ነገ በቅድሚያ የሚደረገውን ጨዋታ የተመለከቱ ጉዳዮችን እንደሚከተለው አንስተናል።
በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ አካባቢ በነጥብ ተቀራርበው የሚገናኙት አዳማ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ቀላል የማይባል ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። 12 የአቻ ውጤቶችን ያስመዘገበው አዳማ ከተማ ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል መመለስ አንድ ደረጃ አሻሽሎ ወደ 6ኛነት ከፍ የማለት ዕድልን ይሰጠዋል። ከአዳማ በሁለት ነጥብ ዝቅ ብለው በ22 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ያሉት ነብሮቹም እንዲሁ እስከ 7ኛነት ማደግ ይችላሉ።
ሁለቱ ቡድኖች ባሰለፍነው ሳምንት ባደረጓቸው ጨዋታዎች ነጥብ ሲጥሉ ለኳስ ምስረታ ሂደታቸው ከተጋጣሚዎቻቸው የተሰጣቸው የተለያየ ምላሽ ፈትኗቸው አልፏል። በማያስከፋ ሁኔታ ከሜዳቸው በቅብብል ለመውጣት የማይቸገሩ የነበሩት አዳማ ከተማዎች የወላይታ ድቻን የአማካይ እና የኋላ መስመር አደረጃጀር ሰብረው ለመግባት ተቸግረው ታይተዋል።
በሌላ በኩል በአርባምንጭ ከተማ ከጅምሩ የኋላ መስመር ተሰላፊዎቻቸው ከፍ ያለ ጫና ሲደርስባቸው የነበሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በሚፈልጉት መጠን ከኳስ ምስረታ ሂደታቸው መነሻነት ተጋጣሚ ሳጥን መድረስ አልሆነላቸውም። ከዚህ አንፃር ሁለቱ ቡድኖች ተመሳሳይ ፈተና ከተጋጣሚዊቻቸው በማይጠብቁበት ጨዋታ በተለይም የተሻለ የመንቀሳቀሻ ቦታን እንደሚያገኙ ሲጠበቅ ማን ይህንን በአማካይ ክፍል ብልጫ እና በተሻለ የማጥቃት ስትራቴጂው ብልጫ አሳይቶ የግብ ዕድሎችን ይፈጥራል የሚለው ነጥብ ከጨዋታው ይጠበቃል።
አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ እስካሁን በመቀመጫ ከተማው ላይ ድልን ማሳካት ያልቻለው ቡድናቸውን የአጨራረስ ችግር ድል ለማድረግ ካለ ጉጉት የሚመነጭ እንደሆነ ተናግረው ነበር። ቡድኑ ከፊት ከሚጠቀምባቸው ተጫዋቾች አንፃራዊ ጥራት አንፃር ጥያቄ የማይነሳበት መሆኑ የአሰልጣኙን ምክንያት አሳማኝ ያደርገዋል። በመሆኑም ከግብ ፊት በሚወሰኑ ውሳኔዎች ላይ አዳማ ከተማ ነገ ይበልጥ ተሻሽሎ መቅረብ የሚገባው መሆኑ ዕሙን ነው።
ከዚህ ባለፈ ግን ከአጥቂ መስመር ተሰላፊዎች ውጪ ሌሎች የግብ ምንጮችን መፈለግ እንዲሁም በዋናነት ከአማካይ ክፍሉ እና ከመስመር ተጫዋቾቹ የሚገኙ የግብ አጋጣሚዎችን በማበረካት ለአጥቂዎች በርካታ አጋጣሚዎችን መፍጠር (የጉጉት ችግሩን ለማቃለል) የቡድኑን ስልነት ሊያሻሽል ይችላል። በተለይም በሦስት ተከላካዮች የሚጠቀመው ተጋጣሚያቸውን ግራ እና ቀኝ ጎን በመስመር አጥቂዎቻቸው ኢላማ ማድረግ ለአዳማዎች አዋጭ ሊሆንላቸው ይችላል።
በዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ አራት ግቦች ያስተናገደው ሀዲያ ሆሳዕና ድራማዊ በነበረው ጨዋታ ነጥብ ተጋርቶ መውጣቱ እጅግ አስደናቂ ነበር። ቡድኑ ለነገው ጨዋታ ካሳለፍነው ሳምንት ፍልሚያው የአልሞት ባይ ተጋዳይነቱን አዎንታዊ ብቃት ይዞ መምጣት ይኖርበታል። ከዚህ ውጪ የማጥቃት እና የመከላከል ሚዛኑን የሚስትባቸው አጋጣሚዎች ሆሳዕናን ዋጋ አስከፍሎት መመልከታችን በተለይ የኋላ መስመሩ የአንድ ለአንድ ግንኙነቶች የአዳማን አጥቂዎች ፍጥነት በሚመጥን መልኩ ተሻሽሎ እንዲቀርብ ይጠበቃል።
አሰልጣኝ መሉጌታ ምህረት የግርማ በቀለን መምጣት ተከትሎ ባደረጓቸው ሽግሽጎች ውስጥ የቡድኑ ማጥቃት በቀኝ በብርሀኑ በቀለ በኩል አጋድሎ መመልከታችን ሌላው የነብሮቹ ትኩረት መሆን ይገባዋል። ብርሀኑ ነገ በሚሊዮን ሰለሞን ከሚመራው ጠንካራ የአዳማ የግራ ወገን ብርቱ ፍልሚያ እንደሚጠብቀው ስናስብ ቡድኑ ከግራው እና መሀል ለመሀል ከሚሰነዝራቸው ጥቃቶችም ንፁህ የግብ ዕድሎችን መፍጠር እንዳለበት እንረዳለን።
የሀዲያ ሆሳዕናው ግብ ጠባቂ ሶሆሆ ሜንሳህ አሁንም ከጉዳቱ ያላገመመ በመሆኑ ከነገው ጨዋታ ውጪ ሲሆን በአንፃሩ ጉዳት ላይ የሰነበተው ሳምሶን ጥላሁን ለጨዋታው ዝግጁ መሆኑ ታውቋል። በአዳማ ከተማ በኩል ብቸኛው ጨዋታው የሚያልፈው ተጫዋች ጉዳት ላይ የምሚገኘው አቡበከር ወንድሙ ብቻ ይሆናል።
ጨዋታው በተካልኝ ለማ የመሀል ዳኝነት ሲከናወን ታምሩ አደም እና ተስፋዬ ንጉሴ በረዳትነት አዳነ ወርቁ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበውበታል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን አምስት የሊግ ግንኙነት ታሪክ ሲኖራቸው አዳማ ከተማ ሁለቴ ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ አንዴ ድል ቀንቷቸው ፤ በዘንድሮው መጨረሻ ጨዋታቸው ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ አስር ግቦች ሲመዘገቡ ሀዲያ የአራቱ አዳማ የስድስቱ ባለቤት ሆነዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
አዳማ ከተማ (4-3-3)
ጀማል ጣሰው
ጀሚል ያዕቆብ – ቶማስ ስምረቱ – አዲስ ተስፋዬ – ሚሊዮን ሰለሞን
አማኑኤል ጎበና – ዮሴፍ ዮሐንስ – ዮናስ ገረመው
አሜ መሀመድ – ዳዋ ሆቴሳ – ወሰኑ ዓሊ
ሀዲያ ሆሳዕና (3-5-2)
ያሬድ በቀለ
ፍሬዘር ካሳ – ቃለአብ ውብሸት – ግርማ በቀለ
ብርሃኑ በቀለ – ሳምሶን ጥላሁን – ተስፋዬ አለባቸው – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን – ሄኖክ አርፌጮ
ሐብታሙ ታደሠ – ባዬ ገዛኸኝ