የባህርዳር ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ ጨዋታ ውሳኔ ተላልፎበታል

ትላንት ከወልቂጤ ከተማ ጋር አቻ ተለያይቶ የነበረው እና ለአክሲዮን ማህበሩ የተጫዋች ተገቢነት ክስ አስገብቶ የነበረው ባህርዳር ከተማ ምላሽ አግኝቷል።

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ18ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በባህርዳር ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ መካከል ተደርጎ 2-2 በሆነ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ባህርዳር ከተማ በወልቂጤ ከተማ ላይ ቅሬታ ማሰማቱንም በድረገፃቸን ጠቁመን ነበር፡፡

የጣና ሞገደኞቹ ‘ሦስት በአረንጓዴ ሁለት በቢጫ ቴሴራ ተጫዋቾች መቀየር ሲገባቸው አምስቱም በአረንጓዴ ቴሴራ የተመዘገቡ ተጫዋቾች ተቀይረው ገብተዋል ይሄ ደግሞ የተቀመጠውን የቅያሬ መመሪያ የጣሰ ነው።’ በሚል ወልቂጤ ከተማ ላይ ለሊግ ካምፓኒው አቤቱታን አቅርበው ነበር፡፡

አወዳዳሪው አካልም ጉዳዩን ተመልክቶ በፕሪምየር ሊጉ የሥነ ሥርአት መመሪያ ክፍል አንድ አንቀፅ 13 በተራ ቁጥር 29 መሠረት ወልቂጤ ከተማ ህጉን የተከተለ አቀያየር አላደረገም በማለት ባህር ዳር ከተማ ሦስት ነጥብ እና ሦስት ጎል እንዲያገኝ ወስኗል፡፡

ያጋሩ