ከሳምንቱ ተጠባቂ መርሐ-ግብሮች መካከል አንዱ የሆነውን ፍልሚያ እንደሚከተለው ዳሰናል።
ባሳለፍነው ሳምንት ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር የታረቁት ኢትዮጵያ ቡናዎች ተከታታይ ድል በማስመዝገብ ካሉበት የደረጃ ሰንጠረዡ አጋማሽ ሽቅብ ለመውጣት እንደሚጥሩ ሲታሰብ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚገኙት ወላይታ ድቻዎች ደግሞ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ እንዲሁም ባለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ያጡትን ድል ለማግኘት ጠንክረው እንደሚጫወቱ ይገመታል።
ሰበታ ከተማን ሁለት ለምንም አሸንፎ ለነገው ጨዋታ እየተዘጋጀ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና በጨዋታው በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ከሚገኘው ቡድን ጋር እንደ መጫወቱ ሙሉ ለሙሉ የሚያስብል ብልጫ ባይኖረውም ሦስት ነጥብ ማግኘቱ መልካም ነው። በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ዘለግ ያሉ ደቂቃዎችን በወሳኝ ሜዳዎች ብልጫ ተወስዶበት በርከት ያሉ የግብ ማግባት ሙከራዎችን ሲያስተናግድ ነበር። በወራጅ ቀጠናው ከሚገኙት ሦስቱ ክለቦች ውጪ ሦስተኛው ብዙ ግብ ያስተናገደው ስብስቡ በጨዋታው በድምሩ ከተሰነዘረበት አጠቃላይ 19 ሙከራዎች አንዱንም አለማስተናገዱ ትልቅ ነገር ነው። በተለይ ደግሞ 240 ደቂቃዎችን ብቻ በሊጉ የተጫወተው የግብ ዘቡ በረከት አማረ ከቆይታ በኋላ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ገብቶ ያሳየው ብቃት የጨዋታው ውጤት እንዳይለወጥ አድርጓል። የሆነው ሆኖ የነገው ተጋጣሚ ወላይታ ድቻ የአጨዋወት መንገድ ከሰበታ ትንሽ ለየት ስለሚል የተለየ የጨዋታ ዝግጅት ቡናማዎቹ ይጠበቅባቸዋል።
ተለምዷዊው የኢትዮጵያ ቡና ከኳስ ጋር የማሳለፍ ፍላጎት ነገም እንደሚደገም ሲጠበቅ ጠጣሩን የወላይታ ድቻ የኋላ መስመር ማስከፈት ግን ከባዱ ፈተና እንደሚሆን ይገመታል። ቡድኑ ከዚህ ቀደም ዝቅ ብለው በቁጥር በዝተው የሚከላከሉ ተጋጣሚዎች ሲያጋጥሙት መጠነኛ የግብ ምንጭ ማግኛ እጥረት ያለበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞም በተጫዋቾች የግል ብቃት በልጦ መገኘት (Qualitative Superiority) የሚያስፈልግ ይሆናል። በማጥቃቱ ብቻ ሳይሆን በመከላከሉም ፈጣኑን የድቻ የመልሶ ማጥቃት እና ሽግግር አጨዋወት ማምከኛ ዘዴ ሊገባቸው ግድ ይላል።
በዛሬው ዕለት የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ መጣሉን ያየው ወላይታ ድቻ የሰባት ነጥቡን ልዩነት ወደ አምስት ለማጥበብ እንዲሁም በጊዜያዊነት በሲዳማ ቡና የተነጠቀውን የሁለተኛ ደረጃ መልሶ ለማግኘት ከቡና የሚጠብቀውን ፈተና ማለፍ ይጠበቅበታል። በግብ በተንበሸበሸው ያሳለፍነው ሳምንት ብቸኛ የአቻ ውጤት ከአዳማ ከተማ ጋር ያስመዘገበው ድቻ እውነተኛ የዋንጫ ተፎካካሪ ከሆነ ከሁለቱ ጨዋታዎች ከጣላቸው አራት ነጥቦች አገግሞ ድሎችን ማስመዝገብ አለበት። በአዳማ ቆይታው ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ 