በኤርሚያስ ብርሀነ
በ1970 መጨረሻ የኢትዮጵያ እግርኳስ ክለቦች ላይ ዱብዳ ወረደ። የ1970 መጨረሻ ጨዋታ እና በ1971 ዓ.ም የተጀመረው “አዲሱ” የክለቦች አደረጃጀት
በኤርሚያስ ብርሀነ
በኢትዮጵያ እግርኳስ ከፍ ባሉ የውድድር እርከኖች ይካሄዱ ከነበሩ ሻምፒዮናዎች መካከል የ1970 ዓ.ምቱ. ማገባደጃ የሸዋ ጥሎ-ማለፍ ፍጻሜ ነበር፡፡ ተጋጣሚዎቹም – አንጋፎቹ የአገራችን ክለቦች – ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኤሌክትሪክ ነበሩ። አሸናፊው የሸዋ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን ይወስዳል፡፡
የዚያን ጊዜ የአዲስ አበባ ክለቦች <የሸዋ ክለቦች/ቡድኖች> የሚል ሥያሜ ሲኖራቸው፣ ውድድሩ ደግሞ <የሸዋ ሻምፒዮና> ይሰኝ ነበር፡፡
በ1970ው የሸዋ ሻምፒዮና-ፍጻሜ ቀን ጨዋታው ከመደረጉ ጥቂት ሰዓታት ቀደም ብሎ የዘነበው ዝናብ ሜዳውን አጨቅይቶታል። ይሁን እንጂ የሜዳው መጨቅየት ጨዋታው እንዳይካሄድ አላደረገም፡፡ ጨዋታው እንደተጀመረ ኤሌክትሪክ ማጥቃቱን ተያያዘው፡፡ በዚህም ሳቢያ ኤሌክትሪክ የመጀመሪያ ግቡን በኛ ሰፈር ልጅ በሲራክ ገብረመድህን (ሴኮ) አማካኝነት አስቆጠረ። ያቺን የሲራክ ግብ በብዙ ነገር አስታውሳታለሁ።
ጨዋታው ከመጀመሩ አስቀድሞ በስታዲዮሙ ዙሪያ-ገባ የወትሮውን ያህል ሰው ስላልበዛ የፖሊስም ሃይል አነስተኛ ነበር፡፡ እኔም በአጥር ሾልኬ ወደ ሜዳ ገባሁ፤ በሚስማር ተራ በኩል በሚገኘው ጎል ኳስ ጠባቂ ሆንሁ። የሲራክ ግብ የተገኘችው እኔ በተቀመጥሁበት በኩል ነበር፡፡ አግቢው ደግሞ በደንብ የማውቀው፣ በዚያው አመት (1970) ለከፍተኛ 21-ቀበሌ 20 ሲጫወት የማየው ሲራክ ገብረመድህን (ሴኮ) ነው። ያን ዓመት የክለብ ተጫዋቾች ለቀበሌም ይጫወቱ ነበር። በወቅቱ በኢህአፓ (የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ፓርቲ) ምክንያት ብዙ ወጣት የሚታስርበት ጊዜ በመሆኑ ቀበሌ ምንም ነገር ቢጠይቅ “እምቢ!” የሚል አልነበረም። ለምሳሌ፡- በእኛ ቀበሌ በከፍተኛ 21-ቀበሌ 04 የፖሊሱ ወንድማገኝ ከበደ እና የአየር መንገዱ ተፈራ እሸቴ ለቀሌያችን ይጫወቱ ነበር። በነገራችን ላይ በዚያ ዘመን የከፍተኛ 21 የቀበሌዎችን ውድድር ያሸነፈው የነ ሲራክ ቀበሌ 20 ሲሆን ጎሉንም ያገባው ራሱ ሲራክ ገብረመድህን ነበር። ያሸነፉትም የነ ንሴብኦን(ኒሴፖ) 09 ቀበሌ ነው። (አቤት! የኒሲፖ ፎርሚች! ሸርተቴ! ያኔ ከርሱ ያየናቸውን እስካሁን ሳንረሳ ኳስን ለማግባትም፣ ለማውጣትም ይኸው ዛሬም ድረስ እንጠቀምባቸዋለን፡፡)
