ሪፖርት | ድሬዳዋ ከስምንት ጨዋታ በኋላ አሸንፏል

የሄኖክ አየለ የ88ኛ ደቂቃ ጎል ለድሬዳዋ ወሳኝ ሦስት ነጥብ ስታሳካ ጅማ አባ ጅፋር በተከታታይ በመጨረሻ ደቂቃ ጎል ለሽንፈት ተዳርጓል።

ድሬዳዋ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊሱ ሽንፈት አምስት ቅያሪዎችን አድርጓል። ተከላካይ መስመሩ ላይ ከቅጣት የተመለሰው መሳይ ጳውሎስ እና አማረ በቀለ በከድር ኸይረዲን እና የቀይ ካርድ ሰለባ በሆነው አብዱለጢፍ መሀመድ ምትክ ሲገቡ አማካይ ክፍል ላይ ዳንኤል ኃይሉ እና ብሩክ ቃልቦሬ በአዲስ ፈራሚው አባይነህ ፊኖ እና ሙኸዲን ሙሳ እንዲሁም ከፊት ማማዱ ሲዲቤ በሄኖክ አየለ ተለውጠዋል። በፋሲል ከነማ 2-1 ተሸንፎ የነበረው ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ ሁለት ቅያሪዎችን ሲያደር በተከላካይ መስመር ላይ ተስፋዬ መላኩ በወንድምአገኝ ማርቆስ ቦታ ሲሰለፍ ዳዊት እስጢፋኖስ ቀይ ካርድ በተመለከተው ሙሴ ካበላ ምትክ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ ተመልሷል።

በሁለቱም በኩል ወደ ቀኝ ያደሉ ጥቃቶችን ከጅምሩ ማሳየት የጀመረው ጨዋታ የተጋጣሚዎቹን የማጥቃት ፍላጎት ያሳየ ነበር። በሙከራ ቀዳሚ የነበሩት ጅማዎች 4ኛው ደቂቃ ላይ የግራ ተመላላሹ ሱራፌል ዐወል ከመስዑድ መሀመድ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ ሳጥን ውስጥ የመጫረሻ ዕድል ቢያገኙም የሱራፌል ሙከራ ወደ ላይ ተነስቷል።

ከወትሮው በተለየ በ4-4-2 አደራደር ጨዋታውን የጀመሩት ድሬዎች የቀጥተኝነት ባህሪ ሲታይባቸው ከጅማ ተከላካዮች ጀርባ ለመግባት መሀል ይሞክሩ ነበር። ይህ ጥረታቸው በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ ቢሆንባቸውም የጅማን የኳስ ስርጭት በማቋረጥ ቀዳሚው ሙከራ አድርገዋል። 12ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አየለ ግራ መስመር ላይ የጅማን የኳስ ምስረታ ሂደት ባቋረጠበት እንቅስቃሴ ዓባይነህ ፊኖ ሳጥን ውስጥ ጥሩ ዕድል አግኝቶ በአላዛር ማርቆስ ሲመለስበት እንየው ካሳሁን ሌላ ዕድል አግኝቶ ሲሞክር ወደላይ ተነስቶበታል።

ከፍተኛ የኳስ ቁጥጥር በእጃቸው ያደረጉት ጅማዎች ሙሉ ለሙሉ በድሬዳዋ ሜዳ ላይ አድልተው ተጫውተዋል። የድሬን ቀጥተኛ ኳሶች በማቆም ረገድ ስራ የነበረባቸው የቡድኑ ተከላካዮች ጭምር በኳስ ምስረታ ሂደት ላይ ሲሳተፉ ቢታዩም ብልጫቸውን በበቂ ሁኔታ ወደግብ ዕድል መቀየር ቀላል አልሆነላቸውም። በዚህ ረገድ 18ኛው ደቂቃ ላይ በግራ የሱራፌል እና መስዑድ ጥምረት በፈጠረው ዕድል ቦና ዓሊ በመቀጠልም መሀመድኑር ናስር ያደረጓቸው ሙከራዎች በድሬዎች ርብርብ ከሽፈዋል። ከዚህ በኋላ በድኑ ሌላ አጋጣሚ የፈጠረው 31ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን እዮብ ዓለማየሁ ጥሩ የአየር ላይ ካስ ቢያሻግርም ቦና ከግቡ ቅርብ ርቀት ላይ በግንባሩ አምክኖታል።
በቀሪዎቹ ደቂቃዎች የተጋጣሚዎቹ የማጥቃት ሂደት እየተቀዛቀዘ ሄዷል። ድሬዎች በንፅፅር በተሻለ ሁኔታ ከሜዳቸው መውጣት ቢችሉም በተለይም የተስፋዬ መላኩ ድንቅ ብቃት የቡድኑን ጥቃቶች እያቋረጠ የጅማም የኳስ ፍሰት ሌላ ንፁህ የሚባል ዕድል ሳይፈጥር ጨዋታው ተጋምሷል።

