የ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኑን የተመለከተ መግለጫ ተሰጥቷል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

👉 ” ከሀገር ይልቅ ቅድሚያ ለክለቦቻቸው ሰጥተዋል።…

👉 “ሁለት ትልልቅ አሰልጣኞች በአንድ ላይ ሲሰሩ መገፋፋት ይኖራል።…

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ብሔራዊ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ካለበት የማጣሪያ ጨዋታ በፊት መግለጫ ተሰጥቷል።

ሕንድ ለምታሰናዳው ከ17 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ ሁለተኛ ዙር ማጣርያ የመጀመርያውን ጨዋታ ከደቡብ አፍሪካ አቻው ጋር በጁሀንስበርግ ከተማ የፊታችን ዓርብ የሚያከናውነው ብሔራዊ ቡድናችን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት ዋናው አሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ እና የቴክኒክ ልማት ዳሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ፍራንኮ ጋራ በጋራ በመሆን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ውስን የሚዲያ ባለሙያዎች በታደሙበት እና የአስራ አምስት ደቂቃ ቆይታ የነበረው በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ አስቀድመው አሰልጣኝ እንዳልካቸው ስለ ቡድኑ ዝግጅት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

” ከመጋቢት 21 ጀምሮ ለሃያ ሰባት ተጫዋቾች ጥሪ አድርገናል። በዕለቱ የተገኙት አስራ አምስት ተጫዋቾች ብቻ ነበሩ። የቀሩት አስራ ሁለት ልጆች ባህር ዳር እና ሰበታ ላይ በሚካሄደው ውድድር ምክንያት ሊገኙልን አልቻሉም። ባሉት አስራ አምስት ተጫዋቾች ዝግጅታችንን ቀጥለናል። ከመጋቢት 29 ጀምሮ የቀሩት ልጆች ተቀላቅለዋው እስከ ዛሬ ድረስ ዝግጅታችንን ስናደርግ ቆይተናል። ለደቡብ አፍሪካው ጨዋታ ይመጥናሉ ብለን ያሰብናቸው ልጆች ነበር የጠራነው። በፊት ከነበሩ አዳዲስ ልጆች አራት ከዲላ ፓይለት ፕሮጀክት አንድ ከድሬደዋ ሦስት ከሌሎች ደግሞ ሰባት ልጆች ጨምረን ዝግጅታችንን ሰርተናል። ትንሽ ክፍተት የተፈጠረው የጠራናቸው ተጫዋቾች በወቅቱ አለመምጣታቸው በሥራችን ላይ ጫና ፈጥሯል። ግን ስንዘጋጅ ቆይተናል።” 

በማስከተል ከጋዜጠኞች የተለያያዩ ጥያቄዎች ተነስተው አሰልጣኝ እንዳልካቸው እና አቶ ቴዎድሮስ ተከታዮቹን ምላሾች ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ

ባልተሟላ መንገድ ዝግጅት መጀመራቸው ስለነበረው ተፅዕኖ

” ክፍተቶችን ለመሙላት በተለይ መሐል ሜዳ ላይ በጎደሉ ልጆች ምትክ ጥሪ አድርገናል። ችግሮች አሉ። አሁን ለችግሩ እጅ መስጠት ሳይሆን እንዴት መስራት መሻገር እንችላለን በሚለው ላይ ነው አሁን እየሰራን ያለነው። ውድድር መቋረጥ የለበትም። ያለውን ሁኔታ ታውቃላቹሁ። መጀመርያ ረጅም ጊዜ ተቋርጧል ፤ ባሉት ልጆች እንደምንም ተደርጎ መሰራት አለበት። ይህም ቢሆን አማራጭ የለንም ባሉት ልጆች መስራት አለብን ማሳበብ አያስፈልግም።

ጥሪ ተደርጎላቸው የቀሩትን ተጫዋቾች ለመጥራት ስለ ተደረገው ጥረት

” ጥረቶች አድርገናል። ክለቦች ጋር ለመነጋገር ባህር ዳር ድረስ ሄጃለሁ ፤ ንግግርም አድርጌአለው። ልጆቹን እንዲለቁ ክለቦች ግን የራሳቸውን ውጤት ነው የሚጠብቁት። ከሀገር ይልቅ ቅድሚያ ለክለቦቻቸው እንዲጫወቱ ፍላጎት የነበራቸው። ብዙም ለመነጋገርም ለመደራደር ሞክረናል። አንድ ሁለት ጨዋታ ተጫውተን እንለቅላቸዋለን አሉ ። ይህም ቢሆን አማራጭ የለንም ባሉት ልጆች መስራት አለብን። እነርሱም ከውድድር ሲመለሱ ለመስራት ሞክረናል ፤ ማሳበብ አያስፈልግም።

