ሪፖርት | በተጠባቂው ጨዋታ ሲዳማ ባለድል ሆኗል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በጨዋታ ሳምንቱ ተጠባቂ በነበረው የሮድዋ ደርቢ ሲዳማ ቡና ሀዋሳ ከተማን 3-1 በመርታት ከመሪዎቹ ያለውን ልዩነት አጥብቧል።

ሲዳማ ቡናዎች ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ያለ ግብ በአቻ ውጤት ከፈፀመው የመጀመሪያ ተሰላፊ ተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ ሁለት ለውጥ ያደረጉ ሲሆን በዚህም ብሩክ ሙሉጌታን እና ብርሃኑ አሻሞን አስወጥተው በሰልሀዲን ሰዒድ እና ሙሉዓለም መስፍን ተክተው ሲቀርቡ በአንፃሩ ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ በመጨረሻ ደቂቃ ግብ ከወላይታ ድቻ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ውስጥ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ በአምስት ቢጫ ዛሬ መሰለፍ ባልቻለው ወንድማገኝ ኃይሉ ምትክ አብዱልባሲጥ ከማልን በማስገባት ወደ ጨዋታው ቀርበዋል።

ቀዝቀዝ ያለ አጀማመርን ያስመለከተን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያው የግብ ሙከራ የጨዋታው የመጀመሪያ ግብ ያስመለከተን ነበር። በ9ኛው ደቂቃ ሲዳማዎች ያገኙትን የማዕዘን ምት ፍሬው ሰለሞን ያሻማውን ኳስ ሙሉዓለም መስፍን በአብዱልባሲጥ ከማል ስህተት ታግዞ በግንባሩ በመግጨት ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።

ጨዋታው ዳግም ሲቀጥል ሀዋሳ ከተማዎች ወደ ግራ ካደላ አቋቋም ያገኙትን የቅጣት ምት ዳንኤል ደርቤ ሲያሻማ መስፍን ታፈሰ በግንባሩ በመግጨት ወደ ግብ የላከውን ኳስ ተክለማርያም ሻንቆ በግሩም ሁኔታ አዳነበት እንጂ ሀዋሳ ከተማዎች በፍጥነት ለተቆጠረባቸው ግብ ምላሽ በሰጡ ነበር።

ቀስ በቀስ ጨዋታውን በመቆጣጠር በቅብብሎች ወደ ፊት ማጥቃት የጀመሩት ሲዳማ ቡናዎች በጨዋታው ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ጀምረዋል። በ17ኛው ደቂቃ ላይ ጊት ጋትኩት ከማዕዘን ምት የተነሳችን ኳስ ወደ ግብ ልኮ በዳግም ተፈራ ጥረት የዳነበት እንዲሁም በ23ኛው ደቂቃ ሰልሀዲን ሰዒድ ከማዕዘን ምት የተሻማን ኳስ በግንባር ገጭቶ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣበት ኳስ አደገኛ ሙከራዎች ነበሩ።

ሀዋሳ ከተማ ላይ ፍፁም የበላይነት ወስደው መጫወታቸውን የቀጠሉት ሲዳማ ቡናዎች የሀዋሳ ከተማን ሦስት የመሀል ተከላካዮችን ጫና ውስጥ በማስገባት መጫወታቸውን ቀጥለዋል። በ26ኛው ደቂቃ ይገዙ ቦጋለ ከተከላካዮች ጀርባ የተጣለለትን ኳስ ተጥቅሞ ወደ ግብ ሞክሯት እና ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣችበት እንዲሁም በ28ኛው ደቂቃ ላይ ሰልሀዲን ሰዒድ ከግራ የሳጥኑ ጠርዝ የሞከረው ኳስ ዳግም ያዳነበት ኳስ በአጋማሹ ስለነበራቸው ብልጫ ማሳያ ነበሩ። በአጋማሹ በጥራት ለመከላከል ሆነ በሚለጉት የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ጨዋታውን መቃኘት የተቸገሩት ሀዋሳዎች በአጋማሹ በሁሉም ረገድ ከሲዳማ ቡና አንፃር ሁለተኛው ቡድን ነበሩ።

