የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ9ኛ ሳምንት የዛሬ ጨዋታዎች ውሎ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ዘጠነኛ ሣምንት ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች ሲጠናቀቅ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና መከላከያ ድል ቀንቷቸዋል።

በቶማስ ቦጋለ

የምንትዋብ ዮሐንስ ብቸኛ ግብ ኤሌክትሪክን ባለድል አድርጋለች

በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ8ኛ ሳምንት መከላከያን 3-1 ከረታበት ስብስብ የአንድ ተጫዋች ብቻ ለውጥ ሲያደርግ መስከረም ኢሳያስ ዘለቃ አሰፋን ተክታ ገብታለች። ጌዴኦ ዲላዎችም ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ያለ ምንም ግብ አቻ ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የአንድ ተጫዋች ብቻ ቅያሪ ሲያደርጉ አልማዝ ብርሃኔ በማማየ ዘገየ ቦታ ተሰልፋለች።

በጣም ቀዝቃዛ እና ለጨዋታ ምቹ በሆነ የአየር ንብረት መደረግ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ በኳስ ቁጥጥሩ ጌዴኦ ዲላዎች የተሻሉ የነበሩ ሲሆን በግብ ሙከራ ግን አትዮ ኤሌክትሪኮች ብልጫ ወስደዋል። ጨዋታው በጀመረ 2ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታም እሸቱ ከዓይናለም አሳምነው ተሻግሮላት ከረጅም ርቀት በቀኝ መስመር ያደረገችው ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ኳስ ሲነጥቁ ቶሎ ቶሎ ወደግብ መድረስ የሚፈልጉት ኤሌክትሪኮች የማጥቃት ጨዋታቸውን የጀመሩበት ሙከራ ነበር።

በተደጋጋሚ በዓይናለም አሳምነው ፣ ቤተልሔም አስረሳኸኝ ፣ ሠላማዊት ጎሣየ እና ሀብታም እሸቱ የግብ ዕድል ለመፍጠር የሞከሩት ኤሌክትሪኮች ተሳክቶላቸው 29ኛው ደቂቃ ላይ ዓይናለም አሳምነው ወደግብ ሞክራው የቀኙን ቋሚ ገጭቶ የተመለሰውን ኳስ ነጻ ሆና ያገኘቸው ምንትዋብ ዮሐንስ ጎል አስቆጥራ ቀዳሚ አድርጋችዋለች። ከግቧ መቆጠር በኋላ የኳስ ፍሰቱን ጥሩ ስታንቀሳቀስ በነበረችው በቤተል ጢባ በኩል ያደረጉት ጌዲኦ ዲላዎች በ ማርያም ታደሠ እና አዲስ ንጉሤ የተለያዩ የግብ ዕድሎች መፍጠር ቢችሉም ውጤታማ ሳይሆኑ ቀርተው የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ በትንሹ ቀዝቀዝ ያለና የሚቆራረጡ ቅብብሎች የበዙበት አጋማሽ ነበር። ሆኖም 57ኛው ደቂቃ ላይ ዓይናለም አሳምነው ከዙሌይካ ጁሃር ተቀብላ ወደ ግብ ድንቅ ሙከራ አድርጋ የግቡ አግዳሚ የመለሰባት አጋጣሚ ኤሌክትሪኮችን ያስቆጨች ነበረች። በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት ቤተል ጢባ እና አልማዝ ብርሃኔ በጥሩ ቅብብል ይዘውት የሄዱትና ቤተል ጢባ ወደግብ ሞክራው ግብ ጠባቂዋ ያዳነችው ኳስ በጌዴኦ ዲላ በኩል የተሻለው የመጀመሪያ ሙከራ ነበር። ዙሌይካ ጁሀር ከምንትዋብ ዮሐንስ የተቀበለችውና ከረጅም ርቀት ሞክራው የግቡን አግዳሚ ገጭቶ የወጣው ኳስ ሌላው ኤሌክትሪኮችን ያስቆጨ አጋጣሚ ነበር።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ተጭነው የተጫወቱት ጌዴኦ ዳላዎች 72ኛው ደቂቃ ላይ አልማዝ ብርሃኔ ከጽዮን ማንጁራ የተቀበለችውና ድንቅ አድርጋ የሞከረችው ኳስ የላይኛውን አግዳሚ ገጭቶ ተመልሷል። ይሄም ከጨዋታው ነጥብ ይዘው ለመውጣት የታገሉትን ጌዲኦ ዲላዎች ያስቆጨ ትልቅ አጋጣሚ ነበር። በቀኙ የሜዳ ክፍል ቅጣት ምት ያገኙት ጌዴኦ ዲላዎች በአዲስ ንጉሤ የግብ ዕድል መፍጠር ቢችሉም ሳይጠቀሙበት ቀርተው ጨዋታው በኤሌክትሪክ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎም ተከታታይ አምስት ጨዋታዎች ያሸነፈው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ18 ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ጌዴኦ ዲላ በነበረበት 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

