የአባቱን መንገድ እየተከተለ የሚገኘው ግብ አስቆጣሪው የፈረሰኞቹ የኋላ ደጀን ፍሪምፖንግ ሜንሱ

👉 “አንዳንድ ጊዜ ቁጭ ብዬ 18 ጨዋታዎችን አለመሸነፋችንን ሳስበው ለራሴ አላምንም”

👉 “አባቴ የቀድሞ እግር ኳስ ተጫዋች ነበር”

👉 “ዋና ኃላፊነቴ ከሆነው መከላከል በተጨማሪ ግቦችንም ማስቆጠሬ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው”

👉 “በዚህ ዓመት እያሳየው ያለሁት ብቃት ከሞላ ጎደል ጥሩ ነው”

የዘንድሮ የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ጅማሮውን በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በማድረግ በድሬዳዋ ዘልቆ በአሁኑ ሰዓት በአዳማ ሳይንስ አና ቴክኖሎጂ ስታዲየም እየተደረገ ይገኛል። ሞቅ ብሎ በቀጠለው ሊግም በርካታ ተጫዋቾች ከሳምንት ሳምንት ምርጥ ብቃት በማሳየት እየተጫወቱ ሲሆን በአንፃራዊነት ከመጀመሪያው ሳምንት አንስቶ እስከ 18ኛ ሳምንት ደረስ በወጥነት ለቡድናቸው ግልጋሎት ከሰጡ ተጫዋቾች መካከል ግንባር ቀደሙ የቅዱስ ጊዮርጊሱ የመሐል ተከላካይ ፍሪምፖንግ ሜንሱ ነው። በሊጉ ቅዱስ ጊዮርጊስ 11 ጊዜ ግቡን እንዳያስደፍር ከአጣማሪው ምኞት ደበበ እንዲሁም ከግብ ዘቡ ቻርለስ ሉክዋጎ ጋር የለፋው ፍሪምፖንግ በራሱ የፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ብቻ ሳይወሰን በተቃራኒ ሳጥንም ድንቅ ሆኖ ይታያል። በዚህም ከኢስማኤል ኦሮ-አጎሮ እና አቤል ያለው በመቀጠል በአራት ግቦች የቡድኑ ሦስተኛ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች ነው።

በፈረሰኞቹ አራተኛ የውድድር ዘመኑን እያሳለፈ የሚገኘውና በምርጥ ብቃቱ ላይ የሚገኘው ተጫዋች አግኝተን ተከታዩን ቆይታ አድርገናል።

በጋና አሻንቲ ክልል በሚገኘው እና ከዋና ከተማው አክራ በመቀጠል ሁለተኛው የሀገሪቱ ትልቁ ከተማ በሆነው ኩማሲ የተወለደው የዛሬው እንግዳችን ፍሪምፖንግ ሜንሱ በልጅነቱ የእግር ኳስ ፍቅር ቢኖረውም ፍቅሩን በደንብ መኖር ለመጀመር የግድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ማጠናቀቅ ነበረበት። ትምህርቱን እየተማረ ግን በሰፈር እና ትምህርት ቤት ከእኩዮቹ ጋር ለደስታ ሲል ብቻ ይጫወት እንደነበር ይናገራል። “እንደ አብዛኞቹ ተጫዋቾች ከልጅነቴ ጀምሮ በደንብ ኳስን እየተጫወትኩ አላደኩም። ቤተሰቦቼ በትምህርቴ እንድገፋ ነው እንጂ ኳስ እንድጫወት አያበረታቱኝም ነበር። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን እስካገባድድ በማገኘው አጋጣሚ ብቻ ነበር እንደ ማንኛውም ታዳጊ ስጫወት የነበረው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን እንደፈፀምኩ ግን ኳስን በደንብ መጫወት ጀመርኩ።”

አስራዎቹ አጋማሽ ላይ ሲደርስ ቤተሰቦቹን እያሳመነ ፍቅሩን ማስታገስ የጀመረው ፍሪምፖንግ አሶክዋ ዲፖርቲቮ የተባለውን የሀገሩን ክለብ በመቀላቀል የክለብ ህይወቱን ‘ሀ’ ብሎ ጀምሯል። በማስከተል ወደ ዋ ኦል ስታርስ በማምራት አንድ ዓመት፣ በሊበሪቲ ፕሮፌሽናልስ አራት ዓመት እንዲሁም በአሻቴ ኮቶኮ ሁለት ዓመት ከግማሽ ቆይቶ ራሱን በሚገባ አጎልብቷል። ተጫዋቹ በዋናው የጋና ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ባይደርሰውም በ17 እና 20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ሀገሩን የማገልገል ዕድል አግኝቷል።

