እድለኛ ያልነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከአራት ተከታታይ ድሎች በኋላ ከመከላከያ ጋር ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጨረሻው የጨዋታ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን ከረታውን ምርጥ 11 ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ ሳያደርጉ በዛሬው ጨዋታ ሲጠቀሙ በአንፃሩ መከላከያዎች ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ከተረታው ስብስብ ላይ የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገዋል በዚህም ተከላካይ መስመር ላይ ብሩክ ሰሙ እና አሚኑ ነስሩን አስወጥተው በምትካቸው ገናናው ረጋሳ እና ልደቱ ጌታቸውን በመጠቀም የዛሬውን ጨዋታ አድርገዋል።
ፈጣን አጀማመርን ባስመለከትን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ ጥረት በማድረግ ጨዋታውን የጀመሩ ሲሆን ቀስ በቀስ ግን ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተለይ አቤል ያለው በተሰለፈበት የቀኝ መስመር በኩል ተደጋጋሚ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ተመልክተናል።
እምብዛም የጠሩ የግብ ዕድሎችን ባላስመለከትን ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የጨዋታውን የመጀመሪያውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ለማድረግ 21 ደቂቃ ለመጠበቅ ተገደዋል ፤ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ወደ ኋላ ተስቦ የተቀበለውን ኳስ በፍጥነት ከተከላካዮች ጀርባ ለመሮጥ ለተዘጋጀው የዓብስራ ተስፋዬ ያደረሰውን እና ተጫዋቹ ወደ መሀል ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ አቤል ያለው ከሳጥን ውስጥ ወደ ግብ የላከውን ኳስ ክሌመንት ቦዬ በሚገርም ሁኔታ አድኖበታል።
በመጀመሪያው አጋማሽ መከላከያዎች በተለይ የኋላ አራት ተከላካዮቻቸውን ለግብ ክልላቸው ቀርበው እንዲጫወቱ በማድረግ እንዲሁም መሀል ሜዳ ላይ ደግሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ አማካዮች ምቾት እንዳይሰማቸው በማድረግ ፍፁም የተዋጣለት አጋማሽን አሳልፈዋል ፤ በዚህም መነሻነት ቅዱስ ጊዮርጊስ በአጋማሹ በቀሪዎቹ ደቂቃዎች የፈጠሯቸው ዕድሎች ከክፍት ጨዋታ ይልቅ ከቆመ ኳስ የተገኙ ነበሩ።
በ32ኛው ደቂቃ ሄኖክ አዱኛ ወደ ቀኝ ካደላ አቋቋም ያሻማውን የቅጣት ምት ኳስ ጋቶች ፖኖም ገጭቶ የሞከራት እንዲሁም በ40ኛው ደቂቃ ሄኖክ አዱኛ ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ልማደኛው ፍሪምፖንግ ሜንሱ ሳይጠበቅ ወደ ቅርቡ ቋሚ በማምራት የገጫትን አደገኛ ኳስ እንዲሁም ጋናዊው የመከላከያ ግብ ጠባቂ ክሌመንት ቦዬ በግሩም ቅልጥፍና አድኖባቸዋል።
