በአስራ ስምንተኛ የጨዋታ ሳምንት የተመለከትናቸው ዓበይት ክለብ ነክ ጉዳዮች እንደሚከተለው ይነበባሉ።
👉 የአርባምንጭ ከተማ የማጥቃት እና የመከላከል ሚዛን
በሊጉ ከከፍተኛ ሊግ መልስ ዳግም የመጀመሪያ የውድድር ዘመናቸውን እያሳለፉ የሚገኙት አርባምንጭ ከተማዎች ከጥንቃቄ መር አጨዋወት ወደ ማጥቃት አጨዋወት እያደረጉ ባሉት ሽግግር የቡድኑ የመከላከል ጥንካሬ እየሳሳ ይሆን ?
ቡድኑ በመጀመሪያ ዙር ባደረጋቸው አስራ አምስት ጨዋታዎች በስድስቱ ግብ ለማስቆጠር ሲቸገር ግብ ማስቆጠር በቻሉባቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች ደግሞ በሁለት ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን ማስመዝገብ ከቻሉባቸው ጨዋታዎች ውጪ ቡድኑ በሚልቁት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ በማስቆጠር ጨዋታቸውን ማጠናቀቅ ችሏል። ከሁለተኛው ዙር አንስቶ ግን ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች በድምሩ ስድስት ግቦችን ማስቆጠር ሲችል በተለይ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ፍፁም የተሻሻለውን የቡድኑን የማጥቃት ጨዋታ እየተመለከትን እንገኛለን።
በመከላከሉ ረገድም ጠንካራ የመከላከል መስመር ባለቤት የሆነው አርባምንጭ በመጀመሪያው ዙር በአራት ጨዋታዎች ግብ ሳያስተናግድ መውጣት የቻለ ሲሆን ግብ ባስተናገዱባቸው ጨዋታዎችም ከአንድ ግብ በላይ ተቆጥሮባቸው ያለማወቃቸው ጉዳይ ስለቡድኑ የጨዋታ አቀራረብ እና የመከላከል አወቃቀር ጥቅል ምስልን የሚሰጡ ቁጥሮች ናቸው። ታድያ በመጨረሻው የጨዋታ ሳምንት አራት ግቦችን በተለይ ደግሞ በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች ሦስት ግብ የማስተናገዳቸው ጉዳይ በድፍረት ማጥቃት መጀመራቸውን ተከትሎ የመከላከል ሚዛናቸው ላይ ጥያቄ እንድናነሳ የሚያስገድድ ነው።
አርባምንጭ በተለይ በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ከፍ ባለ ጫና ለመጫወት አለፍ ሲልም በቀጥተኛ አጨዋወት ተጋጣሚዎቹ ላይ ብልጫ ለመውሰድ ይታትር የነበረ ሲሆን ይህ የአጨዋወት ምርጫቸው ከፍ ያለ አካላዊ ዝግጁነት የሚጠይቅ እንደመሆኑ በተወሰነ መልኩ ይህን ሂደት ለማስቀጠል ተቸግረው የተመለከትን ሲሆን ለማሳያነትም ቡድኑ ሊጉ ተቋርጦ በተመለሰባቸው ሁለት አጋጣሚዎች የነበረውን መነቃቃት መመልከት በቂ ነው።
በሁለተኛው ዙር በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ በጠንካራ ሰራተኝነት የሚታወቁት የቡድኑ የአጥቂ መስመር ተሰላፊዎች ላይ ከጥራት ጋር በተያያዘ ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎች በአህመድ ሁሴን ዝውውር ውስጥ ምላሽ እንዳገኙ የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች በቂ ማሳያ ነበሩ። አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪም ከዚህ ቀደም ስለአቻ ውጤቶች ዋጋ በተደጋጋሚ ሲነገሩ ይደመጥ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ግብ ቢቆጠርበትም ከተጋጣሚው የበለጠ ግብ የሚያስቆጥር ቡድን ለመስራት እየሞከሩ እንደሆነ ሲናገሩ ይደመጣሉ። ቡድኑ ላይም ይህን የአስተሳሰብ ለውጥ እየተመለከትን እንገኛለን።
