ሪፖርት | ሀዲያ ሆሳዕና አዳማ ከተማን ረቷል

ሀዲያ ሆሳዕና በዑመድ ኡኩሪ እና ራምኬል ሎክ ግቦች በመቀመጫ ከተማው የሚጫወተውን አዳማ ከተማን በማሸነፍ በደረጃ ሰንጠረዡ ሽቅብ ወጥቷል።

ባሳለፍነው ሳምንት ከወላይታ ድቻ ጋር አቻ ተለያይተው ለዛሬው ጨዋታ የተዘጋጁት አዳማ ከተማዎች ከጨዋታው ሦስት ተጫዋቾችን እንዲሁም የአደራደር ቅርፅ ለውጥ አድርገው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በ3-5-2 ቅርፅ ዮሴፍ ዮሐንስ፣ ታደለ መንገሻ እና አሜ መሐመድን አሳርፈው ደስታ ዮሐንስ፣ ዘካሪያስ ከበደ እና አዲሱ ተጫዋቻቸው ፀጋአብ ዮሴፍን በአሰላለፋቸው አካተዋል። በአርባ ምንጭ ከተማ 4ለ1 እየተመሩ በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች ውስጥ አቻ ተለያይተው የመጡትን ሀዲያ ሆሳዕናዎች የሚመሩት አሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት በበኩላቸው ተከላካዩ ቃለአብ ውብሸትን ብቻ በአጥቂው ባዬ ገዛኸኝ ተክተው ጨዋታውን ቀርበዋል።

ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው ጨዋታ በ7ኛው ደቂቃ የመጀመሪያ ሙከራ አስተናግዷል። በዚህም በአንፃራዊነት ወደ ግብ ለመድረስ ፍላጎት ሲያሳይ የነበረው ሀዲያ ሆሳዕና በዑመድ ኡኩሪ አማካኝነት መሪ ሊሆን ነበር። ተጫዋቹም ከግራ መስመር ከእያሱ ታምሩ የተሻገረውን ኳስ በግራ እግሩ ተቆጣጥሮ በዛው ግራ እግር ቢሞክረውም የግብ ዘቡ ጀማል ጣሰው አምክኖበታል። ከአስር ደቂቃዎች በኋላም ይሁ አጥቂ በቀኝ የሳጥኑ ክፍል ተገኝቶ ሌላ ጥቃት ሰንዝሮ ነበር። አዳማዎች ደግሞ በ16ኛው ደቂቃ በራሳቸው በኩል የመጀመሪያ ሙከራቸውን ከመዓዘን ምት በተከላካዩ ሚሊዮን ሰለሞን አማካኝነት አድርገው ወጥቶባቸዋል።

በመቀመጫ ከተማቸው እየተጫወቱ የሚገኙት አዳማዎች ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ እጅግ ለግብ ቀርበው ዕድሉን ሳይጠቀሙበት ቀርቷል። በዚህም አብዲሳ ጀማል ከራሱ ