ሪፖርት | ቀዝቃዛው ጨዋታ ያለግብ ተቋጭቷል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የአዳማ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ በ18ኛው ሳምንት ግብ ያልተቆጠረበት የመጀመሪያ ጨዋታ ሆኗል።

ወላይታ ድቻ ከሀዋሳው ጨዋታ የቀጥታ ቀይ ካርድ የተመለከተው እንድሪስ ሰዒድን በአበባየሁ አጪሶ ሲተካ በአዳማ በኩል በተደረጉ ሁለት ለውጦች ታደለ መንገሻ እና አብዲሳ ጀማል በእዮብ ማቲያስ እና ዮናስ ገረመው ተተክተዋል።

በጨዋታው ጅማሮ አዳማ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥር ጫን ብለው የተንቀሳቀሱበት እንቅስቃሴ ታይቷል። በአንፃሩ ወላይታ ድቻ ከሰሞኑ በተለየ ወደ ቀደመ አቀራረቡ መለስ ብሎ በራሱ ሜዳ ላይ በመቆየት የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ይጠባበቅ ነበር። ቀስ በቀስ ቡድኑ ወደ አዳማ የግብ ክልል የቀረበባቸው ፈጣን የማጥቃት ሽግግሮች መታየት ሲጀምሩ 17ኛው ደቂቃ ላይ ግን ይበልጥ ለግብ ቀርቦ ነበር። ከኋላ በቀጥታ በተጣለ ኳስ ቃልኪዳን ዘላለም ከተከላካዮች ጀርባ በመግባት ጀማል ጣሰውን አልፎ ወደ ግብ ለመምታት ከመወሰኑ በፊት ጀማል በድጋሚ ደርሶ አስጥሎታል።

ከቃልኪዳን ሙከራ በኋላ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ አዳማዎች አከታትለው በዳዋ ሆቴሳ እና አማኑኤል ጎበና ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይ አማኑኤል ከአብዲሳ ጀማል ተቀብሎ በቀጥታ ወደ ግብ የመታው ኳስ በፅዮን መርዕድ ነበር ግብ ከመሆን የዳነው። አዳማዎች በቀጣይ ደቂቃዎች በቅብብል ወደ ጎል ለመቅረብ ሲሞክሩ ቢታዩም በበቂ ሁኔታ ሰብረው መግባት አልሆነላቸውም።

የወላይታ ድቻዎች የመልሶ ማጥቃትም አስፈሪነቱ ቀንሶ ቀይቶ ሲታይ በሂደት ግን የቡድኑ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎች ታይተው ነበር። በተለይም 29ኛው ደቂቃ ላይ የያሬድ ቅጣት ምት በድቻ ተጫዋቾች ወደ ግብነት ለመቀየር የተደረገ ርብርብ በአዳማም ተመሳሳይ የመከላከል ምላሽ ተሰጥቶት ከሽፏል። በቀሩት ደቂቃዎች ጨዋታው መሀል ሜዳ ላይ በሚቆራረጡ ካሶች የቀጠለ ሲሆን ወደ ማብቂያው ላይ ድቻዎች ያሬድ ዳዊት በተሰለፈበት የቀኝ መስመር ሁለት አደገኛ ኳሶችን ቢያደርሱም ወደ ሙከራነት ሳይቀየሩ ቀርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ነፍስ የዘራ መስሏል። ሁለቱም ተጋጣሚዎች ወደ ሁለቱም ሳጥኖች የገቡባቸው አጋጣሚዎች ተደጋግመው መታየት ጀምረዋል። ሆኖም እነዚህ የማጥቃት ጥረቶች ወደ መጨረሻ የግብ ዕድልነት ተቀይረው ግብ ጠባቂዎችን ሲፈትኑ አልታዩም። የተሻለው ሙከራ 61ኛው ደቂቃ ላይ ሲታይ አማኑኤል ጎበና እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ በፅዮን ተመልሶበታል። ከዚህ በኋላ እስከ ጨዋታው ፍፃሜ የበረው እንቅስቃሴ አልፎ አልፎ ከርቀር የሚደረጉ ሙከራዎች እየታዩበት እና አንዳቸው የሌላኛቸውን የማግባት ጥረት ከጅምሩ እያቋረጡ ለዓይን በማይማርክ ፉክክር ወደ ፍፃሜው ደርሶ ያለግብ ተጠናቋል።

በውጤቱ ወላይታ ድቻ በ33 ነጥብ ሁለተኛ ላይ ሲረጋ አዳማ ከተማ 24 ደርሶ ከሰባተኝነት ወደ ስድስተኝነት ከፍ ብሏል።