ሪፖርት | የኦኪኪ የጭማሪ ደቂቃ ጎል ፋሲልን ባለድል አድርጋለች

ብርቱ ፉክክር በተደረገበት የዛሬው ቅዳሚ ጨዋታ ፋሲል ከነማ ጅማ አባ ጅፋርን ከመመራት ተነስቶ 2-1 አሸንፏል።

ካሳለፍነው ሳምንት ጨዋታዎች በተደረጉ የአሰላለፍ ለውጦች ጅማ አባ ጅፋር ኢያሱ ለገሰ እና ዳዊት እስጢፋኖስን በሙሳ ካበላ እና ሱራፌል ዐወል ሲተካ የፋሲል ከነማዎቹ ከድር ኩሊባሊ ፣ ይሁን እንዳሻው እና ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ በአስቻለው ታመነ ፣ ሀብታሙ ተከስተ እና ሱራፌል ዳኛቸው ቦታ ተተክተዋል።

በጥሩ ፉክክር በጀመረው ጨዋታ ኳስ መስርተው ለመውጣት ጥረት ከጀመሩት ተጋጣሚዎች ውስጥ ፋሲል የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ይዞ ታይቷል። ሆኖም በመጀመሪያዎቹ 12 ደቂቃዎች የቡድኑ ማጥቅት በሦስት አጋጣሚዎች ለበረከት ደስታ የግብ ዕድሎችን ሲፈጥር ከተከላካይ ጀርባ የሚጣሉ ኳሶች መነሻ ነበሩ።

በአድናን ረሻድ እና ሱራፌል ዐወል የርቀት ሙከራዎች ያደረጉት ጅማዎች ቀስ በቀስ የኳስ ቁጥጥር ድርሻቸውን እያሳደጉ ሲሄዱ ቀድሚ ሙካራቸው 22ኛው ደቂቃ ላይ መስዑድ መሀመድ የሱራፌል ዐወልን የማዕዝን ምት በአጭሩ ጀምሮ ከማዕዘን በቀጥታ ወደ ግብ የላካው እና በግቡ ቋሚ የተመለሰው ኳስ ነበር። ቀጥተኛ ኳሶችን ወደ ግብ ማድረስ ባዘወተሩት ፋሲሎች በኩል 25ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ ከኋላ ከተጣለ ኳስ በረከት ደስታ በቀኝ በኩል ገብቶ ያደረገው እና በአላዛር ማርቆስ የተመለሰው ሙከራ ይጠቀሳል ።

ከውሃ ዕረፍቱ በኋላ በሙከራዎች ቀዝቀዝ ብሎ በቀጠለው ጨዋታ ጅማዎች በኳስ ቁጥጥሩ የተሻለ ትዕግስት እያሳዩ ሲቀጥሉ ፋሲሎች ከሳጥን ውጪ በሚደረጉ ሙከራዎች ተገድበው ቆይተዋል። የጅማዎች የኳስ ፍሰት ቀጥሎ 39ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ ንክኪዎች በተፈጠረ አጋጣሚ ጎል አስቆጥረዋል። ሱራፌል አወል ከሙሴ ካበላ የደረሰውን ኳስ ከግራ መስመር በግሩም ሁኔታ ሲልክለት መሐመድኑር ናስር በግንባር በመግጨት ጅማን ቀዳሚ አድርጓል።
ፋሲሎች በተመሳሳይ አኳኋን በረከት ከቀኝ ባሻገረው እና ሙጂብ በገጨው ኳስ ምላሽ ለመስጠት ቢሞክሩም ኢላማቸውን ሳይጠብቁ ቀርተዋል። 43ኛው ላይም ከዚሁ ከቀኝ አቅጣጫ ዓለምርሀን ይግዛው ያሻገረውን ኳስ በዛብህ መለዮ ከቅርብ ርቀት አምክኖታል።

