በመጨረሻው የዐበይት ጉዳዮች ፅሁፋችን ሌሎች ትኩረት የሳቡ ጉዳዮችን ለማንሳት ሞክረናል።
👉 በግብ የተንበሸበሸው የጨዋታ ሳምንት
በ18ኛ የጨዋታ ሳምንት በሊጉ እስካሁን ከተመለከትናቸው የጨዋታ ሳምንታት ከጎሎች አንፃር ሪከርድ የተጋራ ሆኗል። 25 ግቦችን ያስተናገደው የጨዋታ ሳምንቱ ወላይታ ድቻ እና አዳማ ከተማ ያለግብ ከተለያዩበት ጨዋታ ውጪ በተቀሩት ሰባት ጨዋታዎች ግቦችን በብዛት የተመለከትንበት ሳምንት ነበር።
በአማካይ በጨዋታ 3.25 ግቦች የታየበት የጨዋታ ሳምንቱ ከ11ኛው ሳምንት ዕኩል የግብ መጠኖች የተመዝገቡበት ሆኗል። በእርግጥ ከመረብ ያረፉትን ትተን በመዝገብ የሚሰፍረውን ከግምት ካስገባን የባህር ዳር ከተማ የፎርፌ ውጤት አጠቃላይ የግብ ድምሩን 26 የሚያደርስ የጨዋታ ሳምንቱንም የእስካሁኑ ከፍተኛ ግብ የተቆጠረበት ሳምንት የሚያደርገው ነው።
በነጠላ ጨዋታ ስንመለከተው ደግሞ በ11ኛው ሳምንት ጅማ አባ ጅፋር ሀዲያ ሀሳዕናን 4-2 እንዲሁም በ13ኛው ሳምንት አዲስ አበባ ከተማ ሰበታን 5-1 ያሸነፉባቸው ጨዋታዎች ከፍተኛ ግብ የተመዘገቡባቸው ሆነው የቆዩ ሲሆን የዚህ ሳምንቱ የሀዲያ ሆሳዕና እና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታ በስምንት ግቦች ደምቆ 4-4 በመጠናቀቅ የስድስት ግቦች ሪከርዱን አሻሻሿል።
በሌላው የሳምንቱ ጨዋታዎች የግቦች ገፅታ ደግሞ እንደቀደሙት ሁለት ሳምንታት ሁሉ በርከት ያሉ ግቦች ከቆሙ ኳሶች የተመለከትን ሲሆን በተመሳሳይ ተከላካዮችም በግብ አስቆጣሪነት ስማቸውን አስፍረዋል።
👉 የሀዲያ ሆሳዕና መለያ እና የቀለም ስብጥር
ነጭ በቀይ ቡኒ መለያ ላይ በጥቁር ቀለም የተፃፉ ቁጥሮች እና የተጫዋቾች ስም እንዲሁም ከመለያው ቀለም አንፃር ለዕይታ ምቾት የማይሰጠው ውሀ ሰማያዊ ካሶተኒ ?
