የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

ሁለተኛው የዐበይት ጉዳዮች ትኩረታችን በጨዋታ ሳምንቱ ትኩረት የሳቡ ተጫዋቾች ላይ ያተኮረ ይሆናል።

👉 ጉራማይሌ የጨዋታ ዕለት ያሳለፈው አህመድ ሁሴን

በውድድር ዘመኑ አጋማሽ የዝውውር መስኮት አርባምንጭ ከተማን የተቀላቀለው አህመድ ሁሴን ቡድኑ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር 4-4 በተለያየበት ጨዋታ ሀት-ትሪክ መስራት አና አንድ ግብ ማመቻቸት ቢችልም ደስታውን በሚገባ ሳያጣጥም ለወራት ከሜዳ የሚያርቅ ጉዳት አስተናግዶ ከሜዳ ወጥቷል።

በ2011 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በወልቂጤ ከተማ መለያ ከስንታየሁ መንግሥቱ ጋር ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆኑ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ማደግ የቻለው ተጫዋቹ ከወልቂጤ ከተማ ጋር ቀሪ የስድስት ወር ውሉን በማቋረጥ ወደ አርባምንጭ ከተማ ማምራቱ አይዘነጋም።

በአርባምንጭ ከተማ መለያ ባደረጋቸው የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች በተለይም በሁለተኛው ጨዋታ ጥሩ መንቀሳቀስ የቻለው አህመድ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ሦስተኛ ጨዋታውን አድርጎ በጨዋታው ሀት-ትሪክ መስራት ሲችል ፀጋዬ አበራ ያስቆጠራትን ሌላ ግብ አመቻችቷል። የአስደናቂ ፍጥነት ባለቤት የሆነው አህመድ ሁሴን ግብ ለማስቆጠር በሚረዱ ቦታዎች ላይ በመገኘት ረገድ ጥያቄ ባይነሳበትም የመጨረሻ ውሳኔዎቹ ግን በአብዛኛው አንገት የሚያስደፉ ሲሆኑ ተመልክተናል።

ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ቡድኑ ነጥብ ሲጋራ ሦስቱንም ግቦች ሲያስቆጥር የተገኘባቸው ቦታዎቹ ሆነ ውሳኔዎቹ አስደናቂ ነበሩ። ታድያ ሦስት ግቦችን ማስቆጠር የቻለው ተጫዋቹ 72ኛው ደቂቃ ላይ ለአየር ኳስ ከፍሬዘር ካሳ ባደረገው ፍልሚያ ወቅት ባስተናገደው ጉዳት በአምቡላንስ ለተሻለ ህክምና ወደ ሆስፒታል ማምራቱ ተጫዋቹን ዕድለ ቢስ ያሰኘዋል።

በገጠመው ጉዳት ሁለት ወራት ለሚጠጋ ጊዜ ከሜዳ የሚርቀው አህመድ ከእሱ መምጣት በኋላ በተወሰነ መልኩ ለተነቃቃው የአርባምንጭ ከተማ ማጥቃት ትልቅ ዕጦት ይሆናል ተብሎ ይታመናል።

👉 ግብ አስቆጣሪው ፍሪምፖንግ ሜንሱ

ጋናዊው የመሀል ተከላካይ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመጣበት 2011 የውድድር ዘመን አንስቶ በግራ መስመር ተከላካይነት እና በመሀል ተከላካይነት እጅግ ድንቅ የሚባልን ግልጋሎት በወጥነት ለቡድኑ እየሰጠ ይገኛል።

በተለይ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ሁለተኛው ዙር ከተጀመረ ወዲህ ቡድኑ ባደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች አራት ግቦችን በማስቆጠር የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው እስማኤል ኦሮ-አጎሮ ባይኖርም የእሱን ክፍተት በሚገባ በመድፈን ላይ ይገኛል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ እስካሁን ባደረጋቸው ጨዋታዎች አንድ የጨዋታ ደቂቃ ብቻ ያመለጠው ተጫዋቹ ቡድኑ ድሬዳዋ ከተማን ሲረታ እጅግ ወሳኝ የሆኑትን የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ግቦችን ከመረብ በማዋሀድ ለቡድኑ አለኝታነቱን አሳይቷል። በተለይም ከቆመ ኳስ በቀጥታ ያስቆጠራት አስደናቂ ግብ የተጫዋቹን የቴክኒክ ክህሎት በሚገባ ያሳየች ግብ ነበረች።
ፍሪምፖንግ በመከላከሉ ካለው አስደናቂ አበርክቶ ባለፈ ተጫዋቹ የቆሙ ኳሶችን በማጥቃት ሆነ በመከላከል ረገድ ያለው አበርክቶ የላቀ ነው ለዚህም ያስቆጠራቸው ሦስት ግቦች አብነት ናቸው።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ከሱፐር ስፖርት ጋር ቆይታ የነበረው ተጫዋቹ በግብ ማስቆጠር ረገድ ስላሳየው መሻሻል ሚስጥር ሲናገር የራሱ የግል ጥረት እና ከአሰልጣኝ ቡድን አባላት እያገኘ የሚገኘው ማበረታቻን በምክንያትነት ያቀረበ ሲሆን አያይዞም በቀልድ መልክ ለጊዜው ከቡድኑ ጋር የማይገኘው አጥቂው ኦሮ-አጎሮ ወደ ቡድኑ ሲመለስ ተክቶት እያበረከተ ለሚገኘው የግብ ማስቆጠር ውለታ ሊክሰው እንደሚገባም አንስቷል።

👉 ለኢትዮጵያ ቡና ውለታ የዋለው በረከት አማረ

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ኢትዮጵያ ቡና ሰበታ ከተማን በመርታት ከአምስት ጨዋታ በኋላ ድል ባስመዘገበበት ጨዋታ የግብ ጠባቂው በረከት አማረ ድርሻ የጎላ ነበር።

በጨዋታው አቤል ማሞን ተክቶ በቋሚዎቹ መካከል የጀመረው በረከት በጨዋታው በተለይ በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች የጨዋታውን መልክ ሊቀይሩ ይችሉ የነበሩ ሦስት አደገኛ አጋጣሚዎችን በሚገርም ብቃት በማዳን ቡድኑን በጨዋታ ማቆየት የቻለ ሲሆን በተጨማሪነትም ሰበታ ከተማ የተሻሉ በነበረባቸው ደቂቃዎች ያደረጓቸው ሙከራዎች በማዳን ረገድ እጅግ ስኬታማ ነበር። አስገራሚ መልኩ ኳሶችን ከማዳን ባለፈ ከተከላካይ ጀርባ የሚከፈቱ ሜዳዎችን ለመከላከል ያለው ንቃት እና የኳስ ስርጭቶቹም ጥሩ የሚባሉ ነበሩ።

በዘንድሮው የውድድር ዘመን የሰበታ ከተማውን ጨዋታ ጨምሮ በአራት ጨዋታዎች የቡድኑን ግብ መጠበቅ የቻለው በረከት በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች እጅግ ድንቅ ጊዜያትን ማሳለፍ ችሏል። በመሆኑም በደርቢው አራት ግቦችን ማስተናገዱን ተከትሎ ወደ ተጠባባቂ ወንበር የወረደውን አቤል ማሞን በቀጣይ ጨዋታዎች በአስተማማኝነት ሊተካ እንደሚችል በቂ ማረጋገጫን መስጠትም ችሏል።

👉 ሪችሞንድ አዶንጎ ዕድሎችን ከማምከን ወደ ማስቆጠር

አዲስ አበባ ከተማ መከላከያን በመርታት ከወራጅ ቀጠናው ለጊዜውም ቢሆን የራቀበትን ውጤት ሲያስመዘግብ በጨዋታው የቡድኑን ሁለት ማሸነፊያ ግቦችን ማስቆጠር የቻለው ጋናዊው ሪችሞንድ አዶንጎ ነበር።

ከጥቂት የጨዋታ ሳምንታት በፊት በአሰልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ ጭምር ቡድኑን ለማገዝ ካለው ከፍተኛ ፍላጎት መነሻነት በርካታ ዕድሎችን እንደሚያመክን የተነገረለት ሪችሞንድ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ ወዲህ ከሚያስቆጥራቸው ኳሶች ይልቅ የሚያመክናቸው ፀጉር የሚያስነጩ የግብ አጋጣሚዎች መገለጫዎቹ ነበሩ።

ነገር ግን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን አንድ በሊጉ የመጫወት ልምድ እንዳለው ተጫዋች ቡድኑ የእሱን ግልጋሎት በሚፈልገበት በዚህ ወቅት ሁለት እጅግ ወሳኝ ሚና ያላቸውን ግቦች ማስቆጠር መቻሉ የሚያስወድሰው ሲሆን በቀጣይም ቡድኑ በሊጉ ለመቆየት በሚያድርገው ጥረት ውስጥ የሪችሞንድን መሰል ብቃቶችን ይሻል።

👉 ሱራፌል ዐወል – እስካሁን የት ነበር ?

ጅማ አባ ጅፋር በፋሲል ከነማ በመጨረሻ ደቂቃ ባስተናገዱት ግብ በተሸነፉበት ጨዋታ እንደ ቡድን ጥሩ ጥረት ሲያደርግ ከነበረው የጅማ አባ ጅፋር ስብስብ ውስጥ በጨዋታው በግራ መስመር ተከላካይነት የተሰለፈው ሱራፌል ዐወል ያደረገው ጥረት አድናቆት የሚቸረው ነበር።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በ85ኛው ደቂቃ በቤካም አብደላ ተቀይሮ የወጣበትን ሳይጨምር በዘንድሮው የውድድር ዘመን በድምሩ በስድስት ጨዋታዎች (ሁለት በቋሚነት እንዲሁም አራት ተቀይሮ በመግባት) ተሳትፎ ማድረግ የቻለው ተፈጥሮአዊ የአማካይ መስመር ተጫዋቹ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ባልተለመደ መልኩ በግራ የመስመር ተከላካይነት ተሰልፎ ሲጫወት ተመልክተናል።

እምብዛም በዘንድሮው የውድድር ዘመን የመሰለፍ ዕድልን ማግኘት ያልቻለው ተጫዋቹ በፋሲል ከተማው ጨዋታ በመከላከሉ የተጋጣሚን ጠንካራውን የቀኝ ወገን በመቆጣጠር ረገድ እጅግ የተሳካ ጊዜያትን ያሳለፈ ሲሆን በማጥቃቱ ረገድም አንድ ለግብ የሆነ ኳስ ከማቀበል ባለፈ በጣም የተዋጣለት እንቅስቃሴ ሲያደርግ ነበር።

በርከት ባሉ ጨዋታዎች በተለያዩ ምክንያቶች ከአሰላለፍ ውጪ ሆኖ የከረመው ሱራፌል ዐወል ዳግም ወደ አሰላለፍ በመጣበት ጨዋታ ያሳየው ብቃት እስከዛሬ ለምን በቋሚ አሰላለፍ አልጀመረም ብለን ጥያቄ እንድናነሳ የሚያስገድድ አጋጣሚ ነበር።

👉 ጫላ ተሺታ ወደ ቀድሞ ብቃቱ እየተመለሰ ይመስላል

ወጣቱ የመስመር አጥቂ ጫላ ተሺታ በወልቂጤ ከተማ በተለይ በተሰረዘው የ2012 የውድድር ዘመን እጅግ ድንቅ የሚባል ጊዜን ማሳለፍ ችሏል ፤ አሁን ላይም እነዚያን ጊዜያት ለመመለስ ተጫዋቹ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል።

በ2008 በአሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ ይመራ በነበረው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ደምቀው ከወጡ ተጫዋቾች አንዱ የነበረው ጫላ ተሺታ በፕሪሚየር ሊጉ ራሱን በሲዳማ ቡና መለያ ማስተዋወቅ ችሏል።

እምብዛም ውጤታማ ካልነበረው የሲዳማ ቡና ቆይታ በኋላ ወደ ወልቂጤ ከተማ ያመራው ተጫዋቹ በተሰረዘው የ2012 የውድድር ዘመን እጅግ አስደናቂ ጊዜያትን ማሳለፍ የቻለ ሲሆን በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ግን ወደ ሲዳማ ቡና የሚመልሰውን ዝውውር ቢፈፅምም ቆይታው በጉዳት እና ሌሎች ጉዳዮች በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ አልነበረም።

ዘንድሮ ዳግም ወደ ደመቀበት ወልቂጤ ቤት የተመለሰው ተጫዋቹ በተለይ በሁለተኛ ዙር እያሳየ የሚገኘው እንቅስቃሴ የቀድሞውን ጫላ ተሺታን የሚያስተውሱ ናቸው። 18ኛ የጨዋታ ሳምንትን ጨምሮ በ14 ጨዋታዎች ለ1090 ያክል ደቂቃዎች ቡድኑን ማገልገል የቻለው ጫላ በመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ያስቆጠራቸውን ሁለት ግቦችን ጨምሮ በድምሩ ለቡድኑ አራት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። (የትናንቱ ግብ የጨዋታው ውጤት እንዲሰረዝ በመወሰኑ አይቆጠርም)

ከጉዳት የፀዳ የውድድር ዘመን እያሳለፈ የሚገኘው ተጫዋቹ ለአሰልጣኝ ተመስገን ዳናው ስብስብ በተለይ ከኳስ ውጪ ያለው ታታሪነት ሆነ ለፈጣን የማጥቃት ሽግግር የተመቸ ተጫዋች መሆኑ ይበልጥ የተመቸ ተጫዋች አድርጎታል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ከሱፐር ስፖርት ጋር ቆይታ የነበረው ጫላ ተሺታ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም ወደ ቀደመ ብቃቱ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ተናግሯል።

👉 ሮበርት ኦዶንካራ ተመልሷል

በ2003 የውድድር ዘመን በቅዱስ ጊዮርጊስ መለያ ለ16 ተከታታይ ጨዋታዎች ያህል ግቡን ባለማስደፈር ክብረ ወሰን ያስመዘገበው ዩጋንዳዊው ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ ዳግም ወደ ሊጋችን ተመልሶ የመጀመሪያውን ጨዋታ አድርጓል።

በእግርኳሳችን ከታዩ ምርጥ የውጪ ሀገር ዜግነት ያለው ግብ ጠባቂ እንደሆነ የሚነገርለት ሮበርት ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ ከተማ ቀጥሎ ወደ ወልቂጤ ለማምራት ከሳምንታት በፊት የተስማማ ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ሁለት አቻ በተለያየበት ጨዋታ የመጀመሪያ ጨዋታውን ለአዲሱ ክለቡ አድርጓል።

ምንም እንኳን ሁለት ግቦችን በማስተናገድ የመጀመሪያ ጨዋታውን ቢፈፅምም ሮበርት ኦዶንካራ በቀጣይ ጨዋታዎች ከሰሞኑ ጥሩ ብቃት ላይ ይገኝ ከነበረው ሰዒድ ሀብታሙ ጋር ለመጀመሪያ ተመራጭነት ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

👉የሮቤል ተክለሚካኤል ድንቅ ግብ

ወጣ ገባ መልክ በተላበሰው የኢትዮጵያ ቡና የውድድር ዘመን ጉዞ ውስጥ ብቸኛው ተስፋ ሰጪ ነገር የሮቤል ተክለሚካኤል ብቃት ነው ብንል ማጋነን አይሆንም።

ኤርትራዊው አማካይ በዘንድሮው የሊጉ ውድድር በኢትዮጵያ ቡና ከሳጥን ሳጥን አማካይነት እያሳየ የሚገኘው ብቃት እጅግ የተለየ ነው። አማካዩ በመከላከል ወቅት ወደ ኋላ ተስቦ ከአማኑኤል ዮሐንስ ጋር በመሆን ለቡድኑ መከላከል ደጀን በመሆን ሆነ የተጋጣሚን ማጥቃት ከመነሻው በማቋረጥ ረገድ ባልተቀናጀው ቡድን ውስጥ በግሉ የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው። በማጥቃቱም ተጫዋቹ በአጫጭር ቅብብሎች ተጋጣሚን ለማስከፈት በሚቸገርበት ወቅት በግሉ ያለውን አስደናቂ ረጃጅም ኳሶች የማቀበል ብቃቱን ተጠቅሞ ለቡድኑ ማጥቃት ሌላ አማራጭ ሲፈጥር እንመለከታለን።

አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በስብሳቸው ካሉት አማካዮች ሁሉ የተለየ ሁለገብነት እና ታታሪነትን የተላበሰው አማካዩ በዚህኛው የጨዋታ ደግሞ እጅግ አስደናቂ የነበረች ምናልባትም የውድድር ዘመኑ ምርጥ ግብ ከመሀል ሜዳ በቀጥታ አክርሮ በመምታት ማስቆጠር ችሏል።

ሮቤል በዝምታ ውስጥ አሁንም አስደናቂ ብቃቱን እያሳየ የሚገኝ ሲሆን በዚህኛው ጨዋታ ያስቆጠረው ግብ ደግሞ የተጫዋቾችን የአዕምሮ ፍጥነት እና ብስለቱም ይበልጥ ያሳየን አጋጣሚ ነበር።