ከዕረፍት መልስ መሀል ላይ የተወሰደባቸውን የቁጥር ብልጫ ብሩክ ቃልቦሬን አና አቤል ከበደን በማሰገባት እና ወደ 3-5-2 በመምጣት ያመጣጠኑት ድሬዎች በተሻለ ንቃት ወደ ግራ መስመር ያደላ ጫና ፈጥረው በመጀመር ግብም አስቆጥረዋል። 54ኛው ደቂቃ ላይ በሁለቱ ተቀያሪዎች ቅብብል በግራ መስመር የከፈቱትን ጥቃት አቤል ከበደ አመቻችቶለት ጋዲሳ መብራቴ ጎል አድርጎታል።

ጅማዎች ከጎሉ በኋላ ከሳጥን ውጪ እና ከቆመ ኳስ ምላሽ ለመስጠት ሲሞክሩ የተሻለ በነበረው የ58ኛ ደቂቃ ሙከራ ቦና የሱራፌል ዐወልን ጥሩ የዓየር ላይ ኳስ ያለጫና በግንባር የመግጨት አጋጣሚ ተፈጥሮለት ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። ድሬዳዋዎች ነገሮች ለመልሶ ማጥቃት ተመቻችተውላቸው ሲታይ በተለይም 63ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ከበደ ከሄኖክ አየለ ባገኘው ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር ቢገናኝም ሙከራውን አላዛር ጨርፎ አክሽፎበታል።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች የኳስ ቁጥጥራቸውን መልሰው ማግኘት የቻሉት ጅማዎች ዱላ ሙላቱን እና ዳዊት ፍቃዱን ቀይረው በማስገባት ይበልጥ ጫና ሲፈጥሩ እንደድሬ ሁሉ በቅያሪዎቻቸው ጥረት ግብ አግኝተዋል። ዱላ ከመሀል ያስጀመረውን ጥቃት መሀመድኑር ያመቻቸለት ዳዊት ፍቃዱ ተነጥሎ በመውጣት ግብ ጠባቂውን ጭምር በማለፍ ጅማን 70ኛው ደቂቃ ላይ አቻ ያደረገች ግብ አስቆጥሯል።

በሁለቱም ሳጥኖች ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔዎች መዛነፍ እንጂ የቀሩት ደቂቃዎች ጨዋታው ይበልጥ ክፍት ሆኖባቸዋል። ጅማ በግራ በዱላ እና መሀመድኑር ጥምረት ድሬዎችም በተመሳሳይ በግራ በአቤል ከበደ መስመር ዕድሎችን ፈጥረዋል። በተለይም 83ኛው ደቂቃ ላይ አቤል እንደጎሉ ሁሉ ሌላ ጥሩ ኳስ ወደ ሳጥን ቢያደርስም መኸዲን ሙሳ ከግቡ አፋፍ ላይ በሚያስቆጭ መልኩ አምክኖታል። ሆኖም ሙኸዲን 88ኛው ደቂቃ ላይ ከእንየው የደረሰውን ኳስ እየገፋ በመግባት አመቻችቶ ቡድኑን ሲክስ ሄኖክ አየለ አጋጣሚውን ጎል አድርጎታል።

በመጨረሻ ደቂቃዎችም ጅማዎች አቻ ለመሆን ከሚያደርጉት ጥረት ይልቅ የድሬዳዋ መልሶ ማጥቃቶች ይበልጥ አይለው ጨዋታው በብርቱካናማዎቹ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማ ነጥቡን 20 በማድረስ የወራጅ ቀጠና ቦታውን ለአዲስ አበባ ከተማ ሲያስረክብ ጅማ አባ ጅፋር 15ኛ ደረጃ ላይ ረግቷል።

ያጋሩ