ፌዴሬሽኑ የወልቂጤ ከተማ እና ፋሲል ከነማን ጨዋታ አስመልክቶ የሊግ ካምፓኒው በጠየቀው ማብራርያ ዙርያ ምላሽ ሰጥቷል።
በ17ኛ ሳምንት ወልቂጤ ከተማ ከወቅቱን ከፋሲል ከነማ ያገኘው ጨዋታ ምንም እንኳን በወልቂጤ ከተማ አሸናፊነት ቢጠናቀቅም ከጨዋታው አስቀድሞ ዐፄዎቹ የተጫዋችነት ተገቢነት ክስ ማሳይዛቸው ይታወቃል። የሊግ ካምፓኒው የውድድርና ሥነስርዓት ኮሚቴ በቀረበው ክስ መሠረት ውጤቱ ለጊዜው እንዳይፀድቅና ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ማብራሪያ እንዲሰጠው ውሳኔ አሳልፏል። ይህን ተከትሎ የሊግ ካምፓኒው በትናትናው ዕለት በይፋ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ደብዳቤ በማስገባት ጥያቄውን ያቀረበ ሲሆን ፌዴሬሽኑም በዛሬው ዕለት ምላሹን ለሊግ ካምፓኒው በደብዳቤ አሳውቋል።
ለፋሲል ከነማ ክስ መነሻ የነበረው ወልቂጤ ከተማ በተጫዋቾች ዝውውር ላይ እንዳይሳተፍ ዕግድ ተጥሎበት ባለበት ሰዓት አዳዲስ ተጫዋቾች አስፈርሞ አጫውቷል የሚል ነበር። ሆኖም ፌዴሬሽኑ ለሊጉ አክሲዮን ማኅበር በሰጠው ማብራሪያ መሰረት የተፈፀሙት ዝውውሮች ህጋዊ አካሄድን የጠበቁ መሆናቸውን በማረጋገጥ የፋሲል ከነማን ክስ ውድቅ አድርጎታል።
በዚህ ውሳኔ መሰረትም ሳይፀድቅ ቆይቶ የነበረው ወልቂጤ ከተማ ፋሲል ከነማን 2-1 ያሸነፈበት የ17ኛ ሳምንት ጨዋታ ውጤት በአክሲዮን ማህበሩ እንደሚፀድቅ ይጠበቃል።