[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]
ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የደቡብ አፍሪካ አቻውን ከሜዳው ውጪ ሦስት ለምንም ረቷል።
በህንድ አስተናጋጅነት ለሚከናወነው የዓለም የሴቶች ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ውድድር ለማለፍ የአህጉራችን ብሔራዊ ቡድኖች የማጣሪያ ጨዋታቸውን እያደረጉ እንደሆነ ይታወቃል። በአሠልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በሁለተኛ ዙር ማጣሪያ የዩጋንዳ አቻውን ከሜዳ ውጪ ባገባ በሚለው ህግ ጥሎ የሦስተኛ ዙር የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታውን ለማድረግ ከትናንት በስትያ ወደ ደቡብ አፍሪካ አቅንቷል። ከደቂቃዎች በፊትም ጨዋታውን በአሸናፊነት አገባዶ የመልሱን ጨዋታ አቅሎ ወጥቷል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ክፍት እና የግብ ሙከራዎች የበረከቱበት ነበር። በ5ኛው ደቂቃም አሳንዳ ምቹኑ በቀኝ የሳጥኑ ክፍል በመገኘት በረጅሙ የተላከላትን ኳስ ለመጠቀም በመጣር የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ በደቡብ አፍሪካ በኩል ሰንዝራ ለጥቂት ወጥቶባታል። ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያልቦዘኑት ኢትዮጵያዎች በሰከንዶች ልዩነት በአጥቂዋ እሙሽ ዳንኤል አማካኝነት የሰላ ጥቃት ልከዋል። በ13ኛው ደቂቃ ደግሞ የመስመር አጥቂዋ እየሩስ ወንድሙ ከራስ ሜዳ ከአምበሏ መሰረት ማሞ የተነሳውን ረጅም የቅጣት ምት ኳስ በሳጥን ውስጥ እርጋታ በተሞላበት ሁኔታ ተቆጣጥራ ቡድኗን መሪ አድርጋለች።
ባለሜዳዎቹ ግብ ካስተናገዱ በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረቶችን ሲያደርጉ ታይቷል። በተለይ ዳንኤላ ሴጋል ከቅጣት ምት እንዲሁም አንድሬሊ ሚቢ ከርቀት የሞከሯቸው ኳሶች ለግብ ዘቧ አበባ አጂቦ ፈታኝ ነበሩ። በኳስ ቁጥጥሩ በአጋማሹ ብልጫ የነበራቸው የአሠልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ ተጫዋቾች ያገኙትን መሪነት አስጠብቀው ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮዋቸውን አሳምረው የቀረቡት ደቡብ አፍሪካዎች በተሻለ ወደ ግብ ቢደርሱም በ57ኛው ደቂቃ በሰሩት ስህተት ሁለተኛ ግብ አስተናግደዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም የመሐል ተከላካዩዋ ንታንዶ ፋላ ወደ ኋላ የመለሰችውን ኳስ የግብ ዘቧ ሙሲማንጎ መቆጣጠር ተስኗት ኳስ የግብ መስመሩን አልፋለች።
በ65ኛው ደቂቃ ደግሞ ተቀይራ ወደ ሜዳ የገባችው ቁምነገር ካሣ የተከላካዮችን ስህተት እንዲሁም የግብ ጠባቂዋን መውጣት ተንተርሳ ድንቅ ግብ ልታስቆጥር ጥራ መክኖባታል። በቀሪ ደቂቃዎችም ባለሜዳዎቹ አንዳች ነገር ከሜዳ ይዞ ለመውጣት ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በጭማሪው ደቂቃ ግን ቁምነገር ለቡድኗ ሦስተኛ ጎል አስቆጥራ ጨዋታው ተጠናቋል።
በርከት ባሉ የሀገራችን ደጋፊዎች ሞራል የተጫወተው ብሔራዊ ቡድናችን ሚያዝያ 23 የመልሱን ጨዋታ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚያከናውን ይሆናል።