ወደ ኤሌክትሪክና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ልመለስና ቢረጋ ከግራ በኩል ክሮስ ያደረገውን ኳስ ሲራክ በሚገርም ሁኔታ በግንባሩ በመግጨት ኤሌክትሪክን መሪ አደረገ። ብዙም ሳይቆይ ቢረጋ እንደገና ከቀኝ መስመር ያሻማውን ተሻጋሪ ኳስ አሁንም ሲራክ አግኝቶ በግንባሩ በመግጨት አስገራሚ ሙከራ ቢያደርግም ኳሷ ግብ መሆን አልቻለችም፤ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጣች። ሁለቱም ቡደኖች ለእረፍት በዚህ የግብ ልዩነት ወደ መልበሻ ክፍል አመሩ፡፡
ከእረፍት በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በጣም ተጠናክረው ገቡ፡፡ ከመጀመሪያው ግማሽ በተሸለ አጥቅተውም ተጫወቱ፡፡ በርካታ የግብ ሙከራዎችም አደረጉ። ከእነዚያ ሁሉ የግብ ሙከራዎች መካከል በጣሙን የምታስቆጨው ግን የእንግዳወርቅ ታሪኩ (ሰበታ) ሙከራ ነበረች፡፡ ሰበታ የአሌክትሪክን ተከላካዮችና በረኛው-እስጢፋኖስ ፀጋዬን- ጭምር አልፎ ሄዶ ኳሷ ወደ ጎል መታት፤ እርሱም “ግቧን አገባሁ!” ብሎ ደስታውን እየገለፀ ሳለ በኤሌክትሪክ የግብ ክልል ውስጥ ከጎሉ አፋፍ ላይ በመረጋጋጥ ብዛት የለነቆጠው ጭቃ ኳሷን ያዛት፡፡ በዚህም የግቡን መስመር ሳታልፍ ቀረች፡፡ ለጊዮርጊሶች እጅግ የምታስቆጭ – ለኤሌክትሪኮች ደግሞ መዳኛ ነበረች።
ሰበታ የኳሷን መረብ ውስጥ አለመግባት ካየ በኋላ ጭንቅላቱን ይዞ ሃዘኑን የገለፀበት መንገድ አሁን ድረስ ፊቴ ላይ ይታየኛል። እኔ ደግሞ ያ ሁሉ አክሽን በተካሄደበት የጎል-ክልል ጀርባ ሆኜ ሁሉንም የድርጊት ኩነት ከቅርብ በማየቴ እራሴን እድለኛ አድርጌ እቆጥረዋለሁ። በጨዋታው ሌላ ጎል ሳይቆጠር በሲራክ ገብረመድህን (ሴኮ) ብቸኛና ወሳኝ ጎል ኤክትሪክ የፍጻሜውን ፍልሚያ አሸንፎ የሸዋ የጥሎ ማለፍ ሻምፒዮን ሆነ።
ያ ጨዋታ ለኤሌትሪክም ሆነ ለቅዱስ ጊዮርጊስ የመጨረሻ ጨዋታቸው መሆኑን ማንም ያወቀ ወይም የገመተ አይመስለኝም። አሌክትሪክ በቀጣዩ አመት ሸዋን ወክሎ በኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ለመጫወት፣ ቅዱስ ጊዮርጊስም በ1970 በኦሜድላና በኤሌክትሪክ የተነጠቃቸውን ዋንጫዎች በ1971 ተጠናክሮ በመቅረብ ለማስመለስ- ነበር ውጥናቸው። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እቅድ ግን ሌላ ሆነ፡፡