ክለቦች ከሁለተኛው ዙር አንስቶ የሊጉ የስያሜ መብት ባለቤት የሆነው የቤትኪንግ የስፖርት ውርርድ ተቋም ያሰራቸውን መለያዎችን መጠቀም መጀመራቸው ይታወቃል። መለያውን ያቀረበው ተቋም መለያውን ከማቅረብ ባለፈ በመለያው ላይ ፅሁፎችን የማስፈር ነፃነቱን ለክለቦች በመስጠቱ በአንዳንድ ክለቦች በኩል እጅግ የተለመደ አለፍ ሲልም ፍፁም የወረደ የህትመት ሥራዎችን እየተመለከትን እንገኛለን።
ከቀናት በፊት በኢትዮጵያ ቡና መለያ ላይ እንዳነሳነው ሁሉ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደግሞ ነጭ በቀይ ቡኒ መለያቸው ላይ በጥቁር ቀለም የሰፈረው የተጫዋቾች ስም እና ቁጥር ለዕይታ እጅግ ፈታኝ ሆኖ ተመልክተነዋል። ከዚህ ባለፈም በዚሁ የጨዋታ ዕለት ቡድኑ ባልተለመደ መልኩ ውሀ ሰማያዊ ካልሶተኒ ሲጠቀም አስተውለናል።
ሀዲያ ሆሳዕና በዘንድሮው የውድድር ዘመን በሁለት የቀለም አማራጭ የተመረቱ መለያዎችን ጥቅም ላይ ሲያውል የተመለከትን ሲሆን በዚህ የጨዋታ ሳምንት ሲጠቀምበት የተመለከተነው ውሀ ሰማያዊ ካሶተኒ ግን በሁለቱም የቀለም አማራጭ ከቀረቡት መለያዎች ጋር ጥቅም ላይ ሲውል ያልተመለከትነው ሲሆን ይህ የሆነው ደግሞ ከተጋጣሚው አርባምንጭ ከተማ ትጥቆች ጋር የቀለም ግጭት ሳይኖር መሆኑ ጉዳዩን አስገራሚ ያደርገዋል።
“ክለባዊ ማንነት” የሚለው እሳቤ በእግርኳሳችን ገና የሚታወቅው ባይሆንም የቀለም ምርጫዎች ላይ ግን ክለቦች አሁንም ትኩረት ሰጥተው ማሰብ እንዳለባቸው ያስመለከተ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል። ቢያንስ በመለያዎች ላይ የሚሰፍሩ ፅሁፎች ከመለያው ቀለም ይዘት አንፃር ታሳቢ የተደረጉ እንዲሆን እንመክራለን።
👉 ዝናብ ያልበገራቸው ደጋፊዎች
በጨዋታ ሳምንቱ ተጠባቂ በነበረው የሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡና የወንድማማቾች ደርቢ ጨዋታ በሲዳማ ቡና የበላይነት መጠናቀቁ አይዘነጋም ፤ በጨዋታው ግን የተለየ የደጋፊዎች ትዕይንት ተመልክተናል።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ዕኩሌታ አንስቶ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዮኒቨርስቲ ከንፋስ ጋር ቀላቅሎ በጣለው ዝናብ ውስጥ እንኳን የሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች በከፊል ተራቁተው ቡድናቸውን ሲያበረታቱ ተመልክተናል።
በተለይ በጨዋታው በተለምዶ ከክብር ቱሪቡን ፊት ለፊት በሚገኘው የመቀመጫ ክፍል የነበሩት የሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች በቁጥር ሳይመናመኑ በዝናብ ውስጥ ፀንተው ቡድናቸውን ያበረታቱበት መንገድ ልዩ ነበር።
እነዚሁ ዝናብ ያልበገራቸው ደጋፊዎች በመደበኛ ልብሶች እንኳን መቋቋም በሚያስቸግረው በዚያ የአየር ሁኔታ ውስጥ ሆነው ያሳዩ የነበረው ድጋፍ ለክለቦቻቸው ስላላቸው ፍቅር በሚገባ ያስመለከተን አጋጣሚ ነው።
👉 ወደ ሜዳ የተመለሱት የባህር ዳር ከተማ ደጋፊዎች
ከሰሞኑ ቀስ በቀስ በስታዲየሞች ቁጥራቸው ተመናምነው የነበሩት የባህር ዳር ከተማ ደጋፊዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በክለባቸው ትጥቆች ተውበው ዳግም ወደ ሜዳ ተመልሰዋል።
