ወልቂጤ ከተማ ወዴት እያመራ ነው ?

በክለብ እና በቡድን አስተዳደር ጉዳዮች ከሰሞኑ በርካታ ጥያቄዎች ውስጥ የሆነው ወልቂጤ ከተማን የተመለከተ ጥንቅራችን በዚህ መልክ ተሰናድቷል።

በቅርብ ዓመታት ከጨዋታ ውጪ ክለቦችን የተመለከቱ ዜናዎች ሲወጡ የፋይናንስ ችግር እና እሱን ተከትለው የሚከሰቱት የተጨዋቾች ልምምድ ማቆም እንዲሁም መሰል ጉዳዮች ለአንባቢም አሰልቺ ከመሆን አልፈው መደጋገማቸው የችግሩን ስፋት ሲያደበዝዙት ይታያል። በፕሪምየር ሊጉ ህልውናቸውን በከተማ አስተዳደሮች ስር ያደረጉ ክለቦች በቁጥር በርካታ ሲሆኑ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የፋይናንስ ዕጥረት ገበናቸው ተጋልጦ መውጣት ከጀመረ ውሎ አድሯል። በእርግጥ ክለቦቹ የሁሉንም ትኩሩት የሚስበው እና ውጤቱ ሜዳ ላይ የሚታየው የተጨዋቾች ልምምድ ማቆምን ጉዳይ በብዙ ሩጫዎች በሚደረጉ ጊዜያዊ መፍትሄዎች ሸፍነው ማለፍን አማራጭ አድርገው እዚህ ደርሰዋል። ይኸው የፋይናንስ ችግር ግን አሁንም ወደ ፕሮፌሽናል ተቋምነት ለመቀየር ረጅም መንገድ የሚጠብቃቸው ክለቦቻችንን እስትንፋስ መፈታተኑን ቀጥሏል።

በዚህ ችግር ማዕበል ደጋግመው ሲመቱ ከቆዩ ክለቦች ውስጥ አንዱ ወልቂጤ ከተማ ነው። እርግጥ ነው በክለቦች ውስጥ የፋይናንስ ችግሮችን ተከትለው የሚመጡ መዘዞች ሜዳ ላይ ሲንፀባረቁ ይታይ እንጂ የወልቂጤ ከተማ ከዚህ ለየት ያለ ነው። በመጨረሻ አምስት ጨዋታዎቹ አንድ ጊዜ ብቻ ሽንፈት ያገኘው ወልቂጤ በደረጃ ሰንጠረዡ 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ስንመለከተው (ከፎርፌው ውሳኔ በፊት) ስር የሰደዱ አስተዳደራዊ ችግሮች ላይ ስለመሆኑ ምልክት አይሰጠንም። ሆኖም ባሳለፍነው ሳምንት ከሜዳ ውጪ እየተፈጠሩ ያሉ ጉዳዮች ከዚህ የተለዩ ሆነው እናገኛቸዋለን።

በሌሎች ክለቦች ላይ እንደሚታየው የክለቦች ውጪ እና ገቢን አለመመጣጠን ተከትሎ ደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅምን እንዲሁም ውድድርን ተከትሎ የሚመጡ የጉዞ እና የሆቴል ወጪዎችን መሸፈን ከክለብ አመራሮች አቅም በላይ ይሆናል። ስለዚህም ተጨማሪ የበጀት ድጋፍ ለማግኘት የክለብ አመራሮች እና የከተማ አስረዳደር ኃላፊዎች ተቀራርበው በመስራት ነገሮችን ለማስተካከል ሲጥሩ ይታያል። የወልቂጤ ከተማን አሁናዊ ችግር ለየት የሚያደርገው ግን በሁለቱ አካላት መካከል ያለው ግንኙነት ተመሳሳይ መፍትሄ ለመፍለግ የሚያበቃ ደረጃ ላይ አለመሆኑ ነው። ለዚህም የክለቡ ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ አበባው ሰለሞን ፣ የክለቡ ቦርድ ፀኃፊ አቶ ጌቱ ደጉ እንዲሁም የቦርድ አባሉ እና የደጋፊዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ከማል ጀሚል በጋራ ከመጋቢት 28 ጀምሮ ሥራ ማቆማቸውን አስመልክቶ ለወልቂጤ ከተማ አስተዳደር እና ለጉራጌ ዞን አስተዳደር የፃፉት ደብዳቤ ማሳያ ይሆናል።

