ሪፖርት | አዝናኙ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ጥሩ ፉክክር ያስመለከተን የአመሻሹ ጨዋታ ጫላ ተሺታ በ88ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ ወልቂጤ ከተማ እና ባህር ዳር ከተማ ተከባብረው ጨዋታቸውን በሁለት አቻ ውጤት ፈፅመዋል።

ወልቂጤ ከተማዎች ፋሲል ከነማ ከረታው ስብስብ አራት ለውጦችን ሲያደርጉ በዚህም ሰዒድ ሀብታሙ ፣ ረመዳን የሱፍ ፣ ሀብታሙ ሸዋለም እና አክሊሉ ዋለልኝን ወደ ተጠባባቂነት አውርደው በምትካቸው ሮበርት ኦዶንካራ ፣ ዳግም ንጉሴ ፣ ዮናስ በርታ እና ያሬድ ታደሰ በመጀመሪያ ተመራጭነት አስጀምረዋል።

ባህርዳር ከተማዎች ደግሞ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ነጥብ ከተጋራው ስብስብ በተመሳሳይ አራት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን በዚህም አህመድ ረሺድ ፣ አለልኝ አዘነ ፣ አብዱልከሪም ኒኪማ እና ተመስገን ደረሰን ያስወጡ ሲሆን መሳይ አገኘሁ ፣ አደም አባስ ፣ ግርማ ዲሳሳ እና ኦሲ ማውሊ እነሱን ተክተው ወደ ሜዳ የገቡት ተጫዋቾች ነበሩ።

በጨዋታው ፈጣን አጀማመር ያደረጉት ወልቂጤ ከተማዎች በ30ኛው ሰከንድ መሀል ሜዳ ላይ ከነጠቁት ኳስ በኃይሉ ተሻገር ለጌታነህ ከበደ ባደረሰው ግሩም ኳስ የመጀመሪያ ሙከራቸውን አድርገው ነበር። ኳሷ ለጥቂት የግቡን ቋሚ ታካ ወጣች እንጂ ገና በማለዳው ቀዳሚ በሆኑ ነበር።

በፍጥነት ወደ ፊት መሄዳቸውን የቀጠሉት ወልቂጤ ከተማዎች በ5ኛው ደቂቃ ግን ቀዳሚ መሆን ችለዋል ፤ አበባው ቡጣቆ ከማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ ዋሀቡ አዳምስ በግንባሩ በመግጨት ቀዳሚዋን ግብ አስቆጥሯል።

በወልቂጤ ከተማ ቅድሚያ የተወሰደባቸው ባህር ዳር ከተማዎች ከግቧ በማገገም ቀስ በቀስ የኳስ ቁጥጥር ድርሻቸውን ማሳደግ ቢችሉም በአጋማሹ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ፍፁም ደካማ ነበሩ።

ከመጨረሻው ጨዋታ ከተጠቀሙባቸው የአጥቂ መስመር ተሰላፊዎችን በሙሉ የቀየሩት እና ከእነሱ ጀርባ ደግሞ ፉአድ ፈረጃ እና ፍፁም ዓለሙን በነፃ 8 ቁጥርነት በመጠቀም ፍፁም ለማጥቃት የተመቸ የተጫዋቾች አደራደር ሆነ ምርጫ የነበራቸው ባህር ዳር ከተማዎች እነዚህን ሁሉ ተጫዋቾች ቢይዙም ማጥቃታቸው አስፈሪ አልነበረም።

ባህር ዳር ከተማዎች በአጋማሹ በአመዛኙ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ ወደ ግብ ከሚላኩ እንዲሁም ከሚሻገሩ ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ቢያደርጉም ጥድፊያ የተሞላው ማጥቃታቸው ተጠቃሽ ሙከራን ግን ለመፍጠር ተቸግሯል። በአንፃሩ ከግቧ በኋላ ለተጋጣሚ ኳሱን ፈቅደው ከኳስ ውጪ ብዙ በመታተር እንዲሁ ወደ ማጥቃት በሚደረጉ ፈጠን ያሉ ሽግግሮች ለመጫወት ፍላጎት የነበራቸው ወልቂጤዎች በአንፃራዊነት ወደ ፊት ሲሄዱ አስፈሪ የነበሩ ቢሆንም አጋማሹ ግን ሁለት ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን የተመለከትንበት ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ባህር ዳሮች አደም አባስ እና ሄኖክ ኢሳያስን አስወጥተው በምትካቸው ዓሊ ሱሌይማን እና አብዱልከሪም ኒኪማን በማስገባት ይበልጥ ማጥቃታቸውን ለማሻሻል ጥረት አድርገዋል። ታድያ በ47ኛው ደቂቃ ወደ ጨዋታው የተመለሱበትን ግብ በግርማ ዲሳሳ አማካኝነት አግኝተዋል። ግርማ ዲሳሳ ከሳጥን ውጪ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ የላካት ኳስ ከመረብ መዋሀዷን ተከትሎ ባህር ዳር ከተማዎች ወደ ጨዋታው መመለስ የቻሉበትን አጋጣሚ ፈጥረዋል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ ባህር ዳር ከተማዎች ይበልጥ ጫና አሳድረው በማጥቃት ለመጫወት ጥረት ያደረጉ ሲሆን በዚህም ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር በተለይም በእርጋታ ከማጥቃት አንፃር መሻሻሎችን የተመለከትን ሲሆን በ57ኛው እና 63ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ዓለሙ ከሳጥን ውስጥ ውጭ ያደረጋቸው እና ሮበርት ኦዶንካራ በቀላሉ የያዛቸው ኳሶች ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።

በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ የተሻለ አጋማሽ ያሳለፉት ባህር ዳር ከተማዎች በ75ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተነሳው ኳስ ዳግም ወደ ቀኝ መስመር መውጣቱን ተከትሎ ፍፁም ዓለሙ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ኦሲ ማውሊ የመጀመሪያውን ኳስ ማሸነፉን ተከትሎ በነፃነት ያገኘው አምበላቸው ፍቅረሚካኤል ዓለሙ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሯል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ ባህር ዳር ከተማዎች ይበልጥ ተጠንቅቀው በመጫወት ከአምስት ጨዋታ በኋላ በእጃቸው የገባውን ሦስት ነጥብ ለማስጠበቅ ጥረት ማድረግ ሲጀምሩ በአንፃሩ ወልቂጤ ከተማዎች ደግሞ በጨዋታው አቻ ለመሆን ሲታትሩ አስተውለናል።

የወልቂጤ ከተማዎች ጥረት በስተመጨረሻም ፍሬ አፍርቷል። በ88ኛው ደቂቃ ወልቂጤ ከተማዎች ወደ ግራ ካደላ አቋቋም በጌታነህ ከበደ አማካኝነት ያሻሙትን የቅጣት ምት ኳስ ጫላ ተሺታ በግንባሩ ገጭቶ የባህር ዳሮችን ደስታ ስሜት ላይ ውሃ የቸለሰች እንዲሁም የወልቂጤ ደጋፊዎችን ያስፈነደቀች ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ሁለት አቻ ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ ባህር ዳር ከተማዎች በ22 ነጥብ ወደ አስረኛ ደረጃ ሲንሸራተቱ ወልቂጤ ከተማዎች በ25 ነጥብ በነበሩበት ስድስተኛ ደረጃ ላይ ሆነው ወደ ቀጣዩ የጨዋታ ሳምንት አምርተዋል።