የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ9ኛ ሳምንት የዛሬ ጨዋታዎች ውሎ

በዛሬ በሊጉ በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ሁለቱ መሪዎች ድል ሲቀናቸው አርባምንጭ ከተማም ደረጃውን አሻሽሏል።

በቶማስ ቦጋለ

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ ድል ተመልሷል

መጀመሪያ በወጣለት መርሐ ግብር መሰረት ከሰዓት በኋላ 08:00 ላይ እንደሚደረግ ይጠበቅ የነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ ምሽት ላይ በተከናወነው የኢቢስ ስፖርተኞች ሽልማት ምክንያት ረፋድ 03:00 ላይ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስታድየም ተከናውኗል።

በጨዋታው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
በሎዛ አበራ ፣ አሳቤ ሙሶ እና አረጋሽ ካልሳ ግቦች የመጀመሪያውን አጋማሽ 3-0 እየመራ መውጣት ሲችል ከዕረፍት መልስ ሎዛ እና አረጋሽ ተጨማሪ ግቦችን አክለው ጨዋታው በ5-0 ውጤት ተጠናቋል። ድሉም ለሊጉ መሪዎች ከሁለት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ የተገኘ ነበር።

ከጨዋታው በኋላ ሎዛ አበራ ፣ ሰናይት ቦጋለ እና አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው በሽልማት ሥነ ስርዓቱ ላይ ለመታደም ወደ አዲስ አበባ አቅንተዋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስረኛው ሳምንት ላይ ከሚጠብቀው የሀዋሳ ከተማው ወሳኝ ጨዋታ በፊት ሊጉን በ23 ነጥቦች መምራቱን ሲቀጥል ቅዱስ ጊዮርጊስን ካሸነፈበት ጨዋታ መልስ ከባድ ሽንፈት ያገኘው አዳማ ከተማ ደግሞ ዛሬ ድል ከቀናው አርባምንጭ ከተማ ጋር ይገናኛል።

ሀዋሳ ከተማ ንግድ ባንክን መከተሉን ቀጥሏል

ረፋድ 03:00 ላይ ሀዋሳ እና ጊዮርጊስን ባገናኘው ጨዋታ ፈረሰኞቹ በ8ኛ ሳምንት በአዳማ ከተማ 4-1 በተረቱበት ጨዋታ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የ 2 ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ገብሬላ አበበ እና ቤተልሔም አሰፋ በሰፋኒት ተፈራ እና ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ቀይ ካርድ ባገኘችው ሊዲያ እንድሪስ ተተክተው ገብተዋል። ሐዋሳ ከተማዎች በበኩላቸው በ8ኛ ሳምንት ብርቱ ፉክክር አድርገው አዲስአበባ ከተማን 4-3 ካሸነፉበት አሰላለፍ የአራት ተጫዋቾች ቅያሪ ሲያደርጉ ፍሬወይን ገብሩ ፣ ማሕደር ባየ ፣ ዙፋን ደፈርሻ እና አፍያ አብዱራህማን በመስከረም መንግሥቱ ፣ ፀሐይነሽ ጅላ ፣ ሕይወት ረጉ እና ሣራ ነብሶ ተተክተው ገብተዋል።

ብዙም ፉክክር ባልታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ 6ኛው ደቂቃ ላይ ቤተልሔም መንተሎ ከብዙዓየሁ ፀጋዬ በተቀበለችውና ወደ ግብ ሞክራ ግብ ጠባቂዋ በያዘችው ኳስ የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ታይቷል። እታለም አግኑ ከረጅም ርቀት የሞከረችው እና የግቡን አግዳሚ ታክኮ የወጣው ኳስ የሀዋሳዎች የ8ኛ ደቂቃ ሙከራ ሳይሳካ ቢቀርም ከ11 ደቂቃዎች በኋላ ቡድኑ ቀዳሚ ሆናል። የሀዋሳዋ ነጻነት መና ከቀኝ መስመር ወደግብ ያሻማችውን ኳስ የጊዮርጊሷ ቤተልሔም እሸቱ በራሷ ላይ አስቆጥራ ነበር ሀዋሳዎች ቀዳሚ የሆኑት።

32ኛው ደቂቃ ላይ ተደጋጋሚ የግብ ዕድል ስትፈጥር የነበረችው ቱሪስት ለማ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝታ የጨዋታውን ውጤት ሊያሰፋ የሚችል ወርቃማ ዕድል አምክናለች። 35ኛው ደቂቃ ላይም ማሕደር ባየም ሌላ ኢላማውን የጠበቀ የርቀት ሙከራ ከረጅም ርቀት አድርጋ በግብ ጠባቂዋ ድኖባት ነበር። በሌላው ወገን ፈረሰኞቹ በመልሶ ማጥቃት የወሰዱት እና ሰላም በቃኸኝ ከ ቤተልሔም መንተሎ ተቀብላ የሞከረችውን ኳስ ግብ ጠባቂዋ በቀላሉ ይዛዋለች። 44ኛው ደቂቃ ላይ ዙፋን ደፈርሻ ከማዕዘን ያሻማችውን ኳስ ቅድስት ዘለቀ በግንባሯ ገጭታ ጥሩ ሙከራ ብታደርግም ኢላማውን የጠበቀ አልነበረም። ይህም የመጀመሪያ አጋማሽ የመጨረሻ ሙከራ ሆኗል።

በሁለተኛው አጋማሽ 48ኛው ደቂቃ ላይ መንደሪን ክንድሁን ከቀኝ መስመር ላይ ያገኘቸውን ቅጣት ምት ወደግብ በጥሩ ሁኔታ ብትሞክርም በግብ ጠባቂዋ ጥረት ቀርቶ ከግቡ አግዳሚ ጋር ተጋጭቶ ሲመለስ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ የነበረችው ቅድስት ቴቃ ወደ ግብ ልካው የብድኗን መሪነት አጠናክራለች። ከግቧ መቆጠር በኋላም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር የሞከሩት ሐዋሳ ከተማዎች በ ምሕረት መለሰ እና ዙፋን ደፈርሻ የግብ ዕድል ለመፍጠር ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም።