የ1970ው የሸዋ ሻምፒዮና ከተካሔደ ጥቂት ሳምንታት በኋላ የአገሪቱ እግርኳስ ማህበር በአዲሱ አመት (በ1971) አዲስ የስፖርት መዋቅር እንደሚያስተዋውቅ አወጀ። ፌዴሬሽኑ ከሰላሳ ዓመታት በላይ በቆየው የአገሪቱ እግርኳስ ክለቦች መዋቅራዊ አደረጃጀት ላይ ሥር-ነቀል ለውጥ የማካሄድ አጀንዳ ይዞ ከተፍ አለ፡፡ መዋቅሩ ስፖርታዊ ተሳትፎን በሚመለከት ነጻ እንቅስቃሴን የመገደብ ተልእኮ የነበረው ይመስላል፡፡ ለምሳሌ፡- እግርኳሱን ብቻ ነጥለን ብናይ – ሰዎች በሚሰሩበት መስሪያ ቤት፣ በሚኖሩበት አካባቢ፣ በሚማሩበት የትምህርት ተቋም፣….. እንደሚሳተፉና እንደሚወከሉ ያሳስባል። ውሳኔው ማንም ያልጠበቀው፣ ሁሉን ያስደነገጠና ብዙሃኑን ያሳዘነ ሆነ። “አዲሱ መዋቅር” የአገሪቱን ነባር፣ አንጋፋ፣ ስኬታማና ታሪካዊ ክለቦችን ህልውና ከባድ አደጋ ላይ ጣለ፡፡
እጅጉን በሚያሳዝን መልኩ አንጋፎቹ ክለቦች/ቡድኖች እነ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኤሌክትሪክ፣ ፈጣን ጎዳና፣ በራሪ፣ አንድነት፣ ቴዎድሮስ፣….. የመሳሰሉት ሲቪል ቡድኖች ፈረሱ። በአዲሱ መዋቅር መሰረት በተቋቋሙት በመኢሰማዎቹ ትግል ፍሬ፣ እርምጃችን እና ወደፊት ተተኩ። አዲስ አበባም በአራት ዞኖች ተከፍላ አራት የከነማ ቡድኖች ተመሰረቱ፡፡
1) ሰሜን ዞን፡- የዚህኛው ቀጣና ቡድን አብዮት ፍሬ የተሰኘ ሥያሜ ተሰጠው፡፡
ፒያሳ ፣ ሰሜን ሆቴል፣ አዲሱ ገበያ፣ ጉለሌና ባካባቢው ያሉትን ተጫዋቾች እንዲያካትት ተደረገ፡፡
2) ምእራብ ዞን፡- መጠሪያው ጥቁር አንበሳ ሆነ፡፡
መካኒሳ፣ ልደታ፣ ሰንጋተራ፣ መርካቶ፣….. አካባቢ ያሉትን ተጫዋቾች ይወክላል፡፡
3) ደቡብ ዞን፡- በኢትዮ-ሶማልያ ጦርነት ወቅት ኢትዮጵያ የዚያድ ባሬን ተስፋፊና ወራሪ ኃይል አሸንፋ የድል ችቦዋን ያበራችበት፣ ሰንደቋን የሰቀለችበትና ያውለበለበችበት ተረተር ጫፍ የዚህኛው ቀጣና መሰየሚያ ሆነ፡፡ ካራማራ ! ቦሌ፣ ንፋስ ስልክ፣ ቄራ፣ ለገሃር፣ ሜክሲኮና በአቅራቢያው የነበሩት ተጫዋቾች እዚህኛው ቀጣና ተጠቃለሉ፡፡
4) ምስራቅ ዞን፡- መጠሪያው ድል ብርሃን ተባለ፡፡
ካዛንቺስ፣ ቀበና፣ አራት ኪሎ፣ አምስት ኪሎ፣ ስድስት ኪሎ፣… እና ሌሎችም በዚህ ቀጣና አቅራቢያ ያሉትን ተጫዋቾች እንዲይዙ ተወሰነ።
ከላይ በተመለከተው የከነማ (ከተማ ነዋሪዎች ማህበር) ቡድኖች ውስጥ ተጫዋቾች በየአካባቢያቸው በተቋቋሙ ቡድኖች ውስጥ ተሰገሰጉ። የእኛ አካባቢ ተወካይ ደቡብ ዞን- ካራማራ ነበር።
አንጋፎቹ ፈርሰው፣ በሰራተኛ እና በከነማ ቡድኖች ቢተኩም አራቱ ወታደራዊ/ሚሊታሪ ቡድኖች ግን አልፈረሱም፡፡ የሚሊታሪ ቡድኖች የስም ለውጥ ብቻ ነበር ያደረጉት። እንዲያውም በነበሩት ላይ አንድ ወታደራዊ ቡድን ተጨመረ፡፡ አምስተኛው ወታደራዊ ቡድን ባህር ሃይል (መልህቅ) ተሰኘ።