9 ሰዓት ላይ ጨዋታ ያደረገው ቡድኑ ከአየር ፀባዩ ጋር ተያይዞ በሚመስል መልኩ መጠነኛ የእንቅስቃሴ መውረድ ቢያሳይም በአዳማው ጨዋታ ግን ከወትሮ በተለየ ኳሱን ለመቆጣጠር ፍላጎት ሲያሳይ አስተውለናል። ይህ ፍላጎት ነገ እንደማይኖር ቢታሰብም መቀዛቀዝ ያሳዩበት የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ግን ከፍ ብሎ መከወን ይገባቸዋል። የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ኳስ እንደተነጠቁ ያላቸው የቦታ አጠባበቅ ችግርን ለመጠቀም ደግሞ ይህ ፈጣን ሽግግር አስፈላጊ ነው።
ወላይታ ድቻ ካለበት ደረጃ አንፃር በተደጋጋሚ የግብ ማግባት ሙከራዎችን እያደረገ ግቦችን አለማስቆጠሩ ብዙዎችን ቢያስገርምም ያለፉትን አስራ ሦስት ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ከአንድ ጎል በላይ ማስቆጠሩ ጎል ፊት መጠነኛ መሳሳት እንዳለበት ይመሰክራል። የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች የነበረው ስንታየሁ መንግስቱ መጎዳቱ ደግሞ በእንቅርት ላይ አይነት ነገር ሆኖበታል። ይህ ቢሆንም ግን ከፊት የሚጫወቱት ቃልኪዳን እና ምንይሉ ፍጥነት በኳስ ምስረታ ወቅት እፀፅ ለማይጠፋቸው የቡና ተከላካዮች የራስ ምታት መሆኑ አይቀሬ ነው። ከኳስ ውጪ ደግሞ ግጥግጥ ብሎ በመከላከል ለቡና ተጫዋቾች ምቾት ላለመስጠት እንደሚጥሩ ቀድሞ መናገር ይቻላል።
ኢትዮጵያ ቡና ነገ በቅጣት ምክንያት የሚያጣው ተጫዋች ባይኖርም በጉዳት ምክንያት ግን ሦስት ተጫዋቾች ስብስብ እንደማይኖሩ ተመላክቷል። ተጫዋቾቹም ወንድሜነህ ደረጄ፣ አቤል እንዳለ እና የአብቃል ፈረጃ ናቸው። ባሳለፍነው ሳምንት ጉዳት ላይ የነበረው የመስመር ተከላካዩ ኃይሌ ገብረትንሣኤ ግን በማገገሙ በጨዋታ እንደሚሳተፍ ተገልጿል። ወላይታ ድቻ በበኩሉ አሁንም የወሳኝ አጥቂው ስንታየሁ መንግስቱን ግልጋሎት በጉዳት ምክንያት አያገኝም። ከስንታየሁ በተጨማሪ ደግሞ እድሪስ ሰዒድ ቅጣቱን ባለማገባደዱ ከጨዋታው ውጪ ነው።
ይህንን ጨዋታ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ በመሐል ፋሲካ የኋላእሸት እና አማን ሞላ በመስመር እንዲሁም አባይነህ ሙላት ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት እንደሚመሩት ታውቋል።
እርስ በርስ ግንኙነት
– በ15 ጊዜ የክለቦቹ የቀደመ ግንኙነት 7 የአቻ ውጤቶች ከፍተኛውን ድርሻ ይዘዋል። ወላይታ ድቻ አምስቱን ሲረታ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ሦስቱን አሸንፏል። በእነዚህ 15 ጨዋታዎች አጠቃላይ ከተቆጠሩት 25 ጎሎች ድቻ 13 ቡና ደግሞ 12ቱን አስቆጥሯል።
ግምታዊ አሠላለፍ
ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)
አቤል ማሞ
አስራት ቱንጆ – አበበ ጥላሁን – ገዛኸኝ ደሳለኝ – ሥዩም ተስፋዬ
ሮቤል ተክለሚካኤል – አማኑኤል ዮሐንስ – ታፈሠ ሰለሞን
ሚኪያስ መኮንን – አቡበከር ናስር – ዊሊያም ሰለሞን
ወላይታ ድቻ (4-3-3)
ፅዮን መርዕድ
በረከት ወልደዮሐንስ – አንተነህ ጉግሳ – መልካሙ ቦጋለ – አናጋው ባደግ
ሀብታሙ ንጉሴ – ንጋቱ ገብረስላሴ – አበባየሁ አጪሶ
ያሬድ ዳዊት – ምንይሉ ወንድሙ – ቃልኪዳን ዘላለም