ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ሁለተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል

በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ የማጥቃት ጨዋታን ያሳዩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ለሁለተኛ ተከታታይ ጨዋታ ግብ ባስቆጠረው ሮቤል ተክለሚካኤል ብቸኛ ግብ ወላይታ ድቻን ረተዋል።

ኢትዮጵያ ቡናዎች ሰበታ ከተማን ከረታው የመጀመሪያ 11 ስብስብ ውስጥ ሁለት ለውጦችን በማድረግ አቡበከር ናስር እና ገዛኸኝ ደሳለኝን አስወጥተው በምትካቸው እንዳለ ደባልቄ እና ቴዎድሮስ በቀለን ያስገቡ ሲሆን በአንፃሩ ወላይታ ድቻዎች ደግሞ ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራው ስብስብ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል።

በርካታ ቁጥር ባላቸው የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች ታጅቦ መካሄድ የጀመረው ጨዋታ አጠቃላይ የመጀመሪያው አጋማሽ መልኩ ኳስን ተቆጣጥሮ መጫወት የሚፈልግ ነገርግን ቅብብሎችን ወደ ላይኛው የሜዳ ክፍል ለማሳደግ በተቸገረው ኢትዮጵያ ቡና እና ኳሱን ለተጋጣሚ ፈቅዶ ተጋጣሚን መሀል ሜዳ ላይ ጫና ውስጥ በመክተት ኳሶችን በመንጠቅ መልሶ ማጥቃት የመሰንዘር ፍላጎት በነበረው ወላይታ ድቻ መካከል የተካሄደ ጨዋታ ነበር።

በዚህ ሂደት ኢትዮጵያ ቡና ከ10ኛው እስከ 15ኛው ደቂቃ ባለው የጨዋታ ደቂቃ በተጋጣሚው ወላይታ ድቻ ላይ 91% የኳስ ቁጥጥር ድርሻን እስከ መውሰድ ደርሰው የነበረ ቢሆንም በጨዋታው ግን ኳሶች በማቋረጥ እድሎችን የመፍጠር ፍላጎት የነበራቸው ወላይታ ድቻዎች አጋጣሚዎችን ወደ ጠሩ የግብ እድሎች መቀየር ባይችሉም ወደፊት ሲሄዱ የተሻለ አስፈሪ ነበሩ።

እምብዛም የጠሩ የግብ እድሎችን ባልተመለከትንበት አጋማሽ የአጋማሹ አደገኛ የግብ ሙከራን የተመለከትነው በ41ኛው ደቂቃ ነበር ፤ አስራት ቱንጆ ወደ ግራ ካደላ አቋቋም ወደ ግብ የላከውን የቆመ ኳስ አጋጣሚ ፅዮን መርዕድ አድኖበታል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ወላይታ ድቻዎች በተወሰነ መልኩ ወደ ኃላ መሸሻቸውን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡናዎች በተሻለ መልኩ በተጋጣሚ የሜዳ አጋማሽ በመገኘት ጥቃት ለመሰንዘር ሙከራ ሲያደርጉ ተመልክተናል ፤ በተለይም ዊልያም ሰለሞን በተሰለፈበት የቡድኑ የግራ ወገን ተደጋጋሚ እድሎችን ለመፍጠር ሙከራ አድርገዋል።

በ52ኛው ደቂቃ ዊልያም ሰለሞን ከመስመር ሰብሮ ወደ ውስጥ ከገባ በኃላ ያደረጋት ሙከራ እንዲሁም በ54ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ዊልያም ሰለሞን ከግራ መስመር ተነስቶ በቁጥር በርካት ያሉ የወላይታ ድቻ ተጫዋቸችን አልፎ ያቀበለውን ኳስ እንዳለ ደባልቄ ወደ ግብ የላካት እና ፂሆን መርዕድ ያዳነበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።

በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አንፃር ደከም ያለ እንቅስቃሴን ያደረጉት ወላይታ ድቻዎች የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች በመጠቀም ረገድ ፍፁም ደካማ የነበሩ ሲሆን በአንፃሩ ከቆሙ ኳሶች የተሻለ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሙከራ አድርገዋል። በ61ኛው ደቂቃም በጉዳት ምክንያት በመጀመሪያ ተሰላፊነት ለመጀመር ያልቻለውን አቡበከር ናስር በእንዳለ ደባልቄ ምትክ በማስገባት ይበልጥ ማጥቃታቸውን ለማሻሻል ጥረት ያደረጉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ጥሬያቸው በፍጥነት ፍሬ ለማፍራት ተቃርቦ ነበር።

አቡበከር ናስር ተቀይሮ በገባ በደቂቃዎች ልዮነት ከሮቤል ተክለሚካኤል የደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ ሁት የድቻ ተጫዋቾችን አልፎ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቶበታል። በ74ኛው ደቂቃ በአንፃሩ ወላይታ ድቻዎች በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ሳይጠበቁ በፈጠሩት አጋጣሚ አበባየሁ አጪሶ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ያሬድ ዳዊት ከሳጥኑ ጠርዝ ወደ ግብ የሞከራትን ኳስ በረከት አማረ አድኖበታል።

በ78ኛው ደቂቃ ታድያ ኢትዮጵያ ቡናዎች በሁለተኛው አጋማሽ ለነበራቸው የበላይነት ማረጋገጫ የምትሆን ግብን በስተመጨረሻም አግኝተዋል። ወላይታ ድቻዎች ከግብ ክልላቸው በቅብብሎሽ ለመውጣት ባደረጉት ጥረት በሰሩት የቅብብል ስህተት የተገኘውን አጋጣሚ ኢትዮጵያ ቡናዎች በፈጣን ቅብብል አደገኛ ቦታ ላይ ያደረሱትን ኳስ ሮቤል ተክለሚካኤል ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።

በቀሩት የመጨረሻ ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡናዎች ከግቧ በደቂቃዎች ልዮነት በአቡበከር ናስር አማካኝነት ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ቀርበው የነበረ ቢሆንም ኳሷን ፅዮን መርዕድ አድኖበታል። በአንፃሩ ወላይታ ድቻዎች ደግሞ በሙሉ አቅማቸው ለማጥቃት ጥረት ቢያደርጉም የጠሩ እድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ሁለተኛ ተከታታይ ድላቸውን ያስመዘገቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ነጥባቸውን ወደ 27 በማሳደግ ወደ 6ኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ በአንፃሩ በተከታታይ ጨዋታዎች ውጤት ማስመዝገብ የተቸገረው ወላይታ ድቻ ደግሞ በ33 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።