ስለ ተጋጣሚያቸው ደቡብ አፍሪካ ቡድን ስላላቸቸው መረጃ

“ስለታጋጣሚያችን ደቡብ አፍሪካ ምንም መረጃ የለንም። ጥረት አድርገናል ግን አልተሳካም። ዩጋንዳ ለምሳሌ የተለያዩ ምስሎችን በቪዲዮ ይለቃሉ። ይህን አይቶ መዘጋጀት ይቻል ነበር። ደቡብ አፍሪካ ግን ምንም የሚለቁት ነገር የለም። ቢለቁ እንኳን የቆየ ጨዋታቸውን ነው። ምንም ማድረግ አንችልም ሳንተዋወቅ ነው የምንሄደው። ግን የቻልነውን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን።

ቡድኑ ስለሚገኝበት መንፈስ እና በቀጣይ ከጨዋታው ስለሚጠብቁት ነገር 

” ዝግጅታችን እና የልጆቹ ስሜት ጥሩ ነው። ተነሳሽነታቸው ፍላጎታቸው መልካም ነው። አዳዲስ ከተጨመሩት ልጆች ጋር ያላቸው ቅንጅት አንድነት ደስ ይላል። ይህን በማየት ውጤታችን ጥሩ ይሆናል ብዬ አስባለው። የዝግጅት ቀኑ ጥቂት ቢሆንም እንደብዙ አስበን የኢትዮጵያን ህዝብ ከፈጣሪ ጋር እናስደስታለን ብዬ አስባለሁ።”


አቶ ቴዎድሮስ ፍራንኮ...
ስለአሰልጣኙ የኮንትራት ዘመን

” ከዚህ ቀደም የአሰልጣኝ የውል ዘመን ሦስት ወር ወይ ስደስት ነበር። አሁን ከዚህ አስተሳሰብ መውጣት አለብን ፤ ለእንዳልካቸው እየታየ የሚሻሻል የአንድ ዓመት ኮንትራት ነው የተሰጠው። በዚህ ኮንትራት የሚያቋርጥም የሚያስቀጥልም ነገር አለው። ለሃያ ዓመት በታች አሰልጣኝ ለሁለት ዓመት ኮንትራት ስንሰጥ የምንጠብቃቸው ማሳካት ያለባቸው ነገሮች አሉ። ካላሳካ የማያስቀጥሉ የስምምነት ኮንትራቶች አሉ።

በሌሎች ጋዜጣዊ መግለጫዎች ከዚህ ቀደም ተገኝተው ስለማያቁበት ምክንያት

” እግርኳስ ለተባለ ሁሉ ትኩረት እንሰጣለን። ትኩረት ባለ መስጠት አይደለም ያልተገኘሁት። ከትልልቆቹ የብሔራዊ ቡድን የዕድሜ ዕርከን ይልቅ ለታችኛው የዕድሜ ዕርከን መገኘት ያስፈልጋል። ከሥራ ጨና ያለነው ሰዎች ጥቂት በመሆናችን ነው ያልተገኘነው። ስለዚህ ከሥራ መደራረብ ነው ያልተገኘንበት።

ስለምክትል አሰልጣኝ ቴዎድሮስ ደስታ መነሳት

“ከብሔራዊ ቡድኑ የተለያየበት ሁኔታ አንደኛ የሴቶች እግርኳስ እስከ 2025 ድረስ 80% በሴቶች መሸፈን አለበት። ሁለተኛ በካፍ መስፈርት ምክትል አሰልጣኞች የህክምና ባለሙያዎች ሴት መሆን አለባቸው ይላል። ሦስተኛ ልጆቹን ጠርተን ወደ ዝግጅት ስንገባ ከአሰልጣኝ አባላቶች ጋር ውይይት ሲደረግ እና የእኛም ቴክኒክ ኮሚቴ መረዳት ሁለት ትልልቅ አሰልጣኞች በአንድ ላይ ሲሰሩ መገፋፋት ይኖራል። ስለዚህ ቅድሚያ የምንሰጠው ለተጫዋቾቹ ነው። የግድ አንዱን ማንሳት አስፈላጊ መሆኑን በግምገማ ሪፖርት መነሻነት ነው አሰልጣኝ ቴዎድሮስ ሊነሳ የቻለው።