የጋና ብዙሃን መገናኛዎች የፍሪምፖንግን ስም ሲያነሱ ስለ አባቱ አያይዘው ሀሳብ መስጠታቸው በተደጋጋሚ ይሰማል። ምክንያቱም የፍሪምፖንግ አባት የቀድሞ የጋና ምርጥ ተጫዋች ስለነበሩ። በቀድሞ የእግር ኳስ ተጫዋች አባት እና በንግድ ዓለም ከሚገኙት እናቱ የተገኘው ተጫዋቹም አንድ እህት እና ሁለት ወንድም እንዳለው ከነገረን በኋላ ስለ አባቱ ሀሳቡን አጋርቶናል። “አባቴ የቀድሞ ኳስ ተጫዋች ነበር። የጋና ብሔራዊ ቡድንንም አገልግሏል። በአፍሪካ ዋንጫ ላይም ተሳትፏል። ለአሻንቴ ኮቶኮም ተጫውቷል። የሚገርመው እርሱም የመሐል ተከላካይ ነበር። እሱን እንደ አርዐያ እያየው ነው ያደኩት።”

በታዳጊነቱ በየትኛውም ፕሮጀክት እና አካዳሚ ያላለፈው ተጫዋቹ ከአሻቴ ኮቶኮ በኋላ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጣበትን ጊዜ አራት ዓመት ወደ ኋላ ተጉዞ ሲያስታውስ “ጋና እያለሁ አንድ የሀገሬ የእግር ኳስ ኤጀንት ስልክ ደወለልኝ። ቅዱስ ጊዮርጊስ የመሐል ተከላካይ እንደሚፈልግም ነገረኝ። ከዛ ቪዲዮ እንድልክለት አድርጎኝ ያንን ቪዲዮ በወቅቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ አሠልጣኝ የነበሩት ቫዝ ፒንቶ እንዲያዩት ተደረገ። አሠልጣኙም ቪዲዮውን ወዶት ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ የሦስት ቀን የሙከራ ጊዜ እንዳሳልፍ ፍቃድ ሰጠ። መጥቼ ባሳየሁት ብቃት ወዲያው አስፈረሙኝ።” ሲል ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ አመጣጡ ያስታውሳል።

አንድ ሜትር ከ ሰማንያ ሦስት ሴንቲ ሜትር የሚረዝመው እና ሰባ ስምንት ኪሎ የሚመዝነው ተከላካይ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በፊት ስለ ሀገሪቱ ያለውን ሀሳብ እና እውቀት እንዲህ ይገልፃል “ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቴ በፊት ስለ ሀገሩ የተወሰነ እውቀት ነበረኝ። በተለይ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ መድረክ ጋና መጥቶ ሲጫወት ትንሽ ስለ ኢትዮጵያ እውቀት ኖረኝ። ግን ኢትዮጵያ ተወዳጅ እና ሰላማዊ ሀገር እንደሆነችም እሰማ ነበር። ከመጣው በኋላ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን በጣም ተወዳጅ፣ ተግባቢ እና አክባሪ እንደሆኑ አይቻለው።”

2010 ላይ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ቅዱስ ጊዮርጊስን የተቀላቀለው ተጫዋቹ በቅዱስ ጊዮርጊስ አንፃራዊ የዝቅታ ጊዜ እንዲሁም አሁን ወደ ከፍታ በሚደረገው ጉዞ ውስጥ አካል ነው። ይህንን ጉዳይ ተንተርሰን በቡድኑ ውስጥ ያለው ለውጥን እንዲያነፃፅርልን ጠይቀነው “ከአሁኑ የተለየ በፊት የአንድነት ስሜት አልነበረም። በዚህ ዓመት ግን የአንድነት ስሜቱ አስገራሚ ነው። ሁላችንም እንደጋገፋለን። አንዱ ሲወድቅ አንዱ እየደገፈ ነው እዚህ የደረስነው። ስለዚህ ዋናው ለውጥ የአንድነት ስሜቱ ነው።” ብሎናል።

በርካታ የውጪ ሀገር ተጫዋቾችን በማምጣት የሚታወቀው የ27 ጊዜ የኢትዮጵያ ቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለፉትን ዓመታት ወደ ስብስቡ የቀላቀላቸው አብዛኛዎቹ የውጪ ተጫዋቾች ያን ያህል ስኬታማ ባይሆኑለትም ፍሪምፖንግ ግን ከአብዛኞቹ ተጫዋቾች በተለየ በምርጥ ብቃት ክለቡን እያገለገለ ለዓመታት መቆየት ችሏል። ይህንን ተከትሎም “እኔ የትኛውም ክለብ ልሂድ 110% ያለኝን አቅም አውጥቼ ለመስጠት ነው የምሞክረው። ያለሁበትን ክለብ በደንብ እያገለገልኩ መሆኔንም እርግጠኛ መሆን እፈልጋለው። ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስመጣም ክለቡ ትልቅ ክለብ እንደሆነ ሰምቻለው። ወደ ትልቅ ክለብ ስትመጣ ደግሞ ካንተ ብዙ ነገር ይጠበቃል። በክለቡ የሀገር ውስጥ ተጫዋቾች አሉ። አንተ ከውጪ ስትመጣ ደግሞ ተሽለህ መገኘት እና የሀገር ውስጥ ተጫዋቾቹ ከሚያሳዩት ብቃት በላይ ማሳየት አለብህ። እኔም ይህንን ስለማውቅ በደንብ ጠንክሬ በመስራት ምርጥ ብቃቴ ላይ ለመገኘት እየሞከርኩ ነው።”