በጨዋታው የመጨረሻ 30 ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥሩ የበላይ የነበሩት ፈረሰኞቹ ተጫዋች ቤተልሔም መንተሎ ከዳግማዊት ሠለሞን የተሻገረላትን እና ከግብ ጠባቂ ጋ አንድ ለአንድ ተገናኝታ ያመከነችው ኳስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚፈልጉትን ጊዮርጊሶች ያስቆጨች ነበረች። በተደጋጋሚም በዓይናለም ዓለማየሁ እና በቤተልሔም መንተሎ የግብ ዕድል ለመፍጠር ቢሞክሩም ውጤታማ አልነበሩም። 87ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ ገብታ ጥሩ የተንቀሳቀሰችው ታሪኳ ጴጥሮስ በድንቅ አጨራረስ 3ኛ ግብ ለሀዋሳ ማስቆጠር ችላ ጨዋታው 3- 0 ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ሀዋሳ ነጥቡን 22 አድርሶ ንግድ ባንክን በአንድ ነጥብ ልዩነት መከተሉን ቀጥሏል።

ሊጉ በ10ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሲቀጥል ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዲስአበባ ከተማ ሲገናኝ ሀዋሳ ከተማ ከመሪው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ይጫወታል።

አርባምንጭ ከተማ የ1-0 ድል በማሳካት ደረጃውን አሻሽሏል

ከሰዓት በኋላ በተደረገው የአርባምንጭ እና ቦሌ ክ/ከተማ ጨዋታ አርባምንጮች በ8ኛ ሳምንት ከጌዴኦ ዲላ ያለምንም ግብ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ርብቃ ጣሰውና ደራ ጎሣ ለምለም አስታጥቄን እና ጺዮን ሣህሌን ተክተው ገብተዋል። ቦሌዎችም በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ሁለት አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ መዐዛ አብደላ እና ትዕግስት ሙሉዓለም በይዲዲያ አሜ እና ሲፈን ተስፋዬ ተተክተው ገብተዋል።

ለተመልካች አዝናኝ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በመጀመሪያው ደቂቃዎች ተጭነው የተንቀሳቀሱት ቦሌዎች በምርጥነሽ ዮሐንስ እና ትዕግስት ሙሉዓለም የግብ ዕድል መፍጠር ቢችሉም ውጤታማ መሆን ግን አልቻሉም። በተለይ 14ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ተሻምቶ የአርባምንጭ ተከላካዮች ያወጡትን ኳስ ነፃ ሆና ያገኘቸው ምርጥነሽ ወደግብ ሞክራው የቀኙን ቋሚ ታክኮ የወጣው ኳስ ቦሌዎችን ያስቆጨ ነበር። ከ 15ኛው ደቂቃ በኋላ በጨዋታው የበላይ የነበሩት እና ተጭነው የተጫወቱት አርባምንጮች በ ርብቃ ካሣው ፣ ወርቅነሽ ሚልሜላ ፣ መሠረት ወርቅነህ ፣ ሠርካዲስ ካሣየ ፣ መቅደስ ከበደ የተለያዩ የግብ ዕድሎች መፍጠር ቢችሉም ግብ ማግኘት አልሆነላቸውም። ሆኖም 20ኛው ደቂቃ ላይ ወርቅነሽ ሚልሜላ ወደ ግብ ሞክራው ግብ ጠባቂዋ ያዳነችውን ኳስ ሲመለስ ነፃ ሆና ያገኘችው ድንቅነሽ በቀለ ጥሩ የግብ ማግባት ሙከራ ብታደርግም በግብ ጠባቂዋ ድንቅ ብቃት ተመልሶባታል። የመጀመሪያው አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊት ግብ ለማግኘት ይበልጥ ወደ ተጋጣሚ ክልል ተጭነው የተጫወቱት አዞዎቹ 39ኛው ደቂቃ ላይ ወርቅነሽ ሚልሜላ ከማዕዘን ያሻማችውን ኳስ ካንድአምላክ ሀቆ በግንባር በመግጨት አስቆጥራ ቡድኗን መሪ አድርጋ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

በጣም ቀዝቃዛ ፉክክር በታየበት እና ኢላማውን የጠበቀ ኳስ ባልተሞከረበት የሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ሠርካዲስ ካሣየ የቦሌ ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተጠቅማ ወደግብ የሞከረችውና የላይኛውን አግዳሚ ገጭቶ ሲመለስ ነጻ ሆና ያገኘችው መሠረት ወርቅነህ ኳሱን መቆጣጠር ባለመቻሏ ወርቃማ ዕድል አምክናለች። ከዚህች ሙከራ በኋላ በሁለቱም በኩል ኳስ መስርቶ የመውጣት ፍላጎት የታየበት ሲሆን የኳሶቹ ቶሎ ቶሎ መቆራረጥ አሰልቺ አድርጎታል። በአርባምንጭ በኩል መንፈስ መቼና እና ድንቅነሽ በቀለ በቦሌ በኩል ጤናየ ለታሞ ካደረጉት ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ውጪ ሌላ ምንም ዓይነት የግብ ዕድል ሳይፈጠር ጨዋታው ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎም አርባምንጭ በ13 ነጥቦች 5ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። በቀጣይም በአሥረኛ ሳምንት አርባምንጭ ከተማ ከአዳማ ከተማ ጋር ሲገናኝ ቦሌ ክፍለከተማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ይጫወታል።

ያጋሩ