ቅድመ ዳሰሳ | ጅማ አባ ጅፋር ከ ፋሲል ከነማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የ18ኛው ሳምንት ሦስተኛ የጨዋታ ቀን የመክፈቻ ፍልሚያ አስመልክቶ ተከታዩን ዳሰሳ አዘጋጅተናል።

በሰንጠረዡ የላይ እና የታች ፉክክር ውስጥ ለሚገኙት ጅማ እና ፋሲል የነገው ጨዋታ ውጤት ከፍ ያለ ትርጉም ይኖረዋል። በወራጅ ቀጠናው ውስጥ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር የደረጃ ለውጥ ባያስገኝለትም ከበላዩ ካለው ድሬዳዋ ጋር ያለውን ልዩነት ወደ ሁለት ዝቅ ማድረግ ይችላል። የአምናዎቹ ቻምፒዮኖች ከመጨረሻ አምስት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ማሸነፋቸውን ተከትሎ ከመሪው ጋር ያላቸው ልዩነት 13 በመድረሱ (የወልቂጤው ሽንፈት ለጊዜው አለመፅደቁ እንዳለ ሆኖ) ጨርሰው ከፍልሚያው እንዳይርቁ ሙሉ ነጥብ የግድ ያስፈልጋቸዋል።

ልባቸው ለኳስ ቁጥጥር ብልጫ ከሚያደሉ ቡድኖች ውስጥ የሚካተቱት ሁለቱ ተጋጣሚዎች በቅርብ ጨዋታዎች ከኳስ ምስረታ ሂደታቸው የሚፈልጉትን ያህል የግብ ዕድል እያገኙ ነው ማለት አይቻልም። በመዋቅር ደረጃ ጥሩ መስተካከል እያሳየ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር የኳስ ፍሰቱ በቅብብል ስኬት ታጅቦ ወደ ሳጥን የሚደርስበት ፍጥነት ዝግ ማለት ለተጋጣሚዎች የመደራጀት ጊዜ ሲሰጥ ይታያል። በፋሲል ከነማ በኩልም ከዚህ ቀደም በማጥቃቱ ላይ ከፍ ያለ ተሳትፎ የነበራቸው የመስመር ተከላካዮች እና የመስመር አማካዮች በተለይም በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት መቀነሱ በአጥቂ እና በአማካዮች መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ መካከለኛ ርቀት ያላቸው ተሻጋሪ ኳሶች ላይ ተመርኩዞ እንዲደበዝዝ ያደረገው ይመስላል።

ከአጨዋወት አንፃር የነገው ጨዋታ የመሀል ሜዳ ፍልሚያ ሊወስነው የሚችል በመሆኑ ቡድኖቹ ከላይ በተነሱት ሀሳቦች ላይ መሻሻሎች ያስፈልጓቸዋል። ይህንን ለማድረግ የሚያስችሉ ጠንካራ ነገሮችም በሁለቱም በኩል አይታጡም። ጅማዎች አስጨናቂ ፀጋዬ ከተከላካዮች ፊት ለቡድኑ የጨመረውን ጥንካሬ ተከትሎ የዳዊት እና መስዑድ ጥምረት አድናን ረሻድም ተጨምሮበት ሳጥን ውስጥ በቁጥር በርከት ብሎ የመገኘት ምልክት ሰጥቷል። ይህንን ለነገ አሳድጎ መምጣት እና የመስመር ተመላላሾቹ የማጥቃት ኃይል የተጋጣሚን የኮሪደር እንቅስቃሴ አፍኖ በጥልቀት ማጥቃቱን እንዲያግዝ ማድረግ ለጅማዎች እጅግ ወሳኝ ይሆናል። ባለፉት ጨዋታዎች የተጋጣሚያቸው የኋላ መስመር ተሰላፊዎች ግለሰባዊ ስህተቶች መበራከትም ፈጣን ቅብብሎች ከተሳኩላቸው የነመሐመኑርን ፍጥነት ያማካሉ ኳሶችን ማድረስ ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው ይችላል።

በፋሲል ከነማ በኩል የቡድኑ የኳስ ፍሰት በተጨዋቾች ታታሪነት በሚታጀብ ቀጥተኝነት እየተቀየጠ ተጋጣሚን የሚያስጨንቅበት አኳኋን ቀንሶ ይስተዋላል። ፋሲል ነገ ከአሰልጣኝ ስዩም ጋር ከተለያየ በኋላ የመጀመሪያ ጨዋታውን ማድረጉ በለውጦች ወቅት በቡድኖች ላይ የሚፈጠረው የድል ርሀብ ፋሲልን በዚህ ረገድ ተጠቃሚ ሊያደርገው ይችላል። ይህ የስሜት ግለት ከተፈጠረ የቡድኑን የማጥቃት ሽግግር ወደቀደመ አስፈሪነቱ ከመመለስ ባለፈ የጅማ አባ ጅፋርን ቅብብሎች በአደገኛ ቦታዎች ላይ በማቋረጥ የሚኖረውንም ስኬት ሊጨምረው እንደሚችል መረሳት የለበትም። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ ከፊት እስካሁን በአግባቡ ሊያዋህደው ያልቻለውን የሙጂብ እና ኦኪኪ ፎርሙላ ካገኘ የጅማ የቅርብ ጊዜ ጨዋታዎች ጠንካራ ጎን የሆነው አላዛር ማርቆስን የመፈተን አቅሙ ይኖረዋል።

በጅማ አባ ጅፋር በኩል የተሰማ የጉዳትም ሆነ የቅጣት ዜና የሌለ ሲሆን ከ14ኛው ሳምንት በኋላ ከድር ኩሊባሊን ከጉዳት መልስ በሚያገኘው ፋሲል ከነማ በኩል ግን ሱራፌል ዳኛቸው ከመጠነኛ ጉዳት ቢመለስም ነገ ለሙሉ ለጨዋታው ብቁ መሆኑ እርግጥ አልሆነም።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ቡድኖቹ በሊጉ ከተገናኙባቸው ሰባት ጨዋታዎች ውስጥ አምስቱ በፋሲል አሸናፊነት ሲጠናቀቁ በቀሪዎቹ ሁለቱ የአቻ ውጤቶች ተመዝግበዋል። በጨዋታዎቹ ፋሲል 17 ፤ ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ 2 ግቦች አሏቸው።

ግምታዊ አሰላለፍ

ጅማ አባ ጅፋር (3-6-1)

አላዛር ማርቆስ

ኢያሱ ለገሠ – የአብስራ ሙሉጌታ – ወንድማገኝ ማርቆስ

ቦና ዓሊ – አድናን ረሻድ – ዳዊት እስጢፋኖስ – አስጨናቂ ፀጋዬ – መስዑድ መሐመድ – እዮብ አለማየሁ

መሐመድኑር ናስር

ፋሲል ከነማ (4-1-3-2)

ሚኬል ሳማኪ

ዓለምብርሃን ይግዛው – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን

ሀብታሙ ተከስተ

ሽመክት ጉግሳ – በዛብህ መለዮ – በረከት ደስታ

ሙጂብ ቃሲም – ኦኪኪ አፎላቢ