[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በቀጠሉት የዛሬ የሊጉ ጨዋታዎች መሪው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነጥብ ሲጥል ተከታዩ ሀዋሳ ከተማ ድል ቀንቶታል።
በቶማስ ቦጋለ
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቦሌ ክፍለ ከተማ ነጥብ ተጋርቷል
ረፋድ ላይ በተደረገው ጨዋታ ቦሌ ክፍለከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲያሸንፍ ከነበረው አሰላለፍ የ 3 ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርግ ትግስት ሙሉዓለም ፣ መአዛ አብደላ እና ሂሩት ተስፋዬን በስንታየሁ ሒርኮ ፣ ሲፈን ተስፋዬ እና ይዲዲያ አሜ ቀይሯል። ንግድ ባንኮች ባንፃሩ ከጌዴኦ ዲላ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ የ 7 ተጫዋቾች ቅያሪ ሲያደርጉ ሂሩት ተስፋዬ ፣ ንግስት መዓዛ ፣ ትግስት ኃይሌ ፣ ጥሩአንቺ መንገሻ ፣ ሕይወት ደንጊሶ ፣ የምሥራች ላቀው እና ፀጋነሽ ወርናን በታሪኳ በርገና ፣ ትዝታ ኃ/ሚካኤል ፣ ብዙዓየሁ ታደሠ እመቤት አዲሱ ፣ እፀገነት ብዙነህ ፣ ትግስት ያደታ እና ዮርዳኖስ ምዑዝ ተተክተዋል።
በመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ተጭነው መጫወት የጀመሩት ቦሌዎች 3ኛ ደቂቃ ላይ ንግስት በቀለ ባስቆጠረችው ድንቅ የቅጣት ምት ጎል በጊዜ መሪ መሆን ችለዋል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በመስመር ጨዋታ የግብ ዕድል መፍጠር አስበው ሲጫወቱ የነበሩት ባንኮች ሰናይት ቦጋለ ከሎዛ አበራ የተቀበለችውን ኳስ ወደ ጎል ብትሞክርም የግቡ አግዳሚ መልሶባቸዋል። በተደጋጋሚ በሎዛ አረጋሽ እና እፀገነት የግብ ዕድል መፍጠር የጀመሩት ባንኮች ተሳክቶላቸው 17ኛው ደቂቃ ላይ እፀገነት ከሰናይት የተቀበለችውን ኳስ አስቆጥራ ቡድኗን አቻ አድርጋለች። በተደጋጋሚ አጥቅተው መጫወት የቀጠሉት ባንኮች በፈጠሩት ሌላ ዕድል አረጋሽ የሞከረችው ኳስ በግቡ አግዳሚ ታኮ ወጥቶባታል። 33ኛው ደቂቃ ላይ በተፈጠረ ሌላ የግብ ዕድል ደግሞ የባንኳ ዮርዳኖስ ሙዓዝ ከትዕግሥት ያደታ የተቀበለችውን ኳስ አገባች ሲባል ትልቅ ዕድል አምክናለች።
ከረፍት መልስ ተሽለው የገቡት ንግድ ባንኮች 52ኛው ደቂቃ ላይ ሎዛ አበራ ከሰናይት የተቀበለችውን ኳስ ወደ ግብ በመቀየሯ መሪ መሆን ችለዋል። በጨዋታው ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው የባንኳ አረጋሽ ከቅጣት ምት ወደጎል የሞከረችውና በግቡ አግዳሚ የተመለሰው ኳስም ለቡድኑ የሚያስቆጭ ነበር። የማጥቃት አማራጫቸውን ወደ ንግስት ኳስ በመጣል ያደረጉት ቦሌዎች 61ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ ዕድል አግኝተው ነበር። ንግስት በቀለ ከጤናዬ የተቀበለችውን ኳስ የመስመር ዳኛዋ ምንም ባላለችበት ከጨዋታ ውጪ ነኝ ብላ በማሰብ እና ዘግይታም ለማግባት በመሞከር ቦሌዎች ወደ ጨዋታ ሊመለሱ የሚችሉበትን ወርቃማ ዕድል አምክናለች። ባንኮችም ከ አረጋሽ በሚሻማ ኳስ ተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።
88ኛው ደቂቃ ላይ የባንኳ ፎዝያ ከሎዛ አበራ የተቀበለችውን ኳስ ብታስቆጥርም ኳስ በእጅሽ ነክተሻል በሚል ተሽሮባታል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጭማሪ ደቂቃዎች ሲቀሩ የቦሌዋ ንግስት በቀለ ሌላ ግሩም የቅጣት ምት አስቆጥራ ቦሌን አቻ አድርጋለች። በጭማሪ ደቂቃዎች ግብ ለማግኘት የሞከሩት ባንኮች ሰናይት ቦጋለ ከዓለምነሽ ገረመው የተቀበለችውን ኳስ ወደ ግብ ብትሞክርም የቦሌዋ ግብ ጠባቂ አድናባታለች ፤ ይሄም የጨዋታው የመጨረሻ ትዕይንት ሆኖ ጨዋታው 2-2 ተጠናቋል።
