎች ጫና
“ማንኛውም ጨዋታ ልዩነት የለውም ይሄም ጫና ነው ፣ ያለፈውም ጫና ነው የወደፊቱም ጫና ነው። ስለዚህ በእያንዳንዱ ጨዋታ አቅም በፈቀደ ውጤት ይዞ ለመውጣት መጫወት ነው እንጂ አሁን ጨዋታ የምንመርጥበት አይደለም። ይሄ ቀላል ይሄ ከባድ የሚባል የለም ለእያንዳንዱ ጨዋታ ራስን አዘጋጅቶ መምጣት ነው። “