[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ከሳምንቱ ተጠባቂ መርሐ-ግብሮች መካከል ቀዳሚ የሆነውን ፍልሚያ እንደሚከተለው ቃኝተነዋል።
በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚገኙት ሲዳማ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ ነገ አመሻሽ 12 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ሜዳ የሚያደርጉት ጨዋታ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል። በተለይ ቡድኖቹ መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ የነጥብ ልዩነቱን እያሰፋ ስለሆነ ከፉክክሩ ላለመራቅ ጠንክረው እንደሚጫወቱ ይታመናል። ሲዳማ ቡና ደግሞ ካለፉት ሁለት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው ስድስት ነጥብ አራቱን በመጣሉ ሀይሉን አሟጦ እንደሚንቀሳቀስ ሲገመት ሀዋሳ ከተማም ከአቻ መልስ ዳግም ድል ለማስመዝገብ በማሰብ ብርቱ ትግል ማድረጉ የማይቀር ነው።
የአሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ቡድን ባሳለፍነው ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር አቻ ሲለያይ በተጋጣሚ ቡድን የነበረውን የመከላከል አደረጃጀት አስከፍቶ መግባት ተስኖት ነበር። እርግጥ በክፍት ጨዋታዎች አንዳንድ አጋጣሚዎችን ቢፈጥርም ኳስ እና መረብን ለማገናኘት የሚያስችል ሙከራዎችን በወጥነት በሁለቱ አጋማሾች ሲያደርግ አልታየም። በዋናነትም በቁጥር በዝቶ ሲከላከል የነበረውን የድሬ አደረጃጀት ዘርዘር አድርጎ ተጫዋቾቹ ወደ ፊት እንዲገቡ የሚያስችል ስልት ጠፍቶት ታይቷል። በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አዲሱ ፈራሚያቸው ሳልዓዲን ሰዒድ በግሉ ጥረቶችን ቢያደርግም እሱም ኳስ እና መረብን ማገናኘት አልቻለም። በነገው ጨዋታም ጠንካራ የኋላ መስመር ካላቸው ክለቦች መካከል አንዱን ስለሚገጥም ጎል ፊት ሁነኛ መላ ያስፈልገዋል። በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት እየተፎካከረ የሚገኘው ይገዙ ቦጋለም ለመጨረሻ ጊዜ ለቡድኑ ግብ ያስገኘው ከ528 ደቂቃዎች በፊት ነበር። የሆነው ሆኖ ኳሱን ለቆ እንደሚጫወት የሚገመተውን የሀዋሳ የተደራጀ የኋላ መስመር ለማስከፈት ከአጥቂዎቹ በተጨማሪም የአጥቂ አማካዮቹ ፍሬው እና ዳዊት ከኳስ ጋር እና ውጪ ወደ ሳጥን የሚደረግ ሩጫ ወሳኝ ነው።
የሲዳማ ቡና ትልቁ የነገ ስጋት ሽግግሮች ናቸው። በተለይ ሀዋሳ ከተማ መገለጫው የሆነው ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚደረግ ሽግግር ለሲዳማ ፈታኝ መሆኑ አይቀሬ ነው። በዚህ ሂደት ፈጣኖቹ የወገብ በላይ ተጫዋቾችን መቆጣጠር በሲዳማ በኩል ያለ የጨዋታው ትልቁን ድርሻ የሚወስድ ጉዳይ ይመስላል። ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጠል ከአዳማ ከተማ ጋር በጣምራ ጥቂት ጨዋታዎችን (2) የተረታው ሲዳማ ቡና ነገም በጥሩ ግስጋሴ ላይ በሚገኘው እና እንደተቀመጠበት ደረጃ ሦስተኛ ብዙ ግብ ያስቆጠረ ክለብ በሆነው ሀዋሳ የሚሰነዘርበትን ጫና ማምከኛ ይዞ መቅረብ ይጠበቅበታል።