በውጤቱም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነጥቡን 20 በማድረስ መሪነቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።
በአዝናኙ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ አዲስ አበባን 4-3 አሸንፏል
በ7ኛው ሳምንት አራፊ የነበረው ሐዋሳ በ6ኛ ሳምንት አዳማን በመሠሉ አበራ የራስ ላይ ግብ አንድ ለምንም ካሸነፈበት አሰላለፍ የ 3 ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርግ ብዙኃን እንዳለ ፣ ሲሣይ ገ/ዋህድ እና እሙሽ ዳንኤልን በፀሐይነሽ ጅላ ፣ ቅድስት ቴቃ እና ሣራ ነብሶ ተክቷል። በአዲስ አበባ በኩል በ7ኛ ሳምንት አዳማን በአርያት ኦዶንግ ብቸኛ ግብ አንድ ለምንም ካሸነፉበት ስብስባቸው የአንድ ተጫዋች ለውጥ ሲያደርጉ ንግሥት ኃይሉ ኤልሣቤጥ ብርሀኑን ተክታ ገብታለች።
ሐዋሳዎች የሚይዙትን ኳስ ወደ ቱሪስት ለማ በመላክ ጎል ለመፍጠር በመሞከር ጨዋታውን ጀምረውታል። 9ኛው ደቂቃ ላይ ቱሪስት ለማ ከ ከግራ መስመር ቅድስት ዘለቀ የተቀበለችውን ኳስ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥራ ቡድኗን መሪ አድርጋለች። ተጭነው መጫወት የቀጠሉት ሐዋሳዎች 18ኛው ደቂቃ ላይ ሣራ ነብሶ ከቱሪስት ለማ የተሻማላትን ኳስ በግንባር ገጭታ በማስቆጠር ልዩነቱን ሁለት አድርጋለች። አዲስአበባ ከተማዎች የመጀመሪያ ሙከራ ለማድረግ 32 ደቂቃ የፈጀባቸው ሲሆን ይሄውም በቤተልሔም ሰማኸኝ የተሞከረና በጎሉ አናት የወጣ ኳስ ነበር። የመጀመሪያ አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊት ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ተጭነው የተጫወቱት ሐዋሳዎች በምሕረት መለሰ ፣ ሣራ ነብሶ እና ቱሪስት ለማ ሙከራዎች ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።
ከዕረፍት መልስ አጥቅተው ለመጫወት ያሰቡት አዲስ አበባ ከተማዎች አርያት ኦዶንግን በቤተልሔም ሰማኸኝ ቀይረው አስገብተዋል። 48ኛው ደቂቃ ላይ የሐዋሳዋ ቱርሲት ለማ ጥሩ የግብ ማግባት ሙከራ ብታደርግም የግቡ የግራ ቋሚ መልሶባታል። 51ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ የገባችው አርያት ኦዶንግ ራሷ ላይ በተሠራ ጥፋት የተሰጠውን ፍጹም ቅጣት ምት አስቆጥራ ውጤቱን ለማጥበብ እና ቡድኗን ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥሩ አስተዋጽኦ አድርጋለች። 58ኛው ደቂቃ ላይ የሐዋሳዋ መንደሪን ክንድይሁን ከረጅም ርቀት የቅጣት ምት የግብ ጠባቂዋ ስህተት ተጨምሮበት አስቆጥራ ውጤቱን 3-1 በማድረስ ጫናውን መቀነስ ችላለች። ለተመልካች አዝናኝ በነበረው እና ነፋሻማ ዓየር የነበረት የመጨረሻ 30 ደቂቃ ብርቱ ፉክክር የታየበት ነበር።
በዚህም 78ኛው ደቂቃ ላይ ቱሪስት ለማ ከቅድስት ዘለቀ የተሻማውን የማዕዘን ኳስ በግንባሯ አስቆጥራ ጨዋታውን 4-1 እንዲሆን ስታስችል ተስፋ ባለመቁረጥ ሲታገሉ የነበሩት አዲስ አበባ ከተማዎች 85ኛው ደቂቃ ላይ ኳስ በእጅ በመነካቱ የተገኘውን የጨዋታው ሁለተኛ ፍፁም ቅጣት ምት በአርያት ኦዶንግ አስቆጥረዋል። 89ኛው ደቂቃ ላይ አርያት ኦዶንግ ከ ዘይነባ ሰይድ በመሀል የተሰነጠቀላትን ኳስ ተጠቅማ ሐዋሳዎችን ጫና ውስጥ ያስገባች ሌላ ጎል አክላ ቅያሪው ሙሉ በሙሉ ስኬታማ እንደነበር አረጋግጣለች። ቢሆንም 3ኛ ግቧን ባስቆጠረችበት ሰዓት ከግብ ጠባቂዋ ጋር ተጋጭታ ክፉኛ ተጎድታ መውጣቷ አዲስ አበባዎች ላይ ውሀ የቸለሰ ሁኔታ ተፈጥሯል።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ከጨዋታው ነጥብ ይዘው ለመውጣት የታገሉት አዲስ አበባዎቹ ሳይሳካላቸው ቀርቶ ጨዋታው 4-3 በሆነ ውጤት ተጠናቋል። በዚህም ሐዋሳ ከንግድ ባንክ ጋር ያለውን ልዩነት ወደ 1 አጥብቦ ባለበት 2ኛ ደረጃ ፤ አዲስ አበባዎችም ባሉበት 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
