[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
በ18ኛው ሳምንት የመጨረሻ የጨዋታ ቀን በቅድሚ በሚደረገው ጨዋታ ዙሪያ ቀጣዮቹን ሀሳቦች አንስተናል።
ሽንፈት ካገኛቸው አራት ጨዋታዎችን ያስቆጠሩት ወላይታ ድቻ እና አዳማ ከተማ በጨዋታ ሳምንቱ እያየናቸው እንዳሉት አዝናኝ ፍልሚያዎች ዓይነት ፉክክርን እንደሚያስመለክቱን ይጠበቃል። ከመሪው በስምንት ነጥቦች ርቆ ሁለተኛ ላይ የታቀመጠው ወላይታ ድቻ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ደረጃውን ለማስጠበቅም ሆነ ከበላዩ ካለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ልዩነቱን ወደነበረበት ለመመለስ የነገው ጨዋታ እጅግ አስፈላጊው ነው። አዳማ ከተማዎች በበኩላቸው ከሰንጠረዡ አጋማሽ ወደ ላይኛው ፉክክር ለመጠጋት የነገውን ጨዋታ ነጥቦች እንደ ድልድይ ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ።
ከጨዋታ መንገድ ውጤታማነት አንፃር የሁለቱ ተጋጣሚዎች ግንኙነት ትኩረትን ይስባል። በመጀመሪያው ዙር ለጥንቃቄ ከፍ ቦታ የነበረው ወላይታ ድቻ አሁን ላይ በቅብብሎች ቦታ በመስጠት ኳስ መስርቶ ለመውጣት ሲሞክር እየታየ ይገኛል። አሰልጣኝ ፀጋዬ በሀዋሳው ጨዋታ ተሻጋሪ ኳሶቻቸው በመሀመድ ሙንታሪ ቁጥጥጥር ስር በመዋላቸው በቅብብሎች መግባትን እንደመረጡ የሚጠቁም አስተያየት መስጠጣቸው ለዚህ ነጥብ አንዱ ማሳያ ነው። አሁን ላይ 4-3-3ን እና 3-5-2ን አፈራርቆ እየተጠቀመ የሚገኘው ቡድኑ የቀደመው የመከላከል ጥንካሬው ተሸርሽሯል ማለት ባይቻልም በአሰላለፍ እና በማጥቂያ መንገዶች ላይ አንዳች ነገር ለመለወጥ እየሞከረ እንደሆነ መናገር ይቻላል። ያም ቢሆን ግን ቡድኑ አሁንም ግቦች እና ሙከራዎችን ከኳስ ምስረታው ሂደት ይልቅ ከቆሙ እና ተሻጋሪ ኳሶች እያገኘ ቀጥሏል።
በአዳማ ከተማ በኩልም ተመሳሳይ ነገር እናገኛለን። የቡድኑ የማጥቃት እሳቤ ለኳስ ቁጥጥር የቀረበ ሆኖ ቢስተዋልም በሚፈለገው ልክ ተጋጣሚን ለረጅም ደቂቃዎች ከኳስ ውጪ እንዲቆይ በማድረግ ጨዋታን ሲቆጣጠር ከዚህ ሂደትም የመጨረሻ የግብ ዕድል ሲፈጥር አይታይም። ይልቁኑም ለፈጣን ሽግግሮች የሚመቹ ቅፅበቶች ሲፈጠሩ ከአማካዮቹ ወደ እነ ዳዋ ሆቴሳ እና አሜ መሀመድ የሚላኩ ኳሶች ቡድኑ ከተጋጣሚ ተከላካዮች ጀርባ እንዲገባ ሲያስችለው ይታያል። በጥቅሉ የሁለቱ ቡድኖች የኳስ ምስረታ ሂደት በበቂ ሁኔታ ያደገ እና ዋነኛ የማጥቃት አማራጫቸው ነው ብሎ ለመናገር ይከብዳል። በመሆኑም በነገው ጨዋታ በዚህ አኳኋን ጨዋታውን ከቀረቡ አንዳቸው ለአንዳቸው ጥሩ የቀጥተኛ እና ከኮሪደሮች የሚሻገሩ ኳሶች ዕድሎችን ሊሰጡ እና ከዚህም መነሻነት ግቦችን ሊያስተናግዱ ይችላሉ ብሎ መናገር ይቻላል።