ረቡዕ ሌሊት ከባህር ዳር መነሻቸውን ያደረጉት የባህር ዳር ከተማዎች ሐሙስ ምሽት ለተደረገው የወልቂጤ ከተማ እና ባህር ዳር ከተማ ጨዋታ የተለየ ድባብን ፈጥረው ተመልክተናል። በክለቡ መለያ ቀለማት በተሰሩ መለያዎች የደመቁት እነዚሁ ደጋፊዎች ከአብዛኛው ክለቦች ደጋፊዎች በተለየ የክለባቸውን ባንዲራ እና ስካርፎችን ይዘው ወደ ሜዳ በመግባት ቡድናቸውን አበረታተዋል። ደጋፊዎቹ ሰማያዊ ቀለም ያለው ጭስን (Flair) ተጠቅመው ደስታቸውን የገለፁበት ሂደትም ለስታዲየሙ የተለየ ድባብ ያለባሰ ነበር።
ምንም እንኳን ብባህር ዳር ከተማ በመጨረሻ ደቂቃ ባስተናገደው ግብ ነጥብ ቢጋራ እና የአሸናፊነት ደስታቸውን በስታዲየሙ ውስጥ ባያጣጥሙም ትናንት በተሰጠው የሊጉ አክሲዮን ማህበር ውሳኔ ክለባቸው ጨዋታውን በፎርፌ ማሸነፍ ችሏል።
👉 ቀይ ካርዶች እና አደገኛ ጥፋቶች መበራከት
ሁለተኛው ዙር ጅማሮውን ካደረገ ሦስተኛ የጨዋታ ሳምንቱ ላይ የደረሰ ሲሆን በ16ኛ እና 17ኛ የጨዋታ ሳምንት ምንም ዓይነት ቀይ ካርድ ሳንመለከት ብንቆይም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን ሦስት ቀይ ካርዶች ተመልክተናል።
እንደተለመደው ሦስቱም ቀይ ካርዶች ቡድንን ሊጠቅሙ በሚችሉ ውሳኔዎች የተገኙ ሳይሆኑ ባልተገቡ አጨዋወቶች የተሰጡ ናቸው።
የጨዋታ ሳምንቱን የመጀመሪያ ቀይ ካርድ የተመለከተው የድሬዳዋ ከተማው አብዱለጢፍ መሀመድ ነበር። ፍፁም ሊያስታውሰው የማይፈልገው የጨዋታ ዕለት ያሳለፈው አብዱለጢፍ በ47ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ቢጫውን ከ20 ደቂቃ በኋላ ደግሞ ሁለተኛውን ቢጫ ካርድ ተመልክቶ ከሜዳ ወጥቷል።
ሁለተኛውን እና የሳምንቱም ብቸኛ ቀጥተኛ ቀይ ካርድ የተመለከተው የጅማ አባ ጅፋሩ ሙሴ ካበላ ነበር። አንድ አቻ በቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ጅማዎች የተሻለ መነቃቃት ላይ በነበሩበት እና የፋሲልን ሳጥን በተደጋጋሚ መጎብኘት በጀመሩባቸው ጊዜያት ላይ ሳይታሰብ በ83ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ባየህ ላይ በሰራው አደገኛ ጥፋት በቀይ ካርድ ሲወገድ ቡድኑን ይህን የቁጥር ጉድለት ለማካካስ ፍፁም መከላከል በመምረጡ ግብ አስተናግዶ እንዲሸነፍ ሆኗን።
ሌላኛው የቀይ ካርድ አጋጣሚ ደግሞ ሲዳማ ቡና ሀዋሳን 3-1 በረታበት ጨዋታ ፍሬው ሰለሞን በ5 ደቂቃ ልዩነት በ73ኛው እና በ78ኛው ደቂቃ በተመለከታቸው ሁለት ቢጫ ካርዶች ከሜዳ ተወግዷል።
የቀይ ካርድ አጋጣሚዎቹን አነሳን እንጂ በጨዋታ ሳምንቱ እንዲሁ ከዳኞች ዕይታ የተሰወሩ እንዲሁም በዳኞች ውሳኔ የታለፉ በርካታ አደገኛ ጥፋቶችን የተመለከትንበት ሳምንት ነበር።
👉 የአዳማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም…
በዘንድሮው የውድድር ዘመን ሊጉ እስካሁን ከተደረገባቸው ሜዳዎች መካከል የድሬዳዋ ስታዲየም እና አሁን ሊጉ እየተደረገበት የሚገኘው የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ በብዙ መመዘኛዎች የተሻሉ እንደሆኑ እየተመለከትን እንገኛለን።
በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በምሽት ከተደረጉ ጨዋታዎች መካከል ሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡናን ባገናኘው ጨዋታ የስታዲየሙ የተወሰኑ ክፍሎች የነበሩ መብራቶች በድንገት ጠፍተው የነበሩ ቢሆንም በሰከንዶች ልዩነት ዳግም የበሩበት ሂደት እጅግ አስደናቂ ነበር። እንዲሁ በዕረፍት ሰዓትም ተመሳሳይ የመብራት መቋረጥ ቢከሰትም መልሶ ለመምጣት ጊዜ አልወሰደም። ይህም ሂደት ሌሎች የአስተናጋጅ ከተማ ስታዲየሞች ትምህርት ለወስዱበት የሚገባ ነው።
የአዳማው የመጫወቻ ሜዳ ተመልካችም በዕይታ ማረጋገጥ እንደሚችለው አለፍ ሲልም በጨዋታ ሂደቶች ማስተዋል እንደሚቻለው የሜዳው ይዞታ ጥሩ የሚባል ቢሆንም በሁለቱ የግብ ክልሎች አካባቢ ግን ያለው የሜዳ ሁኔታ መጠነኛ ማሻሻያዎች ሳይፈልግ እንደማይቀር የተወሰኑ ምልክቶችን ተመልክተናል።
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ሲዳማ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ ካደረጉት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ከሱፐር ስፖርት ጋር ቆይታን ያደረገው ፍሬው ጌታሁን ስለተደጋጋሚ የግብ ጠባቂዎች ስህተት ሲጠየቅ ያነሳው ጉዳይ ከስህተቶቹ በስተጀርባ ግብ ክልሎቹ አካባቢ ያለው የሜዳ ሁኔታ ድርሻ እንዳለው ሲናገር ያደመጥን ሲሆን በዚህ ሳምንት ደግሞ ሀሳቡን የሚያጠናክሩ አጋጣሚዎችን ተመልክተናል።
በተለይም ሀዋሳ እና ሲዳማ ባደረጉት ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ ተክለማርያም ሻንቆ ወደ ኋላ የተመለሰለትን ኳስ በእግሩ ለመቆጣጠር ጥረት ባደረገበት ወቅት አግሩን ዘላ ያለፈችው ኳስ ግብ ክልል አካባቢ ስላለው የሜዳ ሁኔታ አስረጅ አጋጣሚ ነበረች።
ተክለማርያም ኳሱን ለመቀበል የቆመበት ቦታ ከግቡ አፍ (Goal Mouth) በመጠኑም በአግድመት የቆመ ስለነበር እንጂ ኳሷ ግብ በሆነች ነበር። በመሆኑም የሜዳው ወሳኝ በሆነው በዚህ ክፍል ስላለው የሜዳ ሁኔታ በአፋጣኝ የማሻሻል ስራዎች ሊሰሩ ይገባል።
👉በብሔራዊ መዝሙር ጨዋታቸውን ያሳረጉት ደጋፊዎች
በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከተመለከትናቸው ትኩረት የሳቡ ጉዳዮች መካከል የወልቂጤ ከተማ ደጋፊዎች ምንን እንኳን የኋላ ኋላ በፎርፌ ቢሸነፉም ከባህር ዳር ጋር አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የፈፀሙት ተግባር ነበር።
ሁለት አቻ ከተጠናቀቀው ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ በስታዲየም ተገኝተው ቡድናቸውን ሲያበረታቱ የቆዩት የወልቂጤ ከተማ ደጋፊዎች ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ከተጫዋቾቻቸው ጋር በጋራ በመሆን የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙርን ሲዘምሩ ተመልክተናል።
ይህ ሂደት በተለይ ቡድኑ በከፍተኛ ሊግ በነበረባቸው ጊዜያት በሜዳቸው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ወቅት ከጨዋታዎች መጀመር አስቀድሞ የክለቡ ደጋፊዎች የኢትዮጵያ ህዝብ መዝመሩ በመዘመር ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ሲሆን ይህ ልምምድ ታድያ ከረጅም ጊዜያት በኋላ በክለቡ ደጋፊዎች ሲከወን ተመልክተናል።
በተመሳሳይ ይህ ልምምድ ሲዳማ ቡና መቀመጫው ይርጋለም በነበረ ጊዜያትም ይደረግ እንደነበር የምናስታውሰው ነበር።