በነገራችን ላይ ያኔ የተደረገው የስም ለውጥ የሚከተለውን ይመስላል።
– መቻል ፡- ምድር ጦር
– ኦሜድላ፡- ፖሊስ
– ንብ፡- አየር ሃይል
– መኩሪያ፡- ማዕከላዊ ዕዝ
ፌዴረሽኑ አዲስ መዋቅር ብሎ ያወጣው ይሄንን ነበር። በመዋቅሩ የአብዮታዊ መንግስት
ጫናና ጣልቃ ገብነት በግልፅ ይታይ ነበር።
የሆነ ሆኖ የ1971 ውድድር በአራት-የከነማ ፣ በሶስት-የመኢሰአማ፣ በአምስት-ወታደራዊ ፣ በአንድ-የተማሪዎች ወካይ (ከፍተኛ ትምህርት ኮሚሽን በኋላም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ቡድኖች ውድድሩ ተጀመረ።
እጅጉን በሚወዳቸው ቡድኖች መፍረስ በጣም አዝኖ የነበረው ተመልካች ከስታዲዮም ራቀ። በተለይም በጣም ብዙ የቅዱስ ጊዮርስ ደጋፊዎች ስታዲዮም መግባት አቆሙ። ብዙዎቹ ጨዋታዎች በቁጥር አነስተኛ ተመልካች ይታዩ ጀመር። መቼም ጊዜው ለአመፅ ከባድ ሆኖ እንጂ እግርኳስ ወዳዱ ደጋፊና ተመልካች በደንብ ያምፅ ነበር። ይሁን እንጂ ቢያምፅ የሚደርስበትን ስለሚያውቅ አኩርፎ ቤቱ በመቅረት ተቃውሞውን ገለፀ። የ1971 ውድድር በዚህ መንገድ ተፈፀመ። የመኢሰማው ተወካይ ወደፊት የሸዋ ሻምፒዮናን አሸነፈ።
በቀጣዩ በ1972 ግን ብዙውን ተመልካች በተለይም አመዛኙን የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ ወደ ስታዲዮም የመለሰ ተግበር ተከናወነ፡፡ ይህንን ጉዳይ በሌላ ርዕስ በሚቀጥለው ጽሁፍ እመለስበታለሁ።
(ለዛሬው ፅሁፌ የተጠቀምሁበትን የቅዱስ ጊዮርጊስን ቡድን ፎቶ የሰጠኝ ገነነ መኩሪያ ነው። ሁሌም ስለ ቅነነቱ፣ ስለ መልካም ምክሩና ማበረታቸው በጣም ላመሰግነው እወዳለሁ። ለዚህ ጽሁፍ የሚሆን ባለቀለም ፎቶ የላከልኝን ጌዲዮን ሥዩምንም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡)
ስለ ፀሃፊው
ጸሃፊው በአዲስ አበባ ስታዲዮም አካባቢ ያደገና ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1981 ዓ.ም ድረስ የተደረጉ የዚያን ዘመን የሃገራችን እግርኳስ ጨዋታዎችን በአካል ተገኝቶ የተመለከተ፣ የጨዋታዎቹን አጠቃላይ ገጽታዎች በጥልቀትና በስፋት የሚያስታውስ እግርኳስ አፍቃሪ ነው፡፡ ከ1981 ዓ.ም በኋላ ነዋሪነቱን በአሜሪካ አገር ቢያደርግም አሁንም ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሃገሩን እግር ኳስ ከመከታተል ወደ ኋላ ብሎ አያውቅም፡፡