ሲዳማ ቡና በአዲሱ ተጫዋቹ ሳላዲን ሰዒድ ሐት-ትሪክ ታግዞ ሰበታን በማሸነፍ በጊዜያዊነት ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ብሏል።
ባሳለፍነው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና ሁለት ለምንም ተረተው የነበሩት ሰበታ ከተማዎች ሦስት ነጥብ ካስረከቡበት ጨዋታ ሁለት ተጫዋቾችን ለውጠዋል። በዚህም በቅጣት ምክንያት ከጨዋታው ውጪ የሆነው ጌቱ ኃይለማርያምን በአለማየሁ ሙለታ እንዲሁም ሳሙኤል ሳሊሶን በቢያድግልኝ ኤሊያስ ለውጠዋል። ቀጥተኛ የዋንጫ ተፎካካሪው ሀዋሳ ከተማን ሦስት ለአንድ አሸንፈው የመጡት ሲዳማ ቡናዎችም በተመሳሳይ ሁለት ለውጦችን አከናውነዋል። በለውጦቹም በቀይ ካርድ ምክንያት የማይኖረው ፍሬው ሰለሞን እና ደግፌ ዓለሙ በተመስገን በጅሮንድ እና አማኑኤል እንዳለ ተተክተዋል።
ጨዋታው ገና እንደተጀመረ ገና አንድ ደቂቃ ሳይሞላ ሲዳማ ቡና ግብ አስቆጥሯል። ሰበታዎች በራሳቸው ሜዳ እየተቀባበሉ የነበሩትን የመጨረሻ ኳስ የደረሰው ተከላካዩ አንተነህ ተስፋዬ ኳሱን ከተቆጣጠረው በኋላ እግሩ ላይ ባላስፈላጊ ሁኔታ ሲያቆየው ሲዳማን በአምበልነት እየመራ የነበረው ሳላዲን ሰዒድ ደርሶ በመንጠቅ ከግቡ መረብ ጋር ቀላቅሎታል። ሳይደናገጡ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የጣሩት ተመሪዎቹ ሰበታዎች ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ዱሬሳ ሹቢሳ በተከላካዮች መካከል ከበኃይሉ ግርማ የተላከለትን ኳስ ለመጠቀም ጥቶ ሳይደርስበት ቀርቷል።
ኳሱን ከሲዳማ በተሻለ እያንሸራሸሩ መጫወት የጀመሩት ሰበታ ከተማዎች ግቡ በራሳቸው ስህተት ቢገኝም ሳይደናገጡ በጥሩ እርጋታ እየተጫወቱ በ11ኛው ደቂቃ የሰላ ጥቃት በዴሪክ ኒስባምቢ አማካኝነት ሰንዝረው ለጥቂት ወጥቶባቸዋል። የሚፈልጉትን በጊዜ ያገኙት ሲዳማዎች በበኩላቸው ኳሱን ለሰበታ ቢለቁም ፈጣን የመልሶ ማጥቃቶችን እንዲሁም ከሳጥን ውጪ የሚመቱ ኳሶችን በመጠቀም መሪነታቸውን ለማሳደግ ተንቀሳቅሰዋል። በ29ኛው ደቂቃም ተሳክቶላቸው ሁለተኛ ግብ አስቆጥረዋል። በዚህም የቀኝ መስመር ተከላካዩ አማኑኤል እንዳለ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ወደ ሳጥን ይዞ የገባውን ኳስ መሬት ለመሬት ሲያሻማው ሳላዲን አግኝቶት በቀኝ እግሩ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ አድርጎታል።
በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ሰበታ በአጥቂው ኒስባምቢ አማካኝ ሁለት ጥሩ ዕድሎችን ፈጥረው ነበር። በቅድሚያ በ38ኛው ደቂቃ አጥቂው ከሳጥን ውጪ ጊት ጋትኩት የተሳሳተውን ኳስ ተረክቦ በቀጥታ መቶ ተክለማርያም ሻንቆ ሲያድነው ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ከዱሬሳ ሹቢሳ የተሻማውን ኳስ እንደምንም ታግሎ አግኝቶ ወደ ግብ ልኮት ለጥቂት ወጥቶበታል። አጋማሹም በሲዳማ ቡና ሁለት ለምንም መሪነት ተጠናቋል።
በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሲዳማ ቡና ጨዋታውን ለመቆጣጠር የሚያስችል ለውጥ ሲያደርግ ሰበታ ከተማ ደግሞ የግብ ዕድሎችን በተሻለ ለማግኘት የሚያስችል የተጫዋች ቅያሪ አከናውኗል። በ53ኛው ደቂቃም የሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ሙከራ ተስተናግዶ ነበር። በዚህም በረጅሙ የተላከን ኳስ ተጨራትፎ የደረሰው የሰበታው አምበል እና አጥቂ ፍፁም ገብረማርያም ኳሱን በጥሩ ሁኔታ ቢመታውም የግራ ቋሚውን ታኮ ወጥቶበታል። ሰበታዎች ከደቂቃ በኋላም የቅጣት ምትን መነሻ ባደረገ ኳስ ሌላ ዕድል ፈጥረው ነበር።
በመጀመሪያው አጋማሽ የተወሰደባቸውን የኳስ ቁጥጥር በዚህ ክፍለ ጊዜ ያገኙት ሲዳማዎች በ63 እና 65ኛው ደቂቃ በሀብታሙ ገዛኸኝ እንዲሁም ዳዊት ተፈራ አማካኝነት መሪነታቸውን ለማስፋት ጥረው ባይሳካላቸውም በ67ኛው ደቂቃ የመዓዘን ምትን መነሻ ባደረገ ኳስ ግብ ሊያስተናግዱ ተቃርበው የግብ ዘቡ አድኗቸዋል። በ72ኛው ደቂቃ ግን አንጋፋው አጥቂ ሳላዲን ሦስታ የሰራበትን ጎል አስቆጥራል። በተጠቀሰው ደቂቃም በቀኝ የሳጥኑ ክፍል ራሱን ነፃ አድርጎ ቆሞ የነበረው ሀብታሙ ወደ ግብ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂው ምንተስኖት ሲተፋው ሳጥን ውስጥ የነበረው ሳላዲን በአንድ ንክኪ ግብ አድርጎታል። ሰበታ ማስተዛዘኛ የሚሆነውን ጎል ለማግኘት በ89ኛው ደቂቃ በሳሙኤል ሳሊሶ የቅጣት ምት ቢሞክርም ሳይሳካለት ቀርቷል። ጨዋታውም በሲዳማ አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።
ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና በጊዜያዊነት በ33 ነጥቦች ከነበረበት አምስተኛ ደረጃ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ሲል ሰበታ ከተማ ደግሞ የግብ ዕዳው ላይ ሁለት ጨምሮ በአስራ ሁለት ነጥቦች የነበረበት የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ፀንቶ ተቀምጧል።