ቅድመ ዳሰሳ | ወልቂጤ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የ18ኛ ሳምንት የማሳረጊያ ጨዋታን እንደሚከተለው ቃኝተነዋል።

በሦስት ነጥብ ተበላልጠው ስድስተኛ እና አስራ አንደኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ወልቂጤ እና ባህር ዳር ከተማ የ18ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታን በጥሩ ፉክክር ያገባድዳሉ ተብሎ ይጠበቃል። በአሠልጣኝ ተመስገን ዳና የሚመራው ወልቂጤ ከ13 ጨዋታዎች በኋላ ተከታታይ ድል ለማስመዝገብ ተግቶ ሲጫወት ባህር ዳር ከተማ ደግሞ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ለመታረቅ ጠንክሮ እንደሚንቀሳቀስ ይታመናል።

ባሳለፍነው ሳምንት ውዝግቦች የተነሱበት ፋሲል ከነማ ላይ ወልቂጤ ያገኘው ድል በዛሬው ዕለት መቋጫ አግኝቷል። ድረ-ገፃችን ከሰዓታት በፊት ባስነበበችው ዘገባም ወልቂጤ ላይ በተጋጣሚ ቡድን የቀረበው የተጫዋች ተገቢነት ክስ ውድቅ በመሆኑም ቡድኑ በወቅቱ የሊጉ ባለ ክብር ላይ ያገኘው ድል ከፍተኛ ተነሳሽነት ፈጥሮ በነገው ጨዋታ ትሩፋቱ ሊቀጥል ይችላል። አዝናኝ በነበረው ጨዋታ ወልቂጤ የፋሲልን ከወገብ በታች የሚገኙ ተጫዋቾች ክፍተት ለመጠቀም የጣረበት መንገድ በደቂቃ ልዩነት ዋጋ አስገኝቶት እንደነበር አይዘነጋም። በተለይ ፈጣኖቹ አጥቂዎች የተከላካዮችን የአቋቋም፣ ውሳኔ እና ቅልጥፍና በመገንዘብ ያደረጉት እንቅስቃሴ አሠልጣኙ ከጨዋታው በኋላ እንዳሉት ታስቦበት የተደረገ ነበር። ምናልባት የባህር ዳር ከተማ ተከላካዮችም የትኩረት እና የውሳኔ ክፍተት ስላለባቸው ስልታቸውን በድጋሜ ተግባራዊ ሊያደርጉ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከኳስ ጋር ፈጣን ከኳስ ውጪ ታታሪ ቡድን የሚመስለው ወልቂጤ በነገው ጨዋታ ኳሱን ለባህር ዳር በመተው እንደሚጫወት ይገመታል። በተለይ ወራጅ ቀጠና ላይ ከሚገኙት ክለቦች ውጪ ሁለተኛው ብዙ ግብ ያስተናገደ ቡድን ስለሆነም ማሸነፍ ናፍቆት የሚመጣውን የባህር ዳር ስብስብ በቡድናዊ መዋቅር ወረድ ብሎ እንደሚከላከል ይታሰባል። ከዚህ ውጪ ደግሞ በፈጣን ሽግግሮች ኳስ እና መረብን ለማገናኘት መጣራቸው የማይቀር ነው። ምናልባት ግን በቡድኑ ሽግግር እና የመስመር ጥቃት ትልቅ ቦታ ያለው የግራ መስመር ተከላካዩ ረመዳን በጉዳት ምክንያት አለመኖሩ መጠነኛ መሳሳት ሊያስከትል ይችላል። የቡድኑን 58.9% ግብ ያስቆጠሩት ጌታነህ እና ጫላ ደግሞ ዋነኞቹ የባህር ዳር ተከላካዮች ትኩረት መሆናቸው የማይቀር ነው።

ካለፉት አስር የሊጉ ጨዋታዎች አንዱን ብቻ የረታው ባህር ዳር ከተማ የውድድር ዓመቱ ሲጀምር ከነበረበት መጠበቅ እጅግ ያነሰ እንቅስቃሴ እያሳየ የወረደ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል። እጅግ መቀራረብ ባለበት የታችኛው የደረጃ ክፍልም ከአስጊው ቀጠና በአራት ነጥቦች እና ሦስት ደረጃዎች ብቻ ከፍ ብሎ ተቀምጧል። እርግጥ በሰንጠረዡ ካለው የነጥብ መቀራረብ አንፃር ጥቂት ድሎች ወደ ላይ ስለሚያስመነድጉ ቡድኑ ከወዲሁ በመንቃት ቦታውን ማሻሻል ይገባዋል። ባሳለፍነው ሳምንት በሀዲያ ሆሳዕና ቡድኑ ሲረታ ጥሩ በነበረበት ደቂቃ ግብ አለማስቆጠሩ እጅግ ዋጋ አስከፍሎታል። በእንቅስቃሴ ደረጃ መጥፎ የሚባል ባይሆንም ባለፉት ጨዋታዎች ሲታይበት ከነበረው የግብ ዕድል የመፍጠር ችግር በተለየ ዕድገት አሳይቶ በተደጋጋሚ የሀዲያ የግብ ክልል ሲጎበኝ ነበር። ነገርግን ያለቀላቸው አጋጣሚዎችንም ሲያመክን ታይቷል። ይህ የጎል ፊት አይናፋርነት ተቀርፎ ከመጣ ግን ወልቂጤ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ያሰጋል።