ብዙ ዝርዝር ያለው የኃላፊዎቹ ደብዳቤ በክለቡ ሥራ አስፈፃሚ እና በፖለቲካ አመራሩ መካከል ያለውን መቃቃር የሚጠቁም ነበር። በዚህም ከ2013 ከጋማሽ ጀምሮ ክለቡ እየገጠመው ላለው የፋይናንስ ችግር ከከተማ እና ከዞኑ እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ጊዜያዊ መፍትሄ በማፈላለግ እንደቆዩ ገልፀዋል። ኃላፊዎቹ ወልቂጤ ከሌሎች አቻ የከተማ አስተዳደር ክለቦች በግማሽ ባነሰ በጀት እየተንቀሳቀሰ (እነርሱ እንዳሉት) ጉድለቱን ለመሙላት የሚደረገው ጥረት በሂደት ለሥራ አስፈፃሚው ብቻ እንደተተወ አንስተዋል። ከበጀት ጉዳዮች ውጪ በአስተዳደራዊ ሰነዶች አዘገጃጀት ፣ ክለቡን በራሱ እንዲቆም በሚደረጉ ጥረቶች እና ሌሎች ጉዳዮች ጋርም ተያይዞ ከፖለቲካ አመራሩ ጋር ልዩነቶች እንዳሏቸው ያነሱት ሦስቱ የሥራ አስፈፃሚ ኃላፊዎች ይህንኑ የሚያጠናክሩ ሰባት ዝርዝር ምክንያቶችን በማስቀመጥ ችግሮች መፍትሄ አልባ እየሆኑ ክለቡን ወደመፍረስ እያመሩት በመሆኑ ሥራቸውን ማቆማቸውን አስቀምጠዋል።

የደብዳቤው ኃሳብ በክለቡ የነበረው ችግር ከኃላፊዎቹ ሥራ መልቀቅ በፊት ስር የሰደደ መሆኑን የሚነግረን ቢሆንም መሰል ውሳኔዎች ሲመጡ ሜዳ ላይም ሆነ ከሜዳ ውጪ የሚፈጥሩት መንፈስ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይሆንም። ነገር ግን ሜዳ ላይ ቡድኑ ከዚህ ውሳኔ በኋላ ሁለት ጨዋታዎችን አድርጎ አራት ነጥቦችን አሳክቷል። ሆኖም ከውጤት ባለፈ በሁለቱም ተጋጣሚዎቹ ከቡድን አስተዳደር ጋር የተያያዙ ክሶችን አስተናግዷል። የመጀመሪያው እና ከፋሲል ከነማ የመጣበትን ከዝውውር ጋር የተያያዘ ጥያቄ ማለፍ ቢችልም ትናንት ምሽት በባህር ዳር የተነሳበት የተጫዋቾች ቅያሪ ክስ ግን ወደ ፎርፌ ቅጣት አምርቶበታል።