ካለፉት 11 ጨዋታዎች አንዱን ብቻ የተረታው ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ ባሳለፍነው ሳምንት ከቀጥተኛ የዋንጫ ተፎካካሪው ወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ነገ ደግሞ ሌላኛውን ተፎካካሪ ለመግጠም እየተዘጋጀ ይገኛል። በድቻው ጨዋታ ሁለት መልክ ይዞ የታየው የአሠልጣኝ ዘርዓይ ቡድን በመጀመሪያው አጋማሽ ከኳስ ጋር ለማሳለፍ ፍላጎት ያለው በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ለመከላከል ቅድሚያ የሰጠ ሆኖ ነበር። ከሁሉም በላይ ደግሞ ለ60 ደቂቃዎች ገደማ የግብ ብልጫ ይዞ እየመራ ይባስ የድቻ ተጫዋች በቀይ ካርድ ወጥቶ በእጁ የገባውን ሦስት ነጥብ ባለቀ ሰዓት ማጣቱ የሚያስቆጨው ይመስላል። ከዚህ መነሻነት በነገው ጨዋታ በሙሉ ሀይሉ ከሦስት ነጥብ ጋር ለመገናኘት እንደሚጥር ይገመታል። ለዚህ ደግሞ የቡድኑን 77% ጎሎችን ያስቆጠሩት ብሩክ፣ መስፍን፣ ኤፍሬም እና ወንድማገኝ ለሲዳማ ተጫዋቾች የራስ ምታት መሆናቸው ቢገመትም የወንድማገኝ በቅጣት አለመኖር ግን መጠነኛ መሳሳት በፈጠራው በኩል ሊያመጣ ይችላል። ይህ ቢሆንም ግን ሦስቱ አጥቂዎች የተጋጣሚ ቡድን ወደ መከላከል ቅርፅ በተደራጀ ሁኔታ ሳይቀየር ፍጥነታቸውን ተጠቅመው የሚያደርጉት የግብ ሙከራ ምናልባት የሀዋሳ የጎል ምንጭ ሊሆን ይችላል።
አብዛኛውን ጊዜ ተመሳሳይ የተጫዋች ምርጫ በሁሉም የሜዳ ክፍሎች የሚያደርገው ሀዋሳ አራቱም የጨዋታ ምዕራፎች ላይ በቡድናዊ መዋቅር ሲንቀሳቀስ ይታያል። ከዚህ ውጪም የተጫዋቾቹ የተነሳሽነት መንፈስም ከፍ ያለ ይመስላል። በነገው ጨዋታ ደግሞ ይህ አይሎ ከመጣ በቀላሉ እጅ እንደማይሰጡ መናገር ይቻላል። በጨዋታው ግን በተወሰነ መልኩ ኳሱን ለሲዳማ ሰጥተው ከላይ እንደገለፅነው ወሳኝ ቅፅበቶችን እየጠበቁ ጥቃት መሰንዘርን ተቀዳሚ ዕቅዳቸው አድርገው ወደ ሜዳ ሊገቡ ይችላሉ።
የጉዳት እና ቅጣት ዜናን በተመለከተ ሲዳማ ቡና በሁለቱም የሚያጣው ተጫዋች የሌለ ሲሆን በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ መጠነኛ ጉዳት ገጥሞት ድሬዳዋን በገጠመው ስብስብ ውስጥ ያልነበረው አማካዩ ሙሉዓለም መስፍን ከጉዳቱ አገግሞ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆኑ ተመላክቷል። ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ የአጥቂ አማካዩ ወንድማገኝ ኃይሉን በአምስት ቢጫ ምክንያት የማያገኝ ሲሆን የጉዳት ዜና ግን አለመኖሩም ተሰምቷል።
ተጠባቂው ጨዋታ በለሚ ንጉሴ አልቢትርነት የሚመራ ሲሆን ሸዋንግዛው ተባበል እና ሙልነህ በዳዳ የመስመር ዮናስ ካሣሁን ደግሞ አራተኛ ዳኛ በመሆን እርዳታ እንደሚሰጡ ታውቋል።
እርስ በርስ ግንኙነት
– 23 ጊዜ ከዚህ ቀደም የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች ተቀራራቢ የመሸናነፍ ታሪክ አላቸው። በዚህም ሲዳማ ቡና ስምንት ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ሰባት ጊዜ ሲያሸንፉ ቀሪው ስምንት ግንኙነት በበኩሉ በአቻ ውጤት ተፈፅሟል።
– በእነዚህ 23 ግንኙነቶች በድምሩ 51 ኳሶች መረብ ላይ ሲያርፉ ሲዳማ 27 ቀሪውን 24 ደግሞ ሀዋሳ አስቆጥቷል።
ግምታዊ አሠላለፍ
ሲዳማ ቡና (4-1-3-2)
ተክለማርያም ሻንቆ
ደግፌ ዓለሙ – ጊት ጋትኩት – ያኩቡ መሐመድ – መሐሪ መና
ሙሉዓለም መስፍን
ዳዊት ተፈራ – ፍሬው ሰለሞን – ሀብታሙ ገዛኸኝ
ይገዙ ቦጋለ – ሳልዓዲን ሰዒድ
ሀዋሳ ከተማ (3-4-3)
ዳግም ተፈራ
አዲስዓለም ተስፋዬ – ላውረንስ ላርቴ – ፀጋሰው ድማሙ
ዳንኤል ደርቤ – አብዱልባሲጥ ከማል – በቃሉ ገነነ – መድሃኔ ብርሃኔ
ኤፍሬም አሻሞ – ብሩክ በየነ – መስፍን ታፈሰ