ቅድመ ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ ከ ጅማ አባ ጅፋር

በወራጅ ቀጠናው ተጠባቂ በሆነው ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

ደካማ የውድድር ዓመት እያሳለፉ የሚገኙት ድሬዳዋ እና ጅማ በአደጋው ዞን ውስጥ ያሉበትን ሁኔታ ለማሻሻል የስድስት ነጥብ ጨዋታ ያደርጋሉ። ባሳለፍነው ሳምንት ወራጅ ቀጠናውን የተቀላቀለው ድሬዳዋ ከተማ ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ ድል ከቀናው ቦታውን በድጋሚ አዲስ አበባ ከተማ የሚያስረክብበት ዕድል ይፈጠራል። ከሦስት ነጥቦች ከራቁ አምስት ዘጠና ደቂቃዎች ላለፋቸው ጅማዎች ደግሞ የደረጃ መሻሻል ባያመጣም ከአደጋው ወደ መውጫ በር ሊያስጠጋቸው ይችላል።

ሁለቱም ቡድኖች በውጤት አይሳካላቸው እንጂ ለኳስ ቁጥጥር ያደላ የጨዋታ ምርጫ እንዳላቸው ሜዳ ላይ በግልፅ ያሳያሉ። በዚህ የጨዋታ ምርጫ የተሻለ አፈፃፀም እያሳዩ የሚገኙት ግን ጅማ አባ ጅፋሮች ናቸው።

የቡድኑ የኳስ ቁጥጥር እና የማጥቃት ሂደት በየጨዋታው መሻሻሎችን እያሳየ የከረመ ሲሆን በፋሲል ከነማው ጨዋታ ይህ የቡድኑ መስመር እየያዘ መምጣት ዋጋ ሊከፍለው ተቃርቦ ነበር። ከተጋጣሚው አንፃር አማካይ ክፍል ላይ ካለው የተጨዋቾች ጥራት ብልጫ አንፃርም ሲታይ ነገም የኳስ ቁጥጥር ብልጫውን መውሰዱ የሚቀር አይመስልም። ይህ ነጥብ በመጨረሻው ጨዋታ በመስመር ተመላላሾቹ የማጥቃት ትጋት መታጀቡን ስናስብ ደግሞ ጅማ የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩም የተሻለ ግምት የሚያሰጠው ይሆናል።

ድሬዳዋ ከተማ አሁንም ቢሆን ኳስ መስርቶ የመውጣት ፍላጎቱ በመዋቅርም ሆነ በስብስብ ደረጃ ሲያዋጣው እየታየ አይገኝም። በቁጥጥር የተሻለ የሚሆንባቸው አጋጣሚዎችም ከተጋጣሚ ድክመት የመነጩ መሆናቸው ይጎላል። ከምንም በላይ እስካሁን በአስር ቁጥር ቦታ ላይ ከአምስት የሚበልጡ ተጫዋቾችን ሲቀያይር መታየቱ ግርምትን የሚያጭር ነው። የጨዋታ ምርጫው እንዳለ ቢሆን እንኳን ቢያንስ መዋቅሩን በሁለት ስምንት ቁጥሮች ወደመጠቀም እንዲያመጣው ይጠበቅ ነበር። ሆኖም ቡድኑ አሁንም በ4-2-3-1 የቀጠለ ሲሆን የተሻለ አስፈሪነት የሚታይበት ግን ከመስመር በሚነሱ ኳሶች ነው። በመሆኑም ነገ በአጨዋወት ምርጫ ረገድ የተሻለ ዕድገት ላይ የሚገኘው ተጋጣሚውን ለመፈተን የሚያዋጣው ቀጥተኝነት የቀላቀለ አቀራረብ እንደሆነ ይታመናል።

ቡድኖቹ በተመሳሳይ ደረጃ ላይ መገኘታቸው ሁለቱም የማጥቃት ድፍረታቸው ጨምሮ ብርቱ ፋክክር ሊያደርጉ የሚችሉበት ይሆናል። በድሬ በኩል ከቀኝ በእንየው ካሳሁን እና ጋዲሳ መብራቴ እንዲሁም ከግራ የአማረ በቀለ ጥሩ ኳሶች ሲጠበቁ ይህም ከጅማ መስመር ተመላላሾች የሚሰጠው ምላሽ በቦታው አይን የሚስብ ፍልሚያን ይፈጥራል። የጅማ አማካይ መስመር ደግሞ ከድሬ የዳንኤል ጥምረቶች ጋር ይሚያደርጉት ፍልሚያ እንዲሁ ተጠባቂ ይሆናል። በግለሰብ ደረጃ ግን የጅማው ግብ ጠባቂ አላዛር ማርቆስ ተከታታይ ድንቅ ብቃት ነገም የትኩረት ማዕከል መሆኑ የሚቀር አይመስልም።

ጉዳት በሌለበት ድሬዳዋ ከተማ በኩል አብዱለጢፍ መሐመድን በሁለት ቢጫ ካርድ ቅጣት ጨዋታው ሲያልፈው በአንፃሩ መሣይ ጳውሎስ ደግሞ ከቅጣት መልስ ለቡድኑ ግልጋሎት ይሰጣል። ጅማ አባ ጅፋር በቅጣት ሙሴ ካበላን የሚያጣው ሲሆን በጉዳት ደግሞ ኢያሱ ለገሰ በስብስቡ ውስጥ አይኖርም።

ማኑሄ ወ/ፃዲቅ የጨዋታው ዋና ዳኛ ሲሆኑ ሙስጠፋ መኪ እና ፋንታሁን አድማሱ ረዳት ዳንኤል ግርማይ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆነው ተመድበዋል። 

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ድሬዳዋ እና ጅማ ከሰባት ግንኙነታቸው በአንዱ ብቻ አቻ በተለያዩበት ታሪካቸው ድሬዳዋ አምስት ጊዜ ጅማ ደግሞ አንድ ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። በጨዋታዎቹ ድሬዎች 12 ግቦችን ሲያስቆጥሩ ጅማዎች ደግሞ አምስት ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ጅማ አባ ጅፋር (3-6-1)

አላዛር ማርቆስ

አስጨናቂ ፀጋዬ – የአብስራ ሙሉጌታ – ወንድማገኝ ማርቆስ

እዮብ ዓለማየሁ – አድናን ረሻድ – ዳዊት እስጢፋኖስ – መስዑድ መሐመድ – ቦና ዓሊ – ሱራፌል ዐወል

መሐመድኑር ናስር

ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)

ፍሬው ጌታሁን

እንየው ካሳሁን – መሳይ ጳውሎስ – አውዱ ናፊዩ – አማረ በቀለ

ዳንኤል ኃይሉ – ዳንኤል ደምሴ

ጋዲሳ መብራቴ – አብዱርሀማን ሙባረክ – ሙኸዲን ሙሳ

ማማዱ ሲዲቤ