የወራጅ ቀጠናው ፍልሚያ በድሬዳዋ አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ ሱፐር ስፖርት ከአሠልጣኞች አስተያየት ተቀብሏል።
ሳምሶን አየለ – ድሬዳዋ ከተማ
ባቀዳችሁት መንገድ ጨዋታው ሄዷል?
ባስቀመጥነው ዕቅድ ነው የሄድነው። ኳሱን ለእነሱ በመተው ጎል እንዳይገባብን በጠንካራ እንቅስቃሴ በመከላከሉ ረገድ በመጀመሪያው አጋማሽ ተጫውተናል። ተከላካዮቹም በአግባቡ ስራቸውን ሰርተዋል። በሁለተኛው አጋማሽ ግን የነበራቸውን ብልጫ ከነበረን 4-4-2 ወደ 3-5-2 በመምጣት ብልጫውን ወስደንባቸው ብዙ ወደ ጎል በመጠጋት ሁለት ጎሎች በማስቆጠር በምንፈልገው ልክ እና በጣም የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ፈጥረን የምንፈልገውን ሦስት ነጥን አግኝተናል። ከእቅዳችን አንፃር የምንፈልገውን አግኝተናል።
የተጫዋች ለውጦቹ ስላመጣው ተፅዕኖ…?
የመጀመሪያው ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ላይ የጅማዎች እንቅስቃሴ ቀድመው ግብ ያገቡና እሱን የማስጠበቅ ነገር ነበር። ይህ እንዳይሆን መጀመሪያ ያሰብነው እነሱን መመከት ነው። ሁለተኛ ተለዋጭ እቅዳችን መሐል ሜዳውን ተቆጣጥረን ብዙ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ማቅረብ እና እነሱን መጠቀም ነው። ከዚህ አንፃር ተሳክቶልናል።
የድሉ አንድምታ..?
ምንም ጥርጥር የለውም። ጅማ እና እኛ የነበርንበት ቀጠና አደገኛ ነው። የዛሬ 3 ነጥብ ለእኛ እንደ 6 ነው። ከዚህ አንፃር ለቀጣይም ትልቅ ጉልበት የሚሆን ነው። ተጫዋቾቹንም ወደ አሸናፊነት ሪትም የሚመልስ ነው። በቡድናችን ላይም የሚፈጥረውን መነሳሳት በቀላሉ የምንገልፀው አይደለም። ይህንን በጥንካሬ እናስቀጥላለን።
አሸናፊ በቀለ – ጅማ አባ ጅፋር
ተጋጣሚያቸው ስላደረገው እንቅስቃሴ?
በድሬዳዋ በኩል በቡድን ፉክክር የተሻለ ነገር አላየሁም። የእኛ ቡድን ነበር ለዋንጫ የሚጫወት የሚመስለው። በቅንጅት ስራ እና በብዙ ነገር ከእነርሱ እንሻላለን ብዬ አስባለው።
ቡድኑ ስላመከናቸው የግብ ማግባት ዕድሎች?
ትክክል። ልምድ ያለው አጥቂ አለመኖሩ ዋጋ አስከፍሎኛል። ስለዚህ ተጫዋቾቹ ላይ ዳግም መስራት ይፈልጋል። በሳል የሆነ አጥቂ በዛ ቦታ ቢኖር ወሳኝነት ይኖረው ነበር። ለምሳሌ ሳላዲን ሰዒድ ከእኛ ጋር የነበረው ውይይት ቢጨርስ ኖሮ ይሄ ሁሉ ችግር አይኖርም ነበር። ይሄ እንደ ምክንያት የሚቀርብ ባይሆንም ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ማካተቱ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው። አሁን ያሉን ተጫዋቾች ከታችኞቹ ሊጎች የመጡ ናቸው። በእነርሱ አቅም አኳያ ያሳዩት ነገር ተስፋ ሰጪ ነው። እንደ ቡድን ይሄንን አጠናክረን ለመሄድ እና የአጨራረስ ስራዎችን ለማስተካከል እንሞክራለን። እንደ ቡድን ግን ተጫዋቾቹ ያደረጉት ተሃድሎ እና እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ እና ጥሩ ነበር።
ዳዊት ፍቃዱ ተቀይሮ ገብቶ ግብ ማስቆጠሩ በቀጣይ ጨዋታዎች ቋሚ እንዲሆን ያረገዋል..?
ልምምዶች ይወስናሉ። በምንፈልገው መልኩ ጥሩ ረድቶኛል። 90 ደቂቃ ይጨርሳል አይጨርስም ሌላ ጉዳይ ሆኖ ግን ያለውን ነገር ስለሰጠ አመሰግነዋለው።
ቡድኑ ካለበት ደረጃ አንፃር ስላለው ተስፋ..?
እያንዳንዱ ጨዋታ የፍፃሜ ጨዋታ ነው። እነዛን ጨዋታዎች በትክክል ነጥብ ይዞ ለመውጣት መታገል ይፈልጋል። አስር አስራ አንድ ጨዋታዎች አሉን እነሱን ተስፋ ባለመቁረጥ ጠንክሮ መቅረብ ይፈልጋል።