በ37ኛው ደቂቃ ላይ ፈጣን ቅያሬን ለማድረግ የወሰኑት አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በግራ የመሀል ተከላካይነት ጨዋታውን የጀመረውን አዲስዓለም ንጉሴን በዮሀንስ ሴጌቦ በመተካት ጨዋታቸውን ቀጥለዋል። በ38ኛው ደቂቃ ላይ በአጋማሹ እጅግ ደካማ የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች ሳይጠበቁ አቻ መሆን ችለዋል። ፀጋሰው ድማሞ ከሀዋሳ የግብ ክልል በቀጥታ ወደ ፊት የላከውን ኳስ ያኩቡ መሀመድ በንቃት መከላከል አለመቻሉን ተከትሎ አፈትልኮ ያመለጠው መስፍን ታፈሰ ተረጋግቶ በግሩም ሁኔታ ባስቆጠራት ግብ ቡድኑን አቻ አድርጓል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ አንስቶ አደራደራቸውን ወደ 4-5-1 በመቀየር የጀመሩት ሀዋሳ ከተማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ የተወሰደባቸውን ብልጫ በተወሰነ መልኩ ለማስመለስ በሚያስችል መልኩ የተነቃቃ አጀማመርን ማድረግ ችለዋል። የተሻለ አጀማመር ያደረጉት ሀዋሳዎች በሁለት አጋጣሚዎች ላውረንስ ላርቴ በግንባሩ በመግጨት የሞከራቸው ኳሶች እንዲሁም ብሩክ በየነ ያደረገው ሙከራ ጥሩ የማግባት አጋጣሚዎች ፈጥረዋል። ሆኖም የመጀመሪያ አጋማሽ የነበራቸውን የበላይነታቸውን ማስቀጠል የተቸገሩ የመሰሉት ሲዳማ ከተማዎች በ65ኛው ደቂቃ ዳግም ወደ መሪነት መጥተዋል። ዳዊት ተፈራ ከመሀል ሜዳ ያስጀመረውን ኳስ ይገዙ ቦጋለ ከሀዋሳ ተከላካዮች አፈትልኮ በማምለጥ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ በዳግም ሲመለስ ራሱ ዳዊት ዳግም ተቆጣጥሮ ወደ ግብነት መቀየር ችሏል።

በ77ኛው ደቂቃ ላይ የሲዳማ ቡናው አምበል ፍሬው ሰለሞን የሀዋሳ አቻው ዳንኤል ደርቤ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ መወገዱን ተከትሎ ሲዳማ ቡናዎች ጨዋታውን በአስር ተጫዋቾች ለመጨረስ ተገደዋል። በጨዋታው ሀዋሳ ከተማዎች የነበራቸውን የቁጥር ብልጫ ለመጠቀም ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ቀሪዎቹን ደቂቃዎች በጥንቃቄ ለመጫወት ምርጫቸው ያደረጉት ሲዳማ ቡናዎች የመከላከል አወቃቀርን መፈተን ሳይችሉ ቀርተዋል።

የጨዋታው መደበኛ ጊዜ ሊጠናቀቅ ጥቂት ሰከንዶች በቀሩበት ሂደት ሲዳማ ቡናዎች ሀዋሳ ከተማዎች የቆመ ኳስን ለማጥቃት በቁጥር በርክትው ወደ ሲዳማ አጋማሽ በሄዱበት ቅፅበት በመልሶ ማጥቃት ከዳዊት ተፈራ በተነሳ ኳስ ይገዙ ቦጋለ ባስቆጠራት ግብ ሲዳማ ቡናዎች ከጨዋታው ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘው መውጣት ችለዋል።

ድሉን ተከትሎ ሲዳማ ቡናዎች ነጥባቸው ወደ 30 በማሳደግ 5ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ በአንፃሩ ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ በ31 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ተገደዋል።