የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 1-0 ወላይታ ድቻ

የምሽቱ ጨዋታ በቡና አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞች ሀሳባቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለጨዋታው

“ጨዋታው ጥሩ ነበር። ያው እነሱ አብዛኛው ቁጥራቸውን ከኳስ ኋላ አድርገው በመከላከል በሚገኙ ክፍተቶች በሚነጠቁ ኳሶችየግብ ዕድል ለመፍጠር ነበር ያሰቡት። ስለዚህ እኛ የኳስ ባለቤትነታችንን አስጠብቀን ሰው ሜዳ ለመግባት ስናስብ ያንንም ታሳቢ እያደረግን ነው። አንድ ሁለት ከዕረፍት በፊት የተነጠቁ ኳሶች አሉ። እነዛን ማስወገድ አለብን ፤ እየተቆጣጠርን እነሱ ሜዳ በመጫወት ከዛ በእነሱ ሜዳ ደግሞ እንዴት ነው ክፍተት ማግኘት የሚቻለው ? ምክንያቱም ብዙ የቁጥር ክምችት ስላለ የእኛም የእነሱም ተጫዋቾች ፤ በቀላሉ ክፍትት ማግኘት አይቻልም። ያንን እንዴት ነው ማግኘት የምንችለው የሚለውን በዕረፍት ሰዓት ለማድረግ ሞክረናል።

የአቡበከር ቅያሪ ልዩነት ስለመፍጠሩ

“አቡበከር ሲገባ ብዙ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ራሳቸው ሜዳ ላይ ስላሉ ክፍተት እና ነፃነት እንደማያገኝ ግልፅ ነው ፤ ከሚጫወቱበት መንገድ አንፃር። ጠቀሜታው ተጋጣሚ እሱ ላይ የሚያደርገው ትኩረት አለ ፤ በሁለት ሦስት ተጫዋቾች። በዛ ሂደት ውስጥ ሌሎች የእኛ ተጫዋቾች ነፃነት ያገኛሉ። ከዛ አንፃር ጠቀሜታ ነበረው።

ስለውጤቱ ጠቃሚነት

“ከሥነ ልቦና አንፃር ትልቅ ጠቀሜታ አለው። ተሸንፈህ ስትመጣ እና አሸንፈህ ስትመጣ ልዩነት አለው። የምታሳልፋቸው የልምምድ ጊዜያቶች ላይም የሚያመጣው ልየነት አለ። ግን እኛ ሁሌም ትኩረት ማደረግ አለብን ብዬ የማምነው ተሸነፍንም አሸነፍንም ምንድነው ማሳደግ ፣ ማረም ያለብን ? የሚለው ላይ ነው። ማድረግ ያልቻልናቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? የሚለው ሁል ጊዜ ከዋናው ችግር እንዳንወጣ ያደርገናል። አንዳንድ ጊዜ ሽንፈቶች ሲመጡ ከዋናው ነገር ትወጣለህ። የእኛ ዋናው እና መሰረታዊው ነገር ሜዳው ላይ የምንሰራው ነገር ነው። ስለዚህ በቀጣዩ ጨዋታ ከዚህ ጨዋታ ተነስተን ምንድነው የምናሻሽለው የሚለውን እናያለን። ምክንያቱም ተጋጣሚም እኛን ያየናል ፤ እዛ ላይ ነው ትኩረት የምናደርገው።”

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም – ወላይታ ድቻ

ስለጨዋታው

“ጨዋታው ጥሩ ነው። ኢትዮጵያ ቡና አስከፍቶ ለመግባት በትዕግስት የሚጫወት ቡድን ነው። ስለዚህ ከግብ ጠባቂያችን ጋር አንድ ለአንድ እንዳይገናኙ ቦታ ከልክለናቸው ነበር በመጀመሪያው አጋማሽ። በሁለተኛው አጋማሽ ተጭነን ለመጫወት ነበር ያሰብነው። መሸናነፍ አልነበረብንም። ምክንያቱም ሁለታችንም ብዙ እያጠቃን አልነበረም። ጎሉም ከእኛ ተከላካይ ስህተት የተገኘ ነበር ማለት ይቻላል። እንዲህ ዓይነት ስህተቶች ዋጋ ያስከፍላሉ። በዛ ምክንያት ነው ነጥብ የጣልነው ማለት እችላለሁ።

ስንታየሁ መንግሥቱን ስለማጣታቸው

“እሱም እንድሪስም በጣም ወሳኝ ናቸው። እነ አበባየሁ ፣ ቢኒያም (ቀይረን የምናስገባው) ወጣት ተጫዋቾች ናቸው። ስብስባችን ይኸው ነው። ግን ባለን ስብስብም ቢሆን ሰርተን መምጣት አለብን ብዬ ነው የማስበው እና አንዴ የሆነ ነገር ነው ስንታየሁን በቀላሉ መልሰን አናገኘውም ፤ ቢኖር ደስ ይለን ነበር። ካልሆነ ግን ያለንን ዕቅድ ይዘን እንቀጥላለን።

ስለቀጣይ ጨዋታዎች ጥንካሬ

“ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ቡድኖች ሁለተኛው ዙር ቀላል የምትለው ቡድን የለም ፤ ጠንከር ብለው እንደሚመጡብን እናውቃለን። ስለዚህ ባለን የሰው ኃይል ራሳችንን አጠናክረን ለመምጣት እንሞክራለን። ቻምፒዮኑም ወራጁም ስላልለየ ጠንክረን መስራት ይኖርብናል።”