ከዕረፍት መልስ ሱራፌል ዳኛቸው እና ኦኪኪ አፎላቢን ቀይረው ያስገቡት ፋሲሎች በተለየ የማጥቃት መንፈስ ተመልሰዋል። ከጅምሩ ወደ ጅማ አጋማሽ በጥልቀት ገብተው ጥቃቶችን መስንዘር ሲጀምሩ 50ኛው ደቂቃ ላይ የግቡን ጣራ ታኮ በወጣው የአምሳሉ ጥላሁን የቅጣት ምት ሙከራቸውን ጀምረዋል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በቅብብሎች ሳጥን ውስጥ የገቡት ፋሲሎች አጋጣሚው ወደ ሙከራነት ሳይቀየርላቸው ቀርቶ በረከት ደስታ ወደ ሳጥን እየመጣ ለነበረው ይሁን እንዳሻው ያመቻቸለትን ይሁን በአስደናቂ የሳጥን ውጪ ምት ጎል አድርጎታል።

ቀጣዮቹ ደቂቃዎች የጅማውን ግብ ጠባቂ አላዛር ማርቆስን ብቃት ያሳዩ ነበሩ። ባላባራው የፋሲል ጥቃት 58ኛው ደቂቃ ላይ ከይሁን ከጥልቅ የተነሳው ኳስ ሽመክት ከተከላካዮች ጀርባ ገብቶ ወደ ግብ ሲመታው እንዲሁም ሱራፌል ዳኛቸው ከአንድ ደቂቃ በኋላ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ የመታው ሌላ አደገኛ ኳስ በአላዛር አስገራሚ ቅልጥፍና ግብ ከመሆን ድነዋል። ከዚህ በኋላ ዳዊት እስጢፋኖስን ቀይረው ያስገቡት ጅማዎች ወደራሳቸው የተመለሱ ሲሆን ከሱራፌል ዐወል አቅጣጫ ጥቃቶችን መሰንዘር ጀምረዋል። ፋሲሎችም ቢሆኑ ጥቃታቸው እንዳልቆመ 68ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳኛቸው ከቀኝ ባሻማው እና ኦኪኪ በግንባር ሞክሮ በሳተው ኳስ አሳይተዋል።


የጅማን የኳስ ቁጥጥር ማንሰራራት ተከትሎ ፋሲሎች ከኋላ ጥሩ ክፍተት ማግኘት ጀምረዋል። በተለይ 76ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል የሰነጠቀው ኳስ በረከት ደስታን ከዓላዛር ጋር ቢያገናኘውም አስጨናቂ ፀጋዬ ደርሶ በአስገራሚ ሁኔታ ያመከነበት አጋጣሚ አስገራሚ ነበር። ከዚህም በላይ ግን 80ኛው ላይ ከዳዊት እስጢፋኖስ ከግራ የተነሳው ኳስ የሳማኬ እና ያሬድ አለመግባባት የታከለበት ኳስ ለጅማ ያለቀለት ዕድል ቢሰጥም እዮብ ዓለማየሁ ከቅርብ ርቀት አግኝቶ አምክኗል። 83ኛው ደቂቃ ላይ ሙሴ ካበላ ያሬድ ባየህ ላይ በሰራው ከባድ ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ የወጣበት አጋጣሚ የጨዋታው ቀጣይ ሁነት ሆኗል።

ከዚህም በኋላ ለፋሲል ጥቃት በተመሳሳይ በኳስ ንክኪዎች በታጀበ ጥቃት በቁጥር ቢያንሱም እንኳን ምላሽ ሲሰጡ የታዩት ጅማዎች በመከላከሉ የነበራቸው ትኩረት መቀነስ በመጨረሻ ዋጋ አስከፍሏቸዋል። በጭማሪ ደቂቃ ከመሀል ሱራፌል ባሻማው ኳስ ሁለቱ የፋሲል አጥቂዎ ያለጫና ሳጥን ውስጥ ሲገኙ ፍቃዱ ያመቻቸለትን ኦኪኪ አፎላቢ በቀድሞው ቡድኑ መረብ ላይ አሳርፎ ፋሲል ከነማን በመጨረሻ ሰዓት ባለድል አድርጓል።

በውጤቱ ፋሲል ከነማ ነጥቡን 30 በማድረስ ፤ ጅማ ደግሞ በነበረበት 12 ነጥብ ላይ በነበሩበት 4ኛ እና 15ኛ ደረጃ ላይ ረግተዋል።