ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ከድል ታርቋል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በረከት አማረ ድንቅ ሆኖ ባመሸበት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ሰበታ ከተማን በአቡበከር ናስር እና ሮቤል ተክለሚካኤል እጅግ ድንቅ ግብ ታግዘው በመርታት ከአምስት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ሙሉ ሦስት ነጥብ አስመዝግበዋል።

በአሰልጣኝ ብርሃኑ ደበሌ የሚመሩት ሰበታ ከተማዎች መከላከያን ካሸነፈው ስብስብ አንድ ለውጥ ያደረጉ ሲሆን በዚህም አጥቂ ስፍራ ላይ ቢስማርክ አፒያን አስወጥተው ፍፁም ገ/ማርያምን ተክተው ያስገቡ ሲሆን በአንፃሩ የአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌው ስብስብ ደግሞ በደርቢው በቅዱስ ጊዮርጊስ አሰቃቂ ሽንፈት ካስተናገደው ስብስብ ሁለት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን አቤል ማሞ እና ተመስገን ገ/ኪዳንን አስወጥተው በምትካቸው በረከት አማረን እና ዊልያም ሰለሞንን በመጀመሪያ ተመራጭነት ተጠቅመዋል።

በጨዋታው እንደተለመደው በኳስ ቁጥጥር ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ ጥረት ያደርጉ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከሚነጠቋቸው ኳሶች መነሻ ያደረጉ አደገኛ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን በሰበታ ከተማዎች በኩል በመጀመሪያው አስር ደቂቃ ሲዘነዘሩ ተመልክተናል። እነዚህ ሂደቶችን ግን በጨዋታው ዳግም ወደ መጀመሪያ ተሰላፊነት የተመለሰው በረከት አማረ በማምከን ኢትዮጵያ ቡናን በጨዋታው ማቆየት ችሏል።

ለሰበታዎች የመጀመሪያ በነበረው የግብ ማግባት አጋጣሚ 2ኛው ደቂቃ ላይ ዴሪክ ንስምባቢ ከራሱ ሜዳ ኳስ እየነዳ ወደ ቡና ሳጥን ከተጠጋ በኃላ ያሻማውን ኳስ ፍፁም ገ/ማርያም ወደ ግብ ቢሞክርም በረከት አማረ በግሩም ሁኔታ ያዳነበት ሲሆን በ6ኛው ደቂቃም እንዲሁ ዱሬሳ ሹቢሳ በተከላካዮች መሀል ያደረሰውን ግሩም ኳስ ፍፁም ገ/ማርያም ከመጠቀሙ በፊት በረከት በፍጥነት ግቡን ለቆ በመውጣት ያቋረጠበት እንዲሁም በተጨማሪነትም በ8ኛው ደቂቃ አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ ከሳጥን ውጭ ያደረገውን ሙከራ ያመከነበት ሂደት የሚደነቅ ነበር።

በጨዋታው ቀስ በቀስ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን መጠጋት የጀመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በ10ኛው ደቂቃ በላይኛው በሜዳ ክፍል ሮቤል የነጠቀውን ኳስ ተጠቅሞ አቡበከር ናስር የሞከራት እና ለጥቂት ወደ ውጭ በመወጣችት ኳስ የመጀመሪያ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። ተነቃቅተው መጫወት የጀመሩት ቡናዎች በ15ኛው ደቂቃ ላይ በአቡበከር ናስር አማካኝነት ቀዳሚ ሆነዋል። ሮቤል ተክለሚካኤል ከግራ መስመር ወደ ውስጥ አጥብቦ ከገባ በኋላ ያቀበለውን ኳስ አቡበከር ከሳጥኑ ጠርዝ በቀጥታ ወደ ግብ በመላክ አስቆጥሯል።