መከላከያ ከኋላ በመነሳት ባህር ዳርን አሸንፏል

08:00 ላይ በተደረገው ጨዋታ ባህር ዳር ከተማዎች በስምንተኛ ሳምንት አቃቂ ቃሊቲን ሲያሸንፉ ከተጠቀሙበት ስብስብ የአንድ ተጫዋች ለውጥ ሲያደርጉ ዝናሽ ደሣለኝ ገነት ገብረማርያምን ተክታ ገብታለች። መከላከያዎች በበኩላቸው በስምንተኛ ሳምንት በኢትዮ ኤሌክትሪክ 3-1 ሲሸነፉ ከተጠቀሙበት ስብስብ የ ሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ካሠች ፍስሃ ፣ ረሂማ ዘርጋው እና ማዕድን ሣህሉ በቤተልሔም በቀለ ፣ መቅደስ ማሞ እና ህድአት ካሱ ተተክተው ገብተዋል።

በበርካታ ተመልካቾች ታጅቦ የተደረገው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ አዝናኝ እና ጥሩ ፉክክር የታየበት ነበር። የመጀመሪያ ሙከራ በማድረግ ቀዳሚ የነበሩት ሞገደኞቹ ሲሆኑ 7ኛ ደቂቃ ላይ ሊዲያ ጌትነት ከምስር ኢብራሂም ጥሩ ኳስ ተቀብላ ግብ ጠባቂዋን አልፋ ጥሩ ሙከራ ብታደርግም ግብጠባቂዋ ተመልሳ በመድረስ በድንቅ ብቃት አድናዋለች። በአንድ ደቂቃ ልዩነት ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ የተገናኘችው የመከላከያዋ መሳይ ተመስገን ወርቃማ ዕድል አምክናለች። በምስር ኢብራሂም እና መንደሪን ታደሠ የተለያዩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የፈለጉት ሞገደኞቹ 12ኛው ደቂቃ ላይ ምስር ኢብራሂም ከሳጥን ውጪ ባስቆጠረችው አስገራሚ ጎል ቀዳሚ ሆነዋል።
ከ5 ደቂቃዎች በኋላ ረሂማ ዘርጋው ከመሳይ ተመስገን የተሻማውን ኳስ በግንባር ገጭታ ብታስቆጥርም ከጨዋታ ውጪ ተብሎ ተሽሮባታል። በሴናፍ ዋቁማ በመሳይ ተመስገን እና ረሂማ ዘርጋው ተደጋጋሚ የግብ ዕድል ለመፍጠር የሞከሩት መከላከያዎች በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ስታደርግ የነበረችው ማዕድን ሳህሉ አመቻችታ ያቀበለቻትን ኳስ መሳይ ተመስገን ግብ ጠባቂዋን አልፋ ወደግራ መስመር ይዛው ወጣ ካሻማችው በኋላ ረሂማ ዘርጋው በግንባር በመግጨት አስቆጥራለች። የመጀመሪያው አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊት ከተጋጣሚ ሳጥን አጠገብ ያገኘቸውን ቅጣት ምት ሴናፍ ዋቁማ በድንቅ ሁኔታ ብታስቆጥርም ከዳኛው ፊሽካ በፊት ተመቷል በሚል ጎሉ ተሽሮ ኳሱ ለባህርዳር ከተማ የመልስ ምት ተሰጥቶ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ በአንጻራዊነት ትንሽ መቀዝቀዝ የታየበት የጨዋታ ክፍለጊዜ ነበር። 56ኛው ደቂቃ ላይ መሳይ ተመስገን በግራ መስመር ይዛው የገባችውን ኳስ አግኝተውት የነበሩት የባህር ዳር ከተማ ተከላካዮች በስርዓት ኳሱን ባለማውጣታቸው የነሱን ስህተት የተጠቀመችው ረሂማ ዘርጋው በድኗን መሪ አድርጋለች። ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በመሳይ ተመስገን በገነት ኃይሉ እና ረሂማ ዘርጋው የተለያዩ የግብ ዕድሎች የፈጠሩት መከላከያዎች በመጨረሻ ኳስ ውጤታማ መሆን አልቻሉም። በአንጻሩ ከዕረፍት መልስ ከራሳቸው የግብ ክልል መውጣት የከበዳቸው ሞገደኞቹ አንድም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው በመከላከያ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎም መከላከያ በ 5ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ባህርዳር ከተማ በነበረበት 11ኛ ደረጃ ላይ ረግቷል።