ይሁን እንጂ በዚህ ሂደት በተለይ በመጨረሻው የሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ ቡድኑ የተከላካይ መስመሩ ከወትሮው በጣሙን ሳስቶ ተመልክተናል። ለማጥቃት ያለ ቅጥ በድፍረት መጫወት መጀመሩ ቡድኑን በመከላከሉ ወቅት በጣም የተከፋፈተ እንዲሆን ያደረገው ሲሆን በዚህ ሂደትም በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ባልተለመደ መልኩ ሦስት ግቦችን አስተናግዶ ነጥብ ለመጋራት ተገዷል።
ከአንድ በላይ ግብ በጨዋታ አስተናግዶ የማያውቀው አርባምንጭ በሀዲያ ሆሳዕናው ጨዋታ አራት ግብ የማስተናገዱ ነገር እንዲሁም አዲስ አበባን በረቱበት ጨዋታ በተመሳሳይ በተጋጣሚው ሳይቀጣ ቀረ እንጂ እጅግ ጥራት ያላቸው ዕድሎችን ሲፈቅድ የማስተዋላችን ጉዳይ በማጥቃቱ ረገድ በእነዚህ ሁለት ጨዋታዎች ያሳዩት የሚበረታታ ድፍረትን ከሚዛናዊ መከላከል ጋር ማዋሀድ ካልቻሉ ጥረታቸው በዜሮ እንዳይባዛ ያሰጋል።
👉 ተስፋ ያልቆረጡት ሀዲያ ሆሳዕናዎች
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለሃያ አራት ዓመታት በዘለቀው የውድድር ዘመናት ታሪክ ውስጥ በግንባር ቀደምነት ከሚጠቀሱ የመጨረሻ ደቂቃ ድራማዊ ክስተትን ካስተናገዱ ጨዋታዎች መካከል ምናልባት ቀዳሚውን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ተመልክተናል።
በ18ኛ የጨዋታ ሳምንት መክፈቻ በነበረው ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ ሀዲያ ሆሳዕናን እስከ 80ኛው ደቂቃ 4-1 ሲመራ ቢቆይም በመጨረሻ ደቂቃዎች ዕብደት ሀዲያ ሆሳዕና ሦስት ግቦችን አስቆጥረው ጨዋታው 4-4 በሆነ አስገራሚ ውጤት ተጠናቋል።
በ54ኛው ደቂቃ አህመድ ሁሴን ባስቆጠራት ግብ በአርባምንጭ ከተማ 3-1 መመራት የጀመሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በ57ኛው ደቂቃ ወጣቱን ተከላካይ ቃለዓብ ውብሸትን እና አማካዩን እያሱ ታምሩን አስወጥተው በምተካቸው አጥቂውን ሀብታሙ ታደሰን እና አማካዩን ኤፍሬም ዘካርያስን የተኩባቸው ውሳኔዎች በውጤት ቅልበሳው ሂደት ከፍተኛ ሚና ነበራቸው።
በጨዋታው የተሻለ የማሸነፍ ግምት አግኝተው የነበሩት ሀዲያዎች ባልተጠበቀ መልኩ በአርባምንጭ ከተማ 4-1 የመመራታቸው ጉዳይ በተጫዋቾቹ አዕምሮ ላይ የሚፈጥረው ጫና ከባድ እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም ፤ ታድያ ተጫዋቾቹ በዚህ ጫና ውስጥ እንኳን ቢሆኑም እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ ውጤቱን መቀልበስ እንደሚቻል በማመን ያሳዩት አስደናቂ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በተለየ መልኩ ሙገሳ የሚገባው ነበር።
በ80ኛው ደቂቃ አከራካሪ የዳኝነት ውሳኔ በታየበት እንቅስቃሴ ተቀይሮ የገባው ሀብታሙ ታደሰ ባስቆጠራት ግብ 4-2 መሆን የቻሉት ሀዲያዎች ይህች ግብ ወደ ጨዋታው የመለሰቻቸው ነበረች ብሎ ማንሳት ይቻላል። በዚህች ግብ ዳግም የተነሳሱት ነብሮቹ ያለማቋረጥ አርባምንጭ ከተማዎች ላይ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል።
በዚህ ሂደት ሄኖክ አርፊጮ ማራኪ የነበረችውን ሦስተኛ ግብን በ88ኛው ደቂቃ ላይ ሲያስቆጥር በሀዲያ ሆሳዕና ተጫዋቾች ላይ እናስተውል የነበረው ውጤቱን መቀየር እንደሚችሉ ይበልጥ የማመን ነገር በመጨረሻም ፍሬ አፍርቷል። መደበኛው ደቂቃ ተጠናቆ በተጨመሩ ደቂቃዎች ላይ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ብርሃኑ በቀለ በግሩም ሁኔታ ከሳጥን ጠርዝ መሬት ለመሬት አክርሮ የመታት ኳስ ከመረብ ተዋህዳ ቡድኑ በ80ኛው ደቂቃ ላይ አርባምንጭ 4 ሀዲያ ሆሳዕና 1 ይል የነበረውን የውጤት መግለጫ ጨዋታው ሲጠናቀቅ ወደ 4-4 እንዲቀየር በማድረግ በሊጉ ለዘመናት የሚወሳ አስደናቂ ገድልን መፈፀም ችሏል።