በአጋማሹ መከላከያዎች ከመከላከል ባለፈ በተወሰኑ አጋጣሚዎች ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሳጥን በተለይ መሀል ሜዳ ላይ ከሚነጠቁ ኳሶች ለመፍጠር ቢጥሩም ቡድኑ በማጥቃት ወቅት በቁጥር ማነሱን ተከትሎ እነዚህን ውስን አጋጣሚዎች መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል።
በመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጋቶች ፖኖም ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ አማኑኤል ገ/ሚካኤል በግንባሩ በመግጨት ያደረጋት ሙከራ በግቡ አግዳሚ መክናበታለች።
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮም በተወሰነ መልኩ በማጥቃት ረገድ የተነቃቃ መከላከያን ብንመለከትም በጥቅሉ እንደ መጀመሪያው ሁሉ የቅዱስ ጊዮርጊስ የበላይነትን የተመለከትንበት አጋማሽ ነበር።
በ52ኛው ደቂቃ ላይ የዓብስራ ተስፋዬ ከሳጥን ጠርዝ ያደረሰውን ኳስ አማኑኤል ገብረሚካኤል ከሳጥን ውጭ በቀጥታ ወደ ግብ የላካት እና ክሊመንት ቦዬ ያዳነበት እንዲሁም በ58ኛው ደቂቃ አማኑኤል ገብረሚካኤል ከመከላከያ ሳጥን የግራ ወገን ወደ ውስጥ ሰብሮ ከገባ በኋላ አመቻችቶ ያቀበለው ኳስ አቤል ያለው ጋር ብትደርስም አቤል ሚዛኑን ባለመጠበቁ የተነሳ ሳይጠቀምበት ቀረ እንጂ ቡድኑን መሪ ለማድረግ የቀረበች አጋጣሚ ነበረች።
በቁጥር በርከት ብሎ መከላከሉን የቀጠለውን የመከላከያን የመከላከል አደረጃጀት በክፍት ጨዋታ ለማስከፈት የተቸገሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከቆሙ ኳሶች መከላከያን በተደጋጋሚ ሲፈትኑ ተመልክተናል።
በ70ኛው ደቂቃ ሄኖክ አዱኛ ወደ ግራ ካደላ አቋቋም ያሻማውን ኳስ ፍሪምፖንግ ሜንሱ በግንባር ገጭቶ ወደ ግብ ቢልክም ኳሷን የመከላከያው ግብ ጠባቂ ክሌመንት ቦዬ ሲያድን ኳሷ ከመስመር ብታልፍም በዕለቱ የመስመር ዳኛ እና ዋና ዳኛ ሳትፀድቅ በመቅረቷ ጨዋታው 0-0 በሆነ ውጤት ሊቀጥል ችሏል።
ታድያ አሁንም የመከላከያን ግብ መጎብኘታቸውን የቀጠሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ72ኛው ደቂቃ ሄኖክ አዱኛ ከቀኝ መስመር ያሻማውን
የቆመ ኳስ ፍሪምፖንግ ሜንሱ ዳግም በግንባሩ የሞከረው ኳስ የግቡ አግዳሚን ገጭታ ወደ ውጭ ወጥታበታለች።
ከዚህ በኋላ በነበሩት የጨዋታ ደቂቃዎች የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች የጨዋታ ደቂቃው በገፋ ቁጥር ይበልጥ የማጥቃት አቅማቸው ተቀዛቅዞ የተመለከትን ሲሆን በእነዚሁ የመጨረሻ ደቂቃዎች ደግሞ የመከላከያ ተጫዋቾች በአንፃሩ በተደጋጋሚ ሜዳ ላይ በመውደቅ የጨዋታውን ሂደት ለማስተጓጎል ያደረጉትን ጥረት ተከትሎ ጊዮርጊሶች በከፍተኛ ብስጭት ስሜት ውስጥ በመግባታቸው ውሳኔዎቻቸው ሲበላሹ አስውለናል።
በጨዋታው የመጨረሻ ቅፅበት ጊዮርጊሶች ከራሳቸው የግብ ክልል በረጅሙ ከተሻማ የቅጣት ምት ተጨማሪ የመጨረሻ የግብ ማግባት አጋጣሚ ቢፈጥሩም ምኞት ደበበ ያደረገውን ሙከራ በጨዋታው ደምቆ የዋለው ክሊመንት ቦዬ አድኖበታል።
ጨዋታው ያለ ግብ በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ነጥባቸውን ወደ 41 በማሳደግ ሊጉን መምራታቸውን ሲቀጥሉ መከላከያዎች ደግሞ በ20 ነጥብ አሁንም 12ኛ ደረጃ ላይ ፀንተዋል።