ወልቂጤ ከተማ በድጋሚ በተጋጣሚው ተከሷል

ሠራተኞቹ በዛሬ ምሽቱ ጨዋታ የተጨዋቾች ተገቢነት ክስ በባህር ዳር ከተማ ተመስርቶባቸዋል።

በ17ኛው ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ፋሲል ከነማን 2-1 ማሸነፍ ይቻሉት ወልቂጤ ከተማዎች በተጨዋቾች ዝውውር መነሻነት በዐፄዎቹ ክስ ተመስርቶባቸው ውጤታቸው ለጊዜው ሳይፀድቅ ቀርቶ እንደነበር ይታወሳል። ከቀናት በፊት ጉዳዩ ከሊጉ አክሲዮን ማህበር ወደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አምርቶ በተሰጠበት ምላሽም ክሱ ውድቅ ሆኖ ነበር። ሆኖም ዛሬ ምሽት በተደረገው ሌላ ጨዋታ ከባህር ዳር ከተማ ጋር 2-2 የተለያዩት ወልቂጤዎች ሌላ ክስ ገጥሟቸዋል።

ባህር ዳር ከተማ ምሽቱን ለፕሪምየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር የላከው ደብዳቤ ወልቂጤ በጨዋታው ላይ ያደረጋቸውን ቅያሪዎች ይመለከታል። በክለቡ ሥራ አስኪያጅ በተፈረመው ደብዳቤ ላይ ወልቂጤ ከተማ በምሽቱ ጨዋታ ቀይሮ ወደ ሜዳ ያስገባቸው ሀብታሙ ሸዋለም ፣ ቤዛ መድህን ፣ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ ፣ ረመዳን የሱፍ እና አቡበከር ሳኒን የክሱ መነሻ ሆነዋል።

ባህር ዳር ከተማ አክሲዮን ማህበሩ ለዘንድሮው ውድድር ባወጣው የተጨዋቾች ቅያሪ ደንብ ላይ ቡድኖች ከሚያደርጓቸው አምስት ቅያሪዎች ሦስቱ በአረንጓዴ ቴሴራ ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ በልዩ ወይንም በቢጫ ቴሴራ የተመዘገቡ ተጫዋቾች መሆን እንዳለባቸው በማንሳት የወልቂጤ የዛሬ ቅያሪዎች በሙሉ በአረንጓዴ ቴሴራ የተመዘገቡ መሆናቸውን አስቀምጧል። በዚህም መሰረት ክለቡ ‘ሊግ ካምፓኒው አስፈላጊውን ውሳኔ ይስጠኝ’ ሲል አመልክቷል።

ያጋሩ