አዲስ አበባ ከተማ ለአሠልጣኙ ደብዳቤ ሲፅፍ አሰልጣኙም ቅሬታ አሰምተዋል

የመዲናይቱ ክለብ አዲስ አበባ ከተማ ለዋና አሠልጣኙ ደምሰው ፍቃዱ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ሲፅፍ አሠልጣኙም በክለቡ አመራሮች ላይ ያላቸውን ቅሬታ ገልፀዋል።

ሊጉን ዘንድሮ የተቀላቀለው አዲስ አበባ ከተማ ውድድሩን በአሠልጣኝ እስማኤል አቡበከር ጀምሮ በአሁኑ ሰዓት በአሠልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ እየተመራ ከተጫወተው ጨዋታ እኩል 18 ነጥቦችን ሰብስቦ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ባለንበት ሳምንት መከላከያን በሪችሞንድ አዶንጎ ሁለት ግቦች ያሸነፈው ክለቡም ከድሉ ዕለት ዋዜማ ለአሠልጣኙ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ መፃፉን አውቀናል።

ለአሠልጣኙ የተፃፈው ደብዳቤ ክለቡ ላይ እየተስተዋለ ያለውን የውጤት መውረድ ግምት ውስጥ በማስገባት በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ውጤት የሚሻሻልበት ሁኔታ እንዲፈጠር በመግለፅ ካልሆነ ግን በውስጥ ደንብ መሠረት ክለቡ የራሱን አማራጭ እንደሚወሰወድ ይገልጻል።

ዋና አሠልጣኙ ደምሰው ፍቃዱ በበኩላቸው ደብዳቤው ከደረሳቸው በኋላ ቅሬታ እንዳላቸው ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል። አሠልጣኙም “ደብዳቤው የተላከልኝ ከትናንት በስትያ ወደ ስታዲየም ልንሄድ ሁለት ሰዓት ሲቀረን ነው። እንደ አጋጣሚ እኔ ደብዳቤውን ያየሁት ከጨዋታው በኋላ ምሽት ላይ ነው። ከጨዋታው በፊት አላየሁትም። ዋናው ነገር ግን እኔ የክለቡ አመራሮች ላይ ቅሬታ አለኝ። እስካሁን በጊዜያዊነት ከዛም በዋና አሠልጣኝነት ስሰራ ዓምና በከፍተኛ ሊግ በምክትልነት ሳሰለጥን በሚከፈለኝ የደሞዝ እርከን ነው። ችግር የለም ላገልግል ብዬ በምሰራበት ሰዓትም እንደዚህ አይነት ሞራል የሚነኩ ነገሮች ይደረጉብኛል። አመራሮቹ በ18 ጨዋታዎች ሦስት ጊዜ ብቻ ነው መተው ስታዲየም የተመለከቱን። ክትትል በደንብ አያደርጉልንም። ይህ ደስተኛ አላደረገኝም። እንዴት እያገለገልኩ እንደሆነ እየታወቀ ይህንን አይነት ደብዳቤ ሊፃፍልኝ አይገባም።” ብለዋል።

የአሠልጣኙን ጥያቄ በተመለከተ በክለቡ በኩል ምላሽ ካለ ብለን ሥራ-አስኪያጁ አቶ ነፃነት ታከለን አግኝተናል። “ልክ ነው። ለአሠልጣኙ በውስጥ ደንብ መሰረት ደብዳቤ ልከናል። ይህ ግን የውስጥ አሰራር ነው። ሁላችንም እየሰራን ያለነው ለክለቡ ነው። እኔን ጨምሮ ማንም ሰው ከክለቡ በላይ አይደለም። ስለዚህ ክለቡን ለማትረፍ ሥራዎች ይሰራሉ። በአጋማሹ የዝውውር መስኮት በአሠልጣኙ ሀሳብ አምስት ተጫዋቾችን ለውጠናል። ይህንን ያረግነው ክለቡን ለማትረፍ ነው። ተጫዋቾቻችን ያላቸው ብቃት ይታወቃል። ፋሲል ከነማ እና መከላከያ የመሳሰሉ ክለቦች ጋር የተጫወቱበት መንገድ አለ። ይህንን የእነሱን ብቃት ማሳደግ ተገቢ ነው። ስለዚህ ክለቡ እስኪወርድ መጠበቅ የለብንም።

“ክትትል አያደርጉም የተባለው አዲስ አበባ በስሩ የወንዶች ቡድን ብቻ አይደለም ያለው ሌሎችም ቡድኖች አሉት። እኛ እንደ አመራር ሁሉንም በእኩል ዐይን እያየን እንከታተላለን። ከሰው ሀይል እጥረት ጋር ተያይዞ ደግሞ ተደራራቢ ስራዎችን ስለምንሰራ ሁሌ ሜዳ ላንገኝ እንችላለን። ግን ደግሞ የቴክኒክ ዳይሬክተር አለን። ከእሱ ጋር በደንብ እየተገናኘን ሪፖርቶችን እንሰማለን። ደሞዝን በተመለከተ እኛ ‘አንተ በርታ እንጂ የሚያስፈልገውን እናረጋለን’ እያልን ነው። አሁንም ማስተካከያ ለማድረግ በንግግር ላይ ነን።” በማለት ምላሽ ሰጥተውናል።

አሠልጣኙ ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት ካስተናዱ አማራጭ ይወሰድባችኋል ቢባሉም ደብዳቤው በተፃፈ ማግስት ድል ማድረጋቸው ቀጣዮቹን ጊዜ እንድንጠብቅ የሚያደርገን ነው።