“በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት ከዚህ በኋላ ሙሉ አቅማችንን እንጠቀማለን” የወልቂጤ ከተማ ፕሬዝደንት

ወልቂጤ ከተማ በአስተዳደራዊ ችግር ምክንያት የሚነሱትን የተለያዮ ጉዳዩችን አስመልክቶ የክለቡ ፕሬዝደንት ወ/ሮ እፀገነት ፍቃዱ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሜዳ ውጭ በሚፈጠሩ የአስተዳደር ጉዳዮች ችግር ምክንያት ከሰሞኑ በርካታ ጥያቄዎች እየተነሱበት የሚገኘው ወልቂጤ ከተማን በተመለከተ ከቀናት በፊት አንድ ጥንቅር ማቅረባችን ይታወቃል። ባቀረብነው ዘገባ ክለቡ ያለበት ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ምላሽ እንዲሰጡን የክለቡን የበላይ አካላትን ለማግኘት ደጋግመን በመደወል ልናገኛቸው ብንሞክር ሳይሳካልን መቅረቱን ገልፀን ከዚህ በኋላም በዚህ ጉዳይ ላይ አመራሮቹ ያላቸውን ሀሳብ ለማስተናገድ በራችን ክፍት እንደሆነ በጠቆምነው መሠረት የክለቡ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ እፀገነት ፍቃዱ ለጥያቄዎቻችን ተከታዩን መልስ ሰጥተውናል።

ትናንት በአዳማ ከቡድኑ ተጫዋቾች ጋር የነበረው ውይይት ምን ይመስላል ?

“የክለቡ የበላይ አካላት በተገኘንበት በትናትናው ዕለት በተለያዮ ጉዳዮች ዙርያ ሰፊ ውይይት አድርገናል። የቡድኑ አባላት አለብለው የሚያነሱትን ችግሮች አድምጠናል። እኛም አግባብነት ያላቸውን ጥያቄዎቻቸውን በመቀበል ወደ ስራ እንዲገቡ እና ክለቡን ውጤታማ እንዲያደርጉ ጠንክረው እንዲሰሩ በመግለፅ በቅርቡ ለሚያነሱ ጥያቄዎቻቸው መልስ የምንሰጥ ይሆናል።”

ተጫዋቾቹ ደሞዝ ጋር በተያያዘ ለሚያነሱት ጥያቄ የክለቡ ምላሽ ምን ነበር ?

“የሁለት ወር ደሞዝ ነው የጠየቁት። ለእርሱ ምላሽ እንሰጣለን። ይህንን ነገር ለማስተካከል እየተንቀሳቀስን ባለንበት ሰዓት ነው አሁን የተገናኘነው። ተገቢነት ያለው ጥያቄ ነው ያቀረቡት። ያው በሌሎች ክለቦች የሚያጋጥም ችግር ነው እኛም ላይ የተነሳው ፤ የተለየ ነገር አይደለም። ይህ ችግር ስለተፈጠረበት ሁኔታ በእርግጥ ከተጫዋቾቹ ጋር ውይይት አድርገን ተማምነናል። እነርሱም ወደ ልምምድ ተመልሰዋል። እኛም በዚህ ሦስት ቀን ውስጥ ክፍያውን እንፈፅማለን።

የክለቡ ስራ አስፈፃሚዎችን ጨምሮ ም/ፕሬዝደንቱ ላቀረቡት የመልቀቂያ ደብዳቤ ዙርያ የእናተ ምን ምላሽ ምድነው ?

“ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። ግን የጋራ አልተደረገም። የጋራ ባልተደረገበት ሁኔታ አሁን የምለው ነገር የለም። ወደፊት የሚኖሩ ማንኛውም አይነት ነገሮች ካሉ የምናሳውቅ ይሆናል።”

አጠቃላይ በክለቡ ዙርያ የሚነሱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ በእናተ በኩል ምን ታስቧል ?

“ክለቡ ላይ እንዲህ ያሉ የፋይናስ ችግሮች ሲያጋጥሙ አዲስ አይደለም። በቀጣይ የገንዘብ አቅሙን ለማጠናከር እና ህዝባዊ ለማድረግ ሥራዎችን ለመስራት በዕቅድ የያዝናቸው ነገሮች አሉ። ያው የፖለቲካ አመራሩ በራሱ የስራ ጫና በመኖሩ ምክንያት ክለቡን በሚገባ መንገድ ደግፈነዋል የሚል ነገር የለንም። ስለዚህ አሁን በዘላቂነት ክለቡ የህብረተሰቡ መገለጫው ነው። ሁሉም የዚህን ክለብ መኖር ይፈልገዋል። በሚፈጠሩ ችግሮች ህብረተሰቡን ማስከፋት አያስፈልግም። የህዝብ ድምፅም ጆሮም ያለው ክለብ ነውና በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት ከዚህ በኋላ ሙሉ አቅማችንን እንጠቀማለን።”

ያጋሩ