👉 ጫና ውስጥ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና አሸንፏል
2014 የውድድር ዘመን ለኢትዮጵያ ቡና እጅግ ፈታኝ ሆኗል። ከሰሞኑ በተከታታይ አምስት ጨዋታዎች የደርቢውን አሰቃቂ ሽንፈትን ጨምሮ ውጤት ለማስመዝገብ ተቸግሮ የቆየው ቡድኑ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን ሰበታ ከተማን 2-0 በመርታት በተወሰነ መልኩ ተንፈስ ያለበትን ውጤት አስመዝግቧል።
በእንቅስቃሴ ረገድ እምብዛም አሳማኝ ያልነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ወሳኙን ነጥብ ግን ከጨዋታው ይዘው መውጣት ችለዋል። የአቡበከር ናስር የመጀመሪያ አጋማሽ እንዲሁም ሮቤል ተ/ሚካኤል በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠረው አስደናቂ ግብ ኢትዮጵያ ቡና በውድድር ዘመኑ የሰበሰውን የነጥብ ብዛትን ወደ 24 አድርሷል።
ከፍ ባለ ጫና ውስጥ የነበሩት አሰልጣኝ ካሳዬ እና ልጆቻቸው ከዚህ ስሜት ለመውጣት በየትኛውም መንገድ የሚገኝ ሦስት ነጥብ እጅግ አስፈላጊ የመሆኑ ነገር ጥያቄ የሚነሳበት አይደለም። ታድያ በዚህ ሂደት ተከታታይ አውንታዊ ውጤቶች መመዝገብ ሲጀምሩ ይበልጥ ከውጤት ባልተናነሰ ስለ እንቅስቃሴያቸው ማሰብ ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በቀጣይ የጨዋታ ሳምንት ወላይታ ድቻን የሚገጥመው ቡና ከድቻው ጨዋታ አስቀድሞ የራስ መተማመኑን ከፍ በማድረግ ረገድ ያስመዘገበው ውጤት ከፍ ያላ ድርሻ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
👉 ሲዳማ ቡና ወደ ዋንጫው ፉክክር እየገባ ይሆን ?
ሲዳማ ቡናዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚገኙት ሀዋሳ ከተማዎችን ማሸነፋቸውን ተከትሎ ነጥባቸውን ወደ 30 በማሳደግ ራሳቸውን ወደ ፉክክር ይበልጥ ያስጠጉበትን ውጤት አስመዝግበዋል።
በ7ኛ የጨዋታ ሳምንት በፋሲል ከነማ አሰቃቂ ሽንፈትን ካስተናገደ በኋላ ባደረጋቸው አስራ አንድ ጨዋታዎች ምንም ዓይነት ሽንፈትን ያለተጎነጨው ሲዳማ ቡና በስድስቱ ጨዋታዎች ድል ሲያደርግ በአምስቱ ደግሞ አቻ ተለያይቷል።
ከእነዚህ ጨዋታዎች ውስጥ በተለይም አቻ የተለያዩባቸውን ጨዋታዎች ወደ ድል መቀየር ቢችሉ ኖሮ በሰንጠረዡ ከዚህ በላይ ገፍተው በተቀመጡ ነበር። በተለይ በመከላከሉ ካለው ጥንካሬ ባለፈ ግቦችን በማስቆጠር ረገድ የሊጉ ሁለተኛ ከፍተኛ አስቆጣሪ በሆነው ይገዙ ቦጋለ ላይ ጥገኛ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ግን በሊጉ ባለፉት 20 ዓመታት ከተመለከትናቸው ዕድሎችን ወደ ግብነት በመቀየር ረገድ ወደር የማይገኝለትን ሰልሀዲን ሰዒድን ማስፈረማቸው የቡድኑ የማግባት ኃላፊነት ወደ ተለያዩ ተጫዋቾች በማሰራጨት ረገድ ሲዳማን ይበልጥ ያግዛል ተብሎ ይጠበቃል።
አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ከሀዋሳው ጨዋታ አስቀድሞ በነበራቸው ቅድመ ጨዋታ ቃለ መጠይቅ እንደተናገሩት የሊጉ አሁናዊ የደረጃ ሰንጠረዥን ተመልክቶ ድምዳሜ መስጠት አስቸጋሪ ስለመሆኑ ያነሱ ሲሆን ቡድናቸው መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ መድረስ እንደሚችልም በልበ ሙሉነት ሲናገሩ ተደምጠዋል።
አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሲዳማ ቡና በሰንጠረዡ ከአናቱ ከሚገኙት አራት ቡድኖች ሁለቱ ነጥብ መጣላቸውን ተከትሎ በሁለተኛ ደረጃ ከሚገኘው ወላይታ ድቻ ጋር ያላቸው ነጥብ ወደ ሁለት የጠበበ ሲሆን ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ በ10 ነጥብ ርቀው ይገኛሉ።
ሁለቱ ቡድኖች በ20ኛው የጨዋታ ሳምንት እንደመገናኘታቸው ሲዳማ ቡና በቀጣይ በሊጉ የዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚኖረውን ድርሻ የሚወስን ጨዋታ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
👉 ድልን አጥብቀው የሚሹት አዳማ እና ባህር ዳር
18ኛ ሳምንቱ ላይ በደረሰው የሊጉ ውድድር በሚፈለገው ደረጃ ውጤት ማስመዝገብ ካልቻሉ ቡድኖች መካከል የአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኙ አዳማ ከተማ እና የአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱው ባህር ዳር ከተማ (ምንም እንኳን በወልቂጤ ከተማ የተጫዋቾች ቅያሪ ስህተት ምክንያት ፎርፌ ቢያገኙም) ከቀዳሚዎቹ ተርታ ይመደባሉ።
በ24 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት አዳማ ከተማዎች ምንም ሽንፈት ካላስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጥሎ ከሲዳማ ቡና ዕኩል ሁለት ጨዋታዎችን ብቻ በመሸነፍ ጥሩ ቁጥር አስመዝግበዋል። በሌላ ጎኑ አዳማ ድል ያደረጋቸው የጨዋታ ብዛት (4) ደግሞ በወራጅ ቀጠናው ከተቀመጡት ሁለት ክለቦች ቀጥሎ በሊጉ ዝቅተኛ የጨዋታ ቁጥር ካሸነፉ ሁለት ክለቦች ጋር በጣምራ ሦስተኛው አነስተኛ የድል መጠን ያስመዘገበው ቡድን ያደርገዋል።
ከዚህ ባለፈ አዳማ ከተማ 12 ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት በመፈፀም በሊጉ ከፍተኛውን የጨዋታ ብዛት አስመዝግቧል። ይባስ ብሎ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት ባደረጋቸው የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች በሙሉ አቻ የመለያየቱ ጉዳይ በነቂስ ወደ ሜዳ መጥቶ እያበረታታቸው ለሚገኘው የክለቡ ደጋፊ የሚዋጥ አይመስልም። አዳማ በብዙ ጨዋታዎች አለመሸነፉ በራሱ በመልካምነቱ የሚነሳ ቢሆንም በድል መታጀብ ካልቻለ ግን በሊጉ ከመቆየት ባለፈ ውጥን ላለው ክለቡ አስደሳች የሚባል አይደለም
በተመሳሳይ ባህር ዳር ከተማዎችም ወደ ዘንድሮው የውድድር ዘመን ሲገቡ በሰንጠረዡ አናት ስለመፎካከር አለፍ ሲልም የአፍሪካ ተሳትፎን አልመው ቢጀምሩም አሁን ላይ በ24 ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። (የዛሬውን የፎርፌ ውጤት ተከትሎ)
በ8ኛ የጨዋታ ሳምንት ከፋሲል ከተማ ጋር ያለ ግብ አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ አንስቶ ካደረጓቸው አስር ጨዋታዎች መካከል በአንዱ ብቻ ድል ሲቀናቸው በአራቱ አቻ እንዲሁም በተቀሩት አራቱ ደግሞ ተሸንፈው በዚህኛው ሳምንት ነጥብ የተጋሩበት ጨዋታ በፎርፌ ሙሉ ነጥብ አስገኝቶላቸውል። ከዚህ መነሻነት ሲታይም የቡድኑ ወቅታዊ አቋም ይጠበቅ ከነበረበት የተፎካካሪነት ደረጃ አንፃር ሲመዘን እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በመሆኑም ሁለቱ ቡድኖች ከምንም በላይ በቀጣይ ጨዋታዎች ድሎችን በማስመዝገብ ከዚህ አስከፊ ግስጋሴ መላቀቅ ካልቻሉ በሰንጠረዡ አጋማሽ ለመቅረት እንዲገደዱ እንዳያደርጋቸው ያሰጋቸዋል።