የ19ኛ ሳምንት የሦስተኛ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹ ሀሳቦች ተነስተዋል።
ዋና አሠልጣኙ ሥዩም ከበደን አሰናብቶ በምክትል አሠልጣኙ ኃይሉ ነጋሽ እየተመራ ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል የተመለሰው የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ከመሪዎቹ ያለውን ልዩነት እያጠበበ ለመሄድ እና ከ17 ጨዋታዎች በኋላ ተከታታይ ድል ለማግኘት እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማም ከአራት ጨዋታዎች በኋላ መከላከያ ላይ ያገኘውን ድል በመድገም ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት የሚያደርገውን ጉዞ ለማጠናከር ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ምክትል አሠልጣኛቸው ኃይሉ ነጋሽን በመንበሩ ሾመው ባሳለፍነው ሳምንት በወራጅ ቀጠናው ቅርቃር እየዳከረ የሚገኘውን ጅማ አባ ጅፋር የገጠሙት ፋሲሎች ተቸግረውም ቢሆን ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ይዘው ወጥተዋል። በጨዋታው ቀድሞ ግብ ተቆጥሮበት የነበረው ቡድኑ በኳስ ቁጥጥሩም ተመጣጣኝ ድርሻ ከጅማ ጋር ቢኖረውም በስብስቡ ጨዋታን በግላቸው የሚወስኑ ተጫዋቾች ስላሉት ተፈላጊዋን ድል አሳክቷል።
በእንቅስቃሴ ደረጃ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ መቻኮሎች የበዙበት ነገሮች በርከት ብለው ታይተው የጨዋታው የሀይል ሚዛን ወደ ጅማ አጋድሎ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ከወገብ በላይ የሚገኙ ተጫዋቾችን በመለወጥ በአንፃራዊነት በተሻለ ወደ ግብ እየደረሰ ግቦችን ለማግኘት የጣረበት መንገድ በ53 እና 91ኛው ደቂቃ ዋጋ አስገኝቶታል። ቡድኑ ላይ ከነበረው የማሸነፍ ጫና አንፃር ድሉ በየትኛውም መንገድ ቢመጣም በከፍተኛ ሁኔታ መጠበቅ ያለበት ስብስቡ ጉዞውን ለማሳመር ሌላ በንፅፅር ቀለል ያለ ቡድን ነገ ማግኘቱ መልካም ይመስላል። ይህ ቢሆንም ግን ከአዲስ አበባ ቀላል የሚባል ፈተና አይጠብቀውም።
ሀዋሳ ላይ በተደረገው የመጀመሪያ ዙር ውድድር በአዲስ አበባ ከተማ ተረቶ የነበረው ፋሲል በእግር ኳሳዊ በቀል ነገ ጠንክሮ እንደሚጫወት ይታሰባል። ምናልባት እንደ ጅማው ጨዋታ የኳስ ቁጥጥር ለማግኘት አዲስ አበባ ከተማም እንደሚግደረደረው ቢገመትም ከተከላካይ እስከ አጥቂ ከግብ ጠባቂ ውጪ በሁሉም የሜዳ ክፍል ከሚጫወቱ 11 ተጫዋቾች ግብ አስቆጣሪ ያሉት ቡድኑም ለአዲስ አበባ ተከላካዮች ከባድ የቤት ሥራ እንደሚሰጥ ይጠበቃል። ከመስመር ከነሽመክት እና በረከት ከመሐል ደግሞ ከሱራፌል እንዲሁም በረጅሙ ከመሐል ተከላካዮች የሚላኩ ኳሶችን ከየአቅጣጫው በማስነሳት የግብ ምንጭ ለማድረግ እንደሚታትሩ ቀድሞ መናገር ይቻላል። ይህ የማይገመት የማጥቃት አጨዋወት ደግሞ ከወራጅ ቀጠናው ክለቦች ውጪ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር በጣምራ ሁለተኛ ብዙ ግብ ያስተናገደ ክለብ ለሆነው አዲስ አበባ ፈተና ነው።
በአሠልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ እየተመራ የሚገኘው የመዲናይቱ ክለብ አዲስ አበባ ከተማ ባሳለፍነው ሳምንት አብሮት ያደገውን መከላከያ አሸንፎ መምጣቱ ትልቅ የሥነ-ልቦና ስንቅ የሚሰጠው ይመስላል። ብዙዎች ባልገመቱት ሁኔታም ከአሰላለፍ ጀምሮ እስከ አጨዋወት መንገድ ድረስ የተደረጉት ለውጦችም ቡድኑን ዋጋ አስገኝተውለታል። በጨዋታውም ቡድኑ በርከት ያሉ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ቢያሰልፍም ለመከላከያ ኳሱን በመልቀቅ ተጋጣሚው ብዙም በማይታወቅበት የኳስ ቁጥጥር