አዳማ ከመመራት ተነስቶ ጊዮጊስን በሰፊ ልዩነት አሸንፏል
በአዳማ በኩል በ 7ኛ ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ በአርያት ኦዶንግ ብቸኛ ግብ ከተሸነፉበት ስብስብ የ ሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ኤደን ሽፈራው ፣ ዝናሽ መንክር እና ምርቃት ፈለቀ በሣምራዊት ኃይሉ ፣ ሠሚራ ከማል እና ሔለን እሸቱ ተተክተዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ በቦሌ ክፍለ ከተማ 2-1 ከተሸነፉበት ስብስብ የአንድ ተጫዋች ብቻ ለውጥ ሲኖር ዳግማዊት ሰለሞን ገብርኤላ አበበን ተክታ ገብታለች።
ደመናማ የዓየር ንብረት የነበረበት ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል ጥሩ ፉክክር የታየበት ነበር። አዳማዎች በቀኝ በኩል ከሔለን እሸቱ በሚነሱ ኳሶች የማጥቃት ፍላጎት ይዘው ሲገቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኳስ መስርቶ በመውጣት በቤተልሔም መንተሎ እና ፍቅርአዲስ ገዛኸኝ ቶሎ ቶሎ ወደግብ በመድረስ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክር ታይቷል። ጨዋታው በጀመረ 10ኛው ደቂቃ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊሷ ቤተልሔም መንተሎ ከግራ መስመር ብዙ ተጫዋቾችን አታልላ በማለፍ ግሩም ግብ አስቆጥራ ፈረሰኞችን መሪ ማድረግ ችላለች። ከጎሏ መቆጠር በኋላ በጣም ተጭነው የተጫወቱት አዳማዎች በሔለን እሸቱ እና መሠሉ አበራ የግብ ሙከራዎችን ቢያደርጉም የቅዱስ ጊዮርጊሷ ግብ ጠባቂ ጽዮን ተፈራ ተይዞባቸዋል።
ነገር ግን 32ኛው ደቂቃ ላይ ሔለን እሸቱ አዳማዎችን አቻ የሚያደርግ ግብ አስቆጥራ የቡድን አባሎቿን አነቃቅታለች። ከ 5 ደቂቃዎች በኋላ 37ኛው ደቂቃ ላይ ትግስት ዘውዴ ወደ ጎል የሞከረችውን ኳስ ግብ ጠባቂዋ ስትመልሰው ጎል ለማስቆጠር ምቹ አጋጣሚ ያገኘቸው ሔለን እሸቱ አዳማን መሪ አድርጋለች። የመጀመሪያው አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊት ግብ ለማስቆጠር አጥቅተው የተጫወቱት ፈረሰኞቹ በቤተልሔም መንተሎ ጥሩ ሙከራ ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ቀዝቀዝ ያለ ፉክክር የታየበት ክፍለጊዜ ሲሆን ብዙ ሙከራም አልተመለከትንም። 55ኛው ደቂቃ ላይ መሠሉ አበራ የመታችውን ቅጣት ምት በእጅ ተነክቷል በሚል የተሰጠውን ፍጹም ቅጣት ምት ሔለን እሸቱ አስቆጥራ ሐት-ትሪክ ሰርታለች። ከግቧ መቆጠር በኋላ በቀኝ መስመር በፍቅርአዲስ ገዛኸኝ የኳስ ፍሰቱን ያስቀጠሉት ፈረሰኞቹ በቤተልሔም መንተሎ እና በፍቅርአዲስ የተወሰኑ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ውጤታማ አልነበሩም።
67ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ ከገባችው ፀባኦት መሀመድ የተሻገረላትን ኳስ ሰርካዲስ ጉታ አስቆጥራ አዳማ በሰፊ የግብ ልዩነት እንዲመራ አስችላለች። ኳሱን አመቻችታ ያቀበለችው ፀባኦት ግን ጉዳት አስተናግዳ ከሜዳ ለመውጣት ተገዳለች። ጨዋታው ከመጠናቀቁ በፊት የፈረሰኞቹ ቤተልሔም መንተሎ እና ፍቅርአዲስ ገዛኸኝ የግብ ዕድል ለመፍጠር ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ቀርቶ ጨዋታው በአዳማ 4-1 አሸናፊት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎም አዳማ ከተማ ከመከላከያ ጋር በዕኩል ነጥብ የግብ ክፍያ በልጦ ደረጃውን ወደ 5ኛ ከፍ ሲያደርግ ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ደረጃ ወርዶ 10 ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።