የምሽቱ ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ሀሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
አሰልጣኝ ብርሀን ደበሌ – ሰበታ ከተማ
የተሳቱ አጋጣሚዎች የሚያስቆጩ ስለመሆናቸው
“አዎ በትክክል ሁለት እና ሦስት ኳሶች መግባት የሚችሉ ነበሩ፡፡ እነዛን አለማግባችን እነሱን እንዲነሳሱ አድርጓቸዋል፡፡ ያንን ደግሞ ለመጠቀም እንደገና ሙከራ አደረግን ሌሎች ኳሶችን አግኝተን ነበር ፤ ማግባት ባለመቻላችን ዋጋ ከፍለናል፡፡
በጨዋታው መጀመሪያ የነበራቸውን ብልጫ ስላለማስቀጠላቸው
“አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ይፈጠራሉ። በኳስ ላይ ለማሸነፍ የወሰድካቸው እንቅስቃሴዎች በመሀል ላይ የተወሰነ ክፍተት ከተገኘ በዛ አጋጣሚ ደግሞ ከገባብህ እየወረድክ ነው የምትሄደው ፤ እንደገና ለማግባት ሌላ ዋጋ ትከፍላለህ። እንዳልኩህ አንድ ለባዶ ሆነን እኛ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ማድረግ አለብን ፤ ያንን ለማድረግ ሞከርን በመሀል ደግሞ ያልታሰበ ኳስ ገባብን። ድጋሚ ሁለተኛ ጎል ሲገባ አይተህ እንደሆነ ጥሩ ለመሆን ሞከርን በአጠቃላይ ይሄን ለማሻሻል እንሰራለን፡፡
ስለአፒያ ቅያሪ
“አማካይ ብቻ አይደለም አፒያ ፤ ወደ ፊት ይበልጥ ይጫወት ነበር፡፡ ከመከላከያ ጋር ስንጫወት ከዱሬሳ ጋር ነበሩ። እንደገና በፍፁም ነው የቀየርነው እና ፎርዋርድ ስለሚጫወት ነው ያስገባነው እንጂ ሙሉ በሙሉ የአማካይ ሥራን አይደለም የሚሰራው። ስለዚህ እዛ ጋር ደግሞ አቅም ስላለው ያንን ኳስ ሆልድ አድርጎ ለሌሎች ሽፋንን ይሰጣል፡፡አብዱላፊዝ እና ዘላለም ተመሳሳይ አጨዋወት ነው ያላቸው ያው ፊት ተደራቢ አጥቂ ሆኖ የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ አብዱላፊዝ ጥሩ ነበር ጥሩ ተንቀሳቅሶ ነበር ያንን ማስቀጠል ባለመቻሉ እንደሁም የተሻለ ልምድ ያለው ዘላለም ነው እሱ ደግሞ የበለጠ ይጠቅመናል ብለን ነበር ያሰብነው ፤ እንደነበረው እንዳሰብከው አይሆንም አንዳንድ ጊዜ ኳስ ይሄንን ነው የሚመስለው፡፡
አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና
ስለ ጨዋታው
“ሁለት ዓይነት መልክ ነበረው ጨዋታውን መቆጣጠር እንፈልጋለን፡፡ ስህተቶች ሲፈጠሩ ደግሞ የተዘበራረቀ ነገር ነበር፡፡ በቀላሉ የኛ ኋላ ያሉ ተጫዋቾችን ሰበታዎች ያገኟቸው ነበር እና ይታያል ይሄ ትንሽ የመጨነቁ ነገር ይታያል፡፡ ጎል የመፈለግ ነገር ነው ጎል ፈልገን ደረጃችንን ከፍ የማድረግ ነገር አለ እና ጫናው ይታያል ፤ በግልፅ ይታያል። በደንብ አብዛኛውን የጨዋታ ጊዜ መቆጣጠር የቻልንበት አይደለም ይታያል ያ ሜዳ ላይ፡፡
በመጀመሪያው አስራ አምስት ደቂቃ ብልጫ ተወስዶባቸው በሂደት ወደ ጨዋታ ስለ ገቡበት ሂደት
“መጀመሪያ ላይ ክፍተቶች ነበሩ፡፡ ከዛ አንዳንድ የገመትናቸው ነገሮች ነበሩ ከጨዋታው በፊት እነዛን ነገሮች እንዳሰብናቸው ነው ያገኘናቸው፡፡ ግን ከዛ በኋላ የእነሱ መስመር ላይ ያሉ ልጆች በተወሰነ ደረጃ ማጥበብ ጀምረው ነበር። የነበረው መስመር ላይ ያሉትን ከኋላ ያሉ የኛን ልጆች ለመቆጣጠር እና እንደገና ደግሞ የኛን የመሀል ተጫዋቾች ለመቆጣጠር በዛ ውስጥ የሚፈጠሩ ስህተቶች ነበር እና ያንን ወዲያውኑ ወደ ማጥቃት ሂደት ውስጥ እየገቡ አንዳንድ ዕድሎችን አግኝተው ነበር። እረፍት ላይ እነዛን ልጆች የሚያጠቡትን የነሱን የመስመር ልጆች ተቆጣጥረው እንዲጫወቱ ነው ያደረግነው። ግን አለ ጫናው አለ ፤ ይታያል ልጆቹ ላይ፡፡
ስለ ሮቤል ተክለሚካኤል አስደናቂ ጎል
“አዎ ጎሉ ያው እንግዲህ የልጁን ዕይታ የሚገልፅ ነው። ይሄ ለጎል ብቻ ሳይሆን ሜዳ ውስጥ ባለ ሂደትም እንዲሆን ነው የምንፈልገው። ብዙ ጊዜ ተጋጣሚ መጥቶ ያጠበብክበት ቦታ ላይ ተጭነው ለመንጠቅ ነው። እና በተወሰነ ርቀው ስለነበረ ነፃ ሰው ይኖራል፡፡ ያንን ለጎል ብቻ ሳይሆን ለሂደቱም እንዲሆን ነው የምንፈልገው ያው እሱ ለጎል አድርጎታል ፤ ጎሉ የልጁን አቅም የሚያሳይ ነው፡፡