ጊዜውን እንዲያሳልፍ አድርገውት ወተዋል። ቡድኑ በድምሩ 10 የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን (5 ዒላማውን የጠበቀ 5 ያልጠበቀ) ሲፈጥር መከላከያ ግን ከ7 አጠቃላይ ሙከራዎች አንዱንም ዒላማውን ሳያስጠብቅ ቀርቷል። ይህ የሚያሳየው አዲስ አበባ በሁለቱ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች ጠንካራ እንደነበሩ ነው። ነገ ግን እንደ መከላከያ አይነት ቀለል ያለ ተጋጣሚ ነገ ስለማይጠብቀው ከኳስ ጋርም ከኳስ ውጪም የሚያሳልፈውን ጊዜ ወደ ፍፁምነት በተጠጋ ሁኔታ መከወን ይገባዋል።
በአዲስ አበባ የአጥቂ መስመር እምብዛም መረዳዳት ባይታይም ብዙ ጊዜ ወደ ሜዳ ከሚገቡት ፍፁም፣ ሪችሞንድ እና እንዳለ የበለጠ ሪችሞንድ አዶንጎ ለተጋጣሚ ተከላካዮች የራስ ምታት ሲሆን ይስተዋላል። በመከላከያውም ጨዋታ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ወደ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ፉክክር ጎራ ብሏል። በወራጅ ቀጠና አካባቢ ከሚገኝ ቡድን በሊጉ የተጫዋቾች ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ፉክክር ላይ መኖሩ የሚገርም ቢሆንም ፍፁምም ሌላኛው የፋሲል ተከላካዮች ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ ተጫዋች ነው። የቡድኑን 65% ግብ ያስቆጠሩት ሁለቱ ተጫዋቾች ብቃት እንዲጎላ ከሚያደርጉ ተጫዋቾች መካከል ግንባር ቀደሙ አማካዩ ቻርለስ ሪባኑ ነው። የተከላካይ አማካዩ በዋናነት ከእግሩ የሚነሱት ረጃጅም ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶችን ፋሲሎች በትኩረት መከታተል ግድ ይላቸዋል። ከመከላከያው ጨዋታ በፊት በተከታታይ አስራ አንድ ጨዋታዎች እንዲሁም ከአጠቃላይ 18 ጨዋታዎች በሁለቱ ብቻ ግቡን ሳያስደፍር የወጣው ቡድኑ የሚቆጠሩበትን ግቦች ካልቀነሰ በአስጊው ቀጠና መዝለቁ የማይቀር ነው። ነገም በሊጉ ሁለተኛ ብዙ ግብ ያስቆጠረውን ክለብ በመግጠሙ የኋላ መስመሩን በሚገባ ማደራጀት ይገባዋል።
ፋሲል ከነማ በነገው ጨዋታ የአጥቂው ሙጂብ ቃሲምን ግልጋሎት በጉዳት ምክንያት ማግኘቱ እርግጥ አይደለም። በአዲስ አበባ በኩል ግን ምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና አለመኖሩ ተመላክቷል። ቡድኑን ዳግም ባሳለፍነው ቅዳሜ የተቀላቀለው ኤሊያስ ማሞም በጨዋታ ስብስብ ስሙ ሊካተት እንደሚችል ሰምተናል።
ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተስማ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ሲመራው ተመስገን ሳሙኤል
እና ሙስጠፋ መኪ ረዳት ዳኞች ቢኒያም ወርቅአገኘሁ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ናቸው።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም ሦስት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን አዲስ አበባ ከተማ ሁለት ፋሲል ከነማ ደግሞ አንድ ጊዜ አሸንፈዋል። እንደ ግንኙነታቸውም ሦስት ሦስት ጊዜ እርስ በእርስ ግብ አስቆጥረዋል።
ግምታዊ አሠላለፍ
ፋሲል ከነማ (4-1-4-1)
ሚኬል ሳማኪ
ዓለምብርሃን ይግዛው – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን
ይሁን እንዳሻው
ሽመክት ጉግሳ – በዛብህ መለዮ – ሱራፌል ዳኛቸው – በረከት ደስታ
ኦኪኪ አፎላቢ
አዲስ አበባ ከተማ (4-3-3)
ዳንኤል ተሾመ
አሰጋኸኝ ጴጥሮስ – ቴዎድሮስ ሀሙ – ኢዮብ በቀታ – ሮቤል ግርማ
ሙሉቀን አዲሱ – ቻርለስ ሩባኑ – ኤሊያስ አህመድ
እንዳለ ከበደ – ሪችሞንድ ኦዶንጎ – ፍፁም ጥላሁን