ድሬዳዋ ከተማ እና አቃቂ ቃሊቲ ነጥብ ተጋርተዋል

10 ሰዓት ላይ የዘጠነኛ ሣምንት የመጨረሻ ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ እና በአቃቂ ቃሊቲ መካከል ሲደረግ በስምንተኛ ሣምንት አራፊ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በሰባተኛ ሣምንት ባህር ዳር ከተማን ሲያሸንፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የ ሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ባንቺርጋ ተስፋየ ፣ ብርቄ አማረ እና ሔለን መሠለን በዘቢብ ኃይለሥላሴ ፣ ጥሩየ ምስጋናው እና ቻይና ግዛቸው ተተክተው ገብተዋል። በአቃቂ ቃሊቲ በኩል በስምንተኛ ሣምንት በባህር ዳር ከተማ ከተሸነፉበት ስብስብ የአንድ ተጫዋች ብቻ ለውጥ ሲያደርጉ በሬዱ በቀለ በምሕረት ታፈሰ ተተክታ ገብታለች።

ለተመልካች አዝናኝ የነበረው እና ከተጠበቀው በላይ ፉክክር በታየበት ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ቶሎ ቶሎ ወደግብ የመድረስ ፍላጎት የታየበት ነበር። በመጀመሪያው ደቂቃዎች ላይ የተሻሉ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በ ሰርካለም ባሳ ፣ ሔለን መሠለ ፣ የካቲት መንግስቱ የተለያዩ የግብ ዕድሎችን ቢፈጥሩም ውጤታማ መሆን ግን አልቻሉም። 15ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ድንቅ ብቃት ያሳየችው ሔለን አባተ ለአቃቂ ከተማ ግብ አስቆጥራ ቡድኗን መሪ ማድረግ ችላለች። ከግቧ መቆጠር በኋላ ይበልጥ ተጭነው የተጫወቱት ድሬዳዋዎች በተደጋጋሚ የግብ ማግባት ዕድል ፈጥረው ነበር። በተለይም ሰርካለም ባሳ የአቃቂዋን ግብ ጠባቂ አልፋ ወደግብ የመታችውና ዓይናለም መኮንን በሚገርም ብቃት ያወጣችው ኳስ ድሬዎችን በመጀመሪያው አጋማሽ አቻ ሊያደርግ የሚችል እጅግ በጣም ያስቆጨ አጋጣሚ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ የማጥቃት አማራጫቸውን መጠቀም የጀመሩት ድሬዳዋዎች በተደጋጋሚ ወደግብ እየተጠጉ የግብ ዕድል በመፍጠር ጀምረውታል። 57ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ የገባችው አሥራት ዓለሙ ከትዕግሥት ዳዊት የተቀበለችውን ምርጥ የመጨረሻ ኳስ ብዙም ኃይል ባልነበረው ሙከራ እድሏን ሳትጠቀምበት ቀርታለች።

በተደጋጋሚ ከቆመ ኳስ ዕድል መፍጠር የቻሉት ድሬዳዋዎች ተሳክቶላቸው 73ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ጥሩ የተንቀሳቀሰችው ቤተልሔም ታምሩ ከረጅም ርቀት ባስቆጠረችው ድንቅ የቅጣት ምት ግብ አቻ መሆን ችለዋል።

ብዙም ሳይቆይ 82ኛው ደቂቃ ላይ ራሷ ቤተልሔም ታምሩ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝታ የሞከረችውንና ተመልሶ የመጣውን ኳስ ነፃ ሆና ያገኘችው አሥራት አለሙ አስቆጥራ ቡድኗ ከኋላ ተነስቶ እንዲመራ አስችላለች። ከሌሎች ጊዜያት በጣም ተሽለው የቀረቡት አቃቂ ቃሊቲዎች ይበልጥ ተጭነው በመጫወት 89ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ የገባችው አሶሬ ሀይሴ በድንቅ አጨራረስ ድንቅ ግብ አስቆጥራ አቻ መሆን ችለዋል። ይሄም የጨዋታው የመጨረሻ ትዕይንት ሆኖ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎም ድሬዳዋ ከተማዎች 8ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ አቃቂ ቃሊቲዎች በነበሩበት የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ይገኛሉ።