ከወራት በፊት ኢትዮጵያ ቡና ከክለቡ አሰናብቶት የቆየው ናትናኤል በርሄ ለፌዴሬሽኑ አቤቱታውን አሰምቷል።
ከዚህ ቀደም በነበረው ዘገባችን ኢትዮጵያ ቡና ካደረጋቸው ጨዋታዎች መካከል በአንዱ ጨዋታ አስቀድሞ በስፖርታዊ ውርርድ ኢትዮጵያ ቡና ይሸነፋል በማለት ተጫዋች ናትናኤል በርሔ በቡድን መሪው አማካኝነት ድርጊቱን ስለመፈፀሙ የሰነድ ማረጋገጫ መቅረቡ ክለቡ ካስቀመጠው የተጫዋቾች የሥነ ምግባር መመርያ ውጪ ዕምነት አጉድሏል በማለት ቀሪ ኮንትራት እያለው ክለቡ ተጫዋቹን ማሰናበቱ ይታወሳል።
ከዚህም ተጨማሪም ፌዴሬሽን የዲሲፒሊን መመርያ መሠረት ለሁለት ዓመት ከማንኛውም እግረኳሳዊ እንቅስቃሴ እንዲያግደው ክለቡ በደብዳቤ ጠይቆም ነበር።
ተጫዋች ናትናኤል በርሔም ድርጊቱን እንዳልፈፀመ እና ከክለቡ ጋር በመነጋገር መተማመን ላይ እንደደረሰ በመግለፅ ውሳኔውን እንደማይቀበል ለሶከር ኢትዮጵያ ሀሳቡን ገልፆ ነበር። ጉዳዩ ለሁለት ወር በዝምታ ከቆየ በኋላ ተጫዋች ናትናኤል የወሰነበት ውሳኔ ተነስቶለት ወደ ክለቡ እንዲመለስ ካልሆነም በስምምነት በመለያየት መልቀቂያ እንዲሰጠው ለክለቡ ጥያቄውን አቅርቧል።
ኢትዮጵያ ቡና በምላሹ ለፌዴሬሽኑ ያቀረበው ሀሳብ ምላሽ ካላገኘ ምንም ዓይነት ነገር ተግባራዊ እንደማያደርግ ገልፆለታል። በዚህ መነሻነት ያለፉትን ‘ከሁለት ወር በላይ ጊዜ ባላደረኩት ነገር ዕግድ ተጥሎብኝ ቆይቻለው ወደ ክለቤ ተመልሼ በቀሪው የውል ዘመኔ እስኪጠናቀቅ ድረስ እንዳገለግል እና ከታገድኩ ጀምሮ ያልተከፈለኝ ደመወዝ እንዲከፈለኝ ፌዴሬሽኑ ፍትህ እንዲሰጠኝ እጠይቃለው’ በማለት ተጫዋቹ ባለሁለት ገፅ የአቤቱታ ደብዳቤ አስገብቷል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ቡና ታህሳስ 19 ላይ ለተጨዋቹ ውሳኔውን በገለፀበት ደብዳቤ ላይ ጉዳዩ ተጫዋቹን ለሁለት ዓመት ከእግርኳስ እንቅስቃሴ እንደሚያሳግድ በመጠቆም ውሳኔ እንዲተላለፍበት ለፌዴሬሽኑ በግልባጭ አሳውቋል። ሆኖም ፌዴሬሽኑ ጉዳዩን ምን እንዳደረሰው ለማጣረት ባደረግነው ጥረት እስካሁን ድረስ ጉዳዩ ወደ ዲስፕሊን ኮሚቴ ተመርቶ እየታየ መሆኑን ለማወቅ ችለናል።