በጨዋታው ከግቧ መቆጠር በኋላ ኢትዮጵያ ቡናዎች ጨዋታውን በተሻለ መልኩ ተቆጣጥረው በመጫወት ረገድ ተሻሽለው ብንመለከትም በጨዋታው የጠሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በአንፃሩ ሰበታ ከተማዎች ደግሞ በተለይ በዛሬው ጨዋታ ከአጥቂው ፍፁም ገ/ማርያም ጀርባ ሲጫወት የነበረው ዴሪክ ንሲምባቢ በግሉ ያደርገው የነበረው ጥረት ሆነ ከመስመር በሚነሱ ኳሶች አደጋ ለመፍጠር ቢታትሩም ውጤታማ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል።

በጨዋታው 40ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ ቡናዎች በኳስ ምስረታ ሂደት ወቅት አበበ ጥላሁን አደገኛ ቦታ ላይ ከልክ ባለፈ የራስ መተማመን መነሻነት የተነጠቀውን ኳስ ሰበታዎች ወደ ኢትዮጵያ ቡና የግብ ክልል ይዘው ቢደርሱም በረከት አማረ እና የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ተረባርበው አድነውባቸዋል። በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ሰበታ ከተማዎች ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች በፍፁም ገ/ማርያም እና ዴሪክ ንሲምባቢ አማካኝነት አደገኛ ሙከራዎችን ቢያደርጉም በጨዋታው ድንቅ የነበረው በረከት አማረ አድኖባቸዋል።


በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮም እንደ መጀመሪያው ሁሉ ሰበታ ከተማዎች ኢትዮጵያ ቡና ላይ ከፍተኛ ጫን በማሳደር ነበር የጀመሩት። በተለይም በ48ኛው ደቂቃ በኃይሉ ግርማ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታት እና በረከት አማረ ያዳነባቸው ኳስ ተጠቃሽ አጋጣሚ ነበር።
ሰበታ ከተማዎች በአንፃራዊነት ኢትዮጵያ ቡና ላይ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ ቡናማዎቹን ወደ ራሳቸው የሜዳ አጋማሽ በጥልቀት እንዲገፉ ማስገደድ የቻሉ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ በመልሶ ማጥቃት ተጋጣሚን መጉዳት የሚችሉባቸው በርካታ አጋጣሚዎችን ቢያገኙም እነዚህን ዕድሎች መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። ከመስመር በሚሻሙ ኳሶች እንዲሁም ከቆሙ ኳሶች ተደጋጋሚ ዕድሎችን መፍጠር የቻሉት ሰበታዎች ጥራት ያላቸው ሙከራዎችን በማድረግ ረገድ ግን ውስንነት ነበረባቸው።

ደቂቃዎች እየገፉ ሲሄዱ ኢትዮጵያ ቡናዎች በተሻለ መልኩ ወደ ጨዋታው መመለስ የቻሉ ሲሆን ፍፁም ለማጥቃት ትኩረት ከሰጡት ሰበታ ከተማ ተከላካዮች በስተጀርባ የሚገኘውን ክፍት ሜዳ ተጫዋቾችን በማስገባት ለመጠቀም ተደጋጋሚ ጥረቶችን ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።

በ80ኛው ደቂቃ ላይ ግን የኢትዮጵያ ቡናው ኤርትራዊ አማካይ ሮቤል ተክለሚካኤል የምንተስኖት አሎን ከግቡ በጥቂቱ መውጣቱን ተከትሎ ከመሀል ሜዳ አካባቢ በቀጥታ ወደ ግብ የላከው ኳስ በግሩም ሁኔታ ከመረብ ተዋህዳ የኢትዮጵያ ቡናን አሸናፊነት የማታ ማታ አስተማማኝ ማድረግ ችሏል።

በሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ድላቸውን ያሳኩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በ24 ነጥብ ወደ ስድስተኛ  ደረጃ ከፍ ማለት የቻሉ ሲሆን በአንፃሩ ሰበታዎች አሁንም በ12 ነጥቦች በሊጉ ግርጌ ይገኛሉ።