እነዚህ ነገሮች ከክስነት ባለፈ የአስተዳደራዊ ችግሮች ትኩሳት ወደ ቡድኑ እየደረሱ ስለመሆነቸው ጠቋሚ መሆናቸው ግን እሙን ነው። ለዚህ አንዱ መሳያ የሚሆነው ባሳለፍነው ማክሰኞ የቡድኑ 30 ተጫዋቾች የደመወዝ እና ጥቅማጥቅም ጉዳዮችን አስመልክተው ያስገቡት ደብዳቤ ነው። ተጫዋቾቹ በደብዳቤያቸው ‘የክለቡን አሰራር በማይረብሽ መልኩ ጥያቄያችንን በትዕግስት ስናቀርብ ብንቆይም ምላሽ ባለማግኘታችን ከመጪው አርብ ጀምሮ ልምምድ ለማቆም እንገደዳለን’ ብለው የነበረ ሲሆን ዛሬ ለማጣራት እንደሞከርነው የተወሰኑ ተጫዋቾች ወደ መኖሪያ ከተማቸው መመለስ መጀመራቸውን አውቀናል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ስማቸው እንዲገለፅ ካልፈለጉ የቡድኑ አባላት እንደሰማነው የቡድኑ ሰሞንኛ መንፈስ ሜዳ ላይ ከሚታየው በተቃራኒ እንደሆነ ፣ በአዳማ ከተማ ያረፉበት ሆቴልም ክለቡ ዕዳውን ባለመክፈሉ ከዛሬ ቁርስ በኋላ እንደማያስተናግዳቸው እንደገለፀላቸው ነግረውናል። የቡድኑ አባለት ከዛሬ ጀምሮ ልምምድ እንዳቆሙ ሲያረጋግጡልን እየተበትኑ መሆናቸው ደግሞ በቀጣዩ የሀዋሳ ከተማ ጨዋታ ላይ ወልቂጤ ከተማ ሜዳ ላይ መገኘቱን ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል።

ከአጠቃላይ የክለቡ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታምራት ታዬ ራሳቸውን ከሥራ ያነሱት ኃላፊዎችን ጥያቄዎች ክለቡ ለብቻው መመለስ የማይችል ባለመሆኑ ለዞኑ መንግስትና በአጠቃላይ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በሙሉ በማሳወቅ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ነግረውናል። ” በመሠረቱ ክለቡ ዕጣ ፈንታው ምንድነው ብሎ ለማለት ችግር የሆነው አሁን አይደለም። በጣም ብዙ ችግሮችን በቦርድ አባላት ኮሚትመንት በመታገዝ ነበር እስከአሁን መዝለቅ የቻለው አሁን ግን በዚህ መልክ መቀጠል ከባድ በመሆኑ ነው እዚህ ደረጃ የደረሰው” የሚለው የሥራ አስኪያጁ ሀሳብም የክለቡ ወቅታዊ ሁኔታ ስላለበት ደረጃ የሚጠቁም ነው።

በ2002 ምስረታውን ያደረገው ወልቂጤ ከተማ በአስር ዓመታት ውስጥ በሀገሪቱ ትልቁ የክለቦች ውድድር ላይ መሳተፍ ችሏል። ባሳለፍነው ዓመት ከሊጉ የሚያወርደውን ውጤት አስመዝግቦ የትግራይ ክለቦችን ለመተካት የተደረገውን ውድድር ተጠቅሞ ወደ ሊጉ ተመልሷል። ዘንድሮስ እስካሁን ከሰንጠረዡ አጋማሽ በላይ ሆኖ እየተፎካከረ ያለበትን አካሄድ ከሜዳ ውጪ ያሉ ጉዳዮች ያፋልሱበት ይሆን ?

ክለቡ ያለበት ወቅታዊ ሁኔታ በአመዛኙ ወይንም ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል ሁኔታ የበላይ አስተዳደሩን የመፍትሄ ሀሳብ የሚጠይቅ ነው። ይህንን ለማጣራትም የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ እንዳለ ገ/መስቀል እና የከተማው የወጣቶች እና ስፖርት ፅ/ቤት ኃላፊ እና የክለቡ ፕሬዘዳንት ወይዘሮ እፀገነት ፍቃዱ ጋር ደጋግመን በመደወል ልናገኛቸው ብንሞክር ሳይሳካልን ቀርቷል። ከዚህ በኋላም በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸውን ሀሳብ ለማስተናገድ በራችን ክፍት እንደሆነ ለመግለፅ እንወዳለን።

ያጋሩ