በላይኛው የፍፁም ቅጣት ምት ብቻ ሳይሆን በራሱም ክልል ደካማ የሆነው ባህር ዳር የተከላካዮች እና የግብ ጠባቂ የግል እና የቡድን ስህተቶች ዋጋ እያስከፈለው ተጫዋች እና መዋቅር ሲለዋውጥ ይታያል። በሀዲያውም ፍልሚያ ወሳኝ ተጫዋቹ ፍፁም ዓለሙን ተጠባባቂ አማካዩ በረከት ጥጋቡ እና ተከላካዩ ሰለሞን ወዴሳን ደግሞ ከጨዋታ ውጪ በታክቲካዊ ውሳኔ ማድረጉ ለዚህ ማሳያ ነው። በተለይ ከኳስ ውጪ ያለው መዋቅር መስተካከል ያለበት ጉዳይ እንደሆነ በሚገባ በየጨዋታው ይታያል። በነገው ጨዋታም ወልቂጤዎች ይህንን ስስ ጎን በማጉላት ውጤት ለመያዝ ስለሚጥሩ መጠንቀቅ ይበጃል። በሀዲያው ጨዋታ ቡድኑ ብቸኛ ያተረፈው ነገር የሚመስለው ጉዳይ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በውሰት የመጣው የአደም አባስ ብቃት ነው። ተጫዋቹ ሊጉን ገና ሳይለምድ ሜዳ ላይ በቆየባቸው 34 ደቂቃዎች የነበረው ፍላጎት፣ ታታሪነት እና ተነሳሽነት በቀጣዮቹ ጨዋታዎች ትልቅ ተስፋ እንዲጣልበት የሚያደርግ ነው። ነገም የጨዋታ ዕድል ካገኘ ዋነኛ የግራ መስመር ተከላካዩን በጉዳት ላጣው ወልቂጤ ከባድ የቤት ሥራ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።

ሰራተኞቹ እንደገለፅነው በፋሲሉ ጨዋታ ተጎድቶ በ70ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የወጣው ረመዳን የሱፍን በነገው ጨዋታ አያገኙም። ከእርሱ በተጨማሪ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አማካይ ኤዲ ኢሞሞ ኒጎዬ የወረቀት ጉዳዮች ባለመገባደዳቸው የጨዋታ ዕድል አይኖረውም። የጣናው ሞገዶቹ በበኩላቸው ከረጅም ሳምንታት በኋላ ከቅጣት እና ጉዳት ዜና የሚርቁ ሲሆን ግርማ ዲሳሳም ቅጣቱን ጨርሶ እንደሚመለስ ታውቋል።

የሳምንቱ መዝጊያን ጨዋታ አሸብር ሰቦቃ በመሐል ሻረው ጌታቸው እና ሶርሳ ዱጉማ በረዳት ለሚ ንጉሴ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት እንደሚሳተፉ ተመላክቷል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ወልቂጤ እና ባህር ዳር ከዚህ ቀደም ሦስት ጊዜ ተገናኝተዋል። በግንኙነታቸውም እኩል አንድ አንድ ጊዜ ተሸናንፈው አቻ ወተዋል። በሦስቱ ጨዋታዎች ወልቂጤ ሁለት ባህር ዳር ደግሞ ሦስት ግብ አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሠላለፍ


ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)

ሰዒድ ሀብታሙ

ተስፋዬ ነጋሽ – ዳግም ንጉሴ – ዋሀብ አዳምስ – አበባው ቡጣቆ

በሀይሉ ተሻገር – ሀብታሙ ሸዋለም – ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ

አብዱልከሪም ወርቁ – ጌታነህ ከበደ – ጫላ ተሺታ

ባህር ዳር ከተማ (4-2-3-1)

ፋሲል ገብረሚካኤል

መሳይ አገኘሁ – ሰለሞን ወዴሳ – ፈቱዲን ጀማል – አህመድ ረሺድ

ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – አለልኝ አዘነ

አብዱልከሪም ኒኪማ – ፍፁም ዓለሙ – አደም አባስ

ኦሲ ማውሊ