ከዚህ ውጪ ተጋጣሚዎቹ ከቆሙ ኳሶች ያላቸው ጥንካሬ ሳይነሳ አይታለፍም። ከቆሙ ኳሶች በሚሻሙ አጋጣሚዎች በቀጥታ ወይም በሁለተኛ ኳስ ከባድ ዕድሎችን የሚፈጥሩት ድቻዎች የመጨራሻዎቹን አራት ነጥቦች በዚህ መንገድ ማግኘታቸውን ስናስብ ነገም በተለይ ከመሀል ሜዳው አቅራቢያ የሚገኙ የድቻ ቅጣት ምቶችን እና የማዕዘን ምቶችን በትኩረት እንድናይ ያደርገናል። በአዳማ በኩል ደግሞ ከሊጉ ምርጥ የቅጣት ምት መቺዎች መካከል አንዱ ምናልባትም ግንባር ቀደሙ የሆነው ዳዋ ሆቴሳ መኖር እንዲሁ የግብ ምንጭ ሊሆን መቻሉ የሚነሳ ነው። በጨዋታው እነዚህ የቆሙ ኳሶች ልዩነት ሊፈጥሩ ይችላሉ ብሎ ለመጠበቅ መነሻ የሚሆነው ደግሞ የቡድኖቹ የመከላከል ቁጥር ነው። እስካሁን አዳማ ከተማ 11 ወላይታ ድቻ ደግሞ 13 ግቦችን ብቻ በማስተናገድ በሊጉ ከጊዮርጊስ ቀጥለው የሚቀመጡ በመሆናቸው የነገው ፍልሚያ ከክፍት ጨዋታ ይልቅ ይበልጥ ለመከላከል አስቸጋሪ በሆኑ የቆሙ ኳሶች ግብ የማስተናገድ ዕድሉ ከፍ ብሎ እንዲገኝ ያደርገዋል።
ወላይታ ድቻ ስንታየሁ መንግሥቱን በረጅም ጊዜ ጉዳት እንድሪስ ስዒድን ደግሞ በቀጥታ ቀይ ካርድ ቅጣት ያጣል። አቡበከር ወንድሙ ከጉዳት ያልተመለሰለት አዳማ ተጨማሪ የጉዳት እና ቅጣት ዜና ባይኖርበትም የአዲስ ፈራሚዎቹ ወሰኑ ዓሊ ፣ ፀጋአብ ዮሐንስ እና ውብሸት ጭላሎ የወረቀት ጉዳይ ባለመጠናቀቁ እንደማይጠቀምባቸው ታውቋል።
ጨዋታውን ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው በመሀል ዳኝነት ሲመሩት ኢያሱ ካሳሁን እና ለዓለም ዋሲሁን በረዳትነት ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታደሰ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበውበታል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ 13 ጊዜ የመገናኘት ታሪክ አላቸው። አንድ ጊዜ ብቻ ነጥብ የተጋሩ ሲሆን ወላይታ ድቻ ሰባት ጊዜ አዳማ ደግሞ አምስት ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። በጨዋታዎቹ 26 ግቦች ሲቆጠሩ ወላይታ ድቻ 15 አዳማ ከተማ ደግሞ 11 ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ወላይታ ድቻ (3-5-2)
ፅዮን መርዕድ
በረከት ወልደዮሐንስ – አንተነህ ጉግሳ – መልካሙ ቦጋለ
ያሬድ ዳዊት – ሀብታሙ ንጉሴ – ንጋቱ ገብረስላሴ – አዲስ ህንፃ – አናጋው ባደግ
ምንይሉ ወንድሙ – ቃልኪዳን ዘላለም
አዳማ ከተማ (4-3-3)
ጀማል ጣሰው
ጀሚል ያዕቆብ – ቶማስ ስምረቱ – አዲስ ተስፋዬ – ሚሊዮን ሰለሞን
አማኑኤል ጎበና – ዮሴፍ ዮሐንስ – ዮናስ ገረመው
አሜ መሀመድ – ዳዋ ሆቴሳ – አብዲሳ ጀማል