የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 2-2 ባህርዳር ከተማ

የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞች ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

አሰልጣኝ ተመስገን ዳና – ወልቂጤ ከተማ

ስለጨዋታው

“በፈለግነው መንገድ ሄዷል ብዬ አላስብም። የመጀመሪያው አርባ አምስት ላይ የእነርሱ ቁልፍ ተጫዋቾችን ለማቆም የነበረን ከፍተኛ ጭንቀት ከራሳችን መንገድ አውጥቶናል፡፡ ያንን ለማስተካከል በሁለተኛው አጋማሽ ተጫዋቾችን ቀይረን ጥሩ ጀምረን ነበር። ነገር ግን ጎል ስናስተናግድ ከጀመርነው መንገድ ወጣን ስለዚህ ፕላኖቻችንን ስንቀያይር የተረጋጋ ቡድን አልነበርንም ዛሬ ማለት እችላለሁ፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ስለታየባቸው ድካም

“የድካም ሁኔታ ሳይሆን እነሱ ለዚህ ጨዋታ በጣም ተዘጋጅተው እንደሚመጡ እንገምት ነበር። ምክንያቱም በርካታ ጨዋታዎችን ነጥብ አጥተው ነው የመጡት። ስለዚህ በቁርጠኝነት ይሄን ጨዋታ ለማሸነፍ እንደሚመጡ እናውቃለን፡፡ ጠንካራ ተፎካካሪዎች እንደሆኑም እኛም እናውቃለን። ሁለተኛ አርባ አምስት ላይ ለማስጠበቅ የነበረን ነገር ነው የጎዳን ብዬ ነው የማስበው፡፡ ፕላኖችን በተወሰኑ ደቂቃዎች እንቀይር ነበር ያ ቡድናችን የተረጋጋ መንገድ እንዳይኖረው አድርጎታል፡፡

ስለሮበርት ኦዶንካራ ብቃት እና ጥሩ የነበረው ሰይድ ስላቸርለመሰለፉ

“ሰይድ ሀብታሙ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ላይ የነበረው ብቃት ሁሉም ሰው የሚመሰክረው ነው፡፡ ሮበርት ኦዶንካራ ግን ወደ ፉክክር ለማስገባት ይሄንን ጨዋታ ማስጀመር ነበር፡፡ ምክንያቱም ሰይድ ሀብታሙ ሁለተኛ ጨዋታውን ተጫውቶ ሦስተኛ ጨዋታ ብናስቀጥለው ሮበርት ኦዶንካራን ከፉክክር እናስወጣዋለን። ስለዚህ ፉክክሩ ተመጣጣኝ እንዲሆን የግድ ሁለቱንም ማየት አለብን የሚል ነገር ስላለ ነው፡፡

ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ጎል ስላስቆጠረው ጫላ ተሺታ ብቃት

“ጫላ እጅግ አስገራሚ ልጅ ነው፡፡ ገና ትልቅ ቦታ መድረስ የሚችል ነው፡፡ ለሀገራችንም ፕሮፌሽናልም ሆኖ ለትልቅ ደረጃ ይጫወታል ብዬ አስባለሁ፡፡ ካለው ዕድሜ ካለው ኳሊቲ እና ከኳስ ፍላጎት አንፃር ይሄንን ማሳካት ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡”

አሰልጣኝ አብረሃም መብራቱ – ባህርዳር ከተማ

ስለጨዋታው

“የመጀመሪያው አርባ አምስት የመጀመሪያ አስራ አምስት ደቂቃዎች በምፈልገው መልኩ አልሄደም። ከዛ በኋላ ግን ባደረግነው የታክቲክ ለውጥ ከመጀመሪያው አስራ አምስት ደቂቃ ጀምሮ ጨዋታው እስከሚያልቅ በሚገባ ተቆጣጥረናል ማለት እችላለሁ፡፡ ከመጀመሪያው አርባ አምስት ሁለተኛው አርባ አምስት የተሻለ ተንቀሳቅሰናል ብዬ አስባለሁ፡፡

ስለሁለተኛው አጋማሽ መሻሻል

“በመጀመሪያ አርባ አምስት ላይ የተጫወትነው 4-3-2-1 ነበረ፡፡ ከዕረፍት በኋላ ግን የማጥቃት ሚዛናችንን ከፍ ለማድረግ ወይም ጎል ለማግኘት 4-4-2 በዳይመንድ ተጫውተናል ፤ ውጤታማ ሆነንበታል። ግን ዞሮ ዞሮ ከቆሙ ኳሶች የሚገቡብን ጎሎች ዋጋ አስከፍለውናል፡፡ በተረፈ ግን ተጫዋቾቹ በዛሬው ጨዋታ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሁለተኛ ጎል ካስቆጠሩ በኋላ ተከላካይ መቀየራቸው ለማስጠበቅ ስለመሆኑ

“ያው ፉአድ ከፆሙ ጋር ተያይዞ ትንሽ ደከም ስላለ በምትኩ ደግሞ የኃላውን ክፍል ለማጠናከር ስለፈለግን በአብዛኛው በክንፍ የሚመጡ ኳሶች በተለይ ደግሞ በነሱ የቀኝ በኩል የሚመጡ ኳሶች አደገኛ ስለነበሩ ተከላካዩን ጠንካራ አድርገን ውጤቱን ይዘን ለመውጣት ነበረ ያሰብነው። ነገር ግን የቆመ ኳስ አግኝተው ሳጥን ውስጥ ሰው በሰው ማርኪንግ የተሻለ ስላልነበረ ያ ኳስ በግንባር ተገጭቶ እኛ ላይ ገብቶብናል፡፡ እና ለውጡን ያደረኩት የታክቲክ ለውጥ በማድረግ ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት ነው፡፡”