በእስካሁኑ የሊጉ ጉዞ 18ቱም ጨዋታዎች ላይ (1619 ደቂቃዎችን) ተሳትፎ ያደረገው ተጫዋቹ ናትናኤል ዘለቀ እና ሐይደር ሸረፋ ባልነሩባቸው በርካታ ጨዋታዎች ላይ ቡድኑን በአምበልነት መርቷል። በሀገራችን በመቶ የሚቆጠሩ የውጪ ዜጋ ተጫዋቾች ቢመጡም በአምበልነት ያየናቸው ጥቂቶቹን ብቻ ነበር። የፍሪምፖንግን ያህል በርካታ ጨዋታን በአምበልነት የመሩ ፈልጎ ማግኘት ደግሞ አዳጋች ነው። ጋናዊው ተከላካይ በጥሩ ቡድናዊ መዋቅር የተገነባውን ስብስብ ሜዳ ላይ የሚመራበት መንገድ አስገራሚ ነው። በታላቁ ክለብ አምበል ስለመሆኑም ደስታውን ሳይሸሽግ ተከታዩን አጫውቶናል።

“ይህ በጣም ደስታ የሚሰጠኝ እና የሚያኮራኝ ነገር ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ብዙ ጊዜ አልተለመደም። ከውጪ የመጡ ተጫዋቾች ቡድኖችን በአምበልነት ብዙ እንዲመሩ አይመረጡም። አሁን በጊዮርጊስ ይህንን ክብር አግኝቻለው። በዚህም ትልቅ ደስታ ይሰማኛል። አምበል ስላደረጉኝም አመሰግናለሁ።”

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ የሚገኘው የፍሪምፖንግ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ እስካሁን በአንድም ጨዋታ ሽንፈት አላስተናገደም። ሽንፈት ብቻ ሳይሆን ጥቂት ግቦችን በማስተናገድ እና በርካታ ግቦችን ተጋጣሚ ላይ በማስቆጠር እንዲሁም በርካታ ጨዋታዎችን በማሸነፍ የሊጉ ቀዳሚ ክለብ ነው። ብዙዎችን እያስገረመ የሚገኘው የቡድኑ ብቃትን እና ወደ ዋንጫ እየተደረገ የሚገኘውን ጉዞ በተመለከተም ፍሪምፖን የሚለው አለ።

“የቡድናችን ብቃት በጣም ድንቅ ነው። የኢትዮጵያን የእግር ኳስ ታሪክ በደንብ ባላውቅም ግን እንደዚህ 18 ጨዋታዎችን ሳይሸነፍ የሄደ ክለብ አላውቅም። አንዳንድ ጊዜ ቁጭ ብዬ 18 ጨዋታዎችን አለመሸነፋችንን ሳስበው ለራሴ አላምንም። ሁል ጊዜ ወደ ሜዳ ስንገባ ግባችንን ላለማስደፈር እና ለማሸነፍ ነው የምናስበው። ድንገት ተጋጣሚ ቀድሞ ቢያገባብን እንኳን ወዲያው ምላሽ ለመስጠት እንፈልጋለን። ይህ ፍላጎታችን አንድም ጨዋታ እንዳንሸነፍ አድርጎናል።

“ሁሌ ከፊታችን ያለውን ጨዋታ እያሰብን እሱን ለማሸነፍ ነው የምንጥረው። ዋናው ትኩረታችን ቀጣዩ ጨዋታ ነው። ከማንም ጋር ብንጫወት እሱን ጨዋታ እያሰብን ነው የምንቆየው። ያንን ጨዋታ እንደ ተወጣን ደግሞ ስለ ቀጣዩ እናስባለን። እንደዚህ እያደረግን ነው የምንጓዘው።”

በውጪ አሠልጣኞች እና በሀገር ውስጥ አሠልጣኞች መሰልጠን ያለውን ልዩነት በተመለከተ “እኔ ከማንኛውም አሠልጣኝ ጋር መስራት እችላለው። የሀገር ውስጥም ሆነ የውጪ አሠልጣኝ የሚለኝን በልምምድ ላይ በደንብ እሰራለው።” የሚለው ጋናዊው ተከላካይ ስለ ቡድኑ ሀሳቡን ካጋራን በኋላ በማስከተል ስለ ግል ምርጥ ብቃቱ እና ግብ አስቆጣሪ ስለመሆኑ “በዚህ ዓመት እያሳየው ያለሁት ብቃት ከሞላ ጎደል ጥሩ ነው። በዚህም ደግሞ ደስተኛ ነኝ። ዋና ኃላፊነቴ ከሆነው መከላከል በተጨማሪ ግቦችንም ማስቆጠሬ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው።” በማለት ሀሳብ ሰጥቶናል።

በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ሀገሩ ጋናን ለማገልገል ከፍተኛ ተስፋ ያለው ፍሪምፖንግ በመጨረሻም ለቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ያለውን አክብሮት በመግለፅ ከአጋሮቹ ጋር በመሆን የሊጉን ዋንጫ ዘንድሮ አንስተው እንደሚያስደስቷቸው በመግለፅ ቆይታውን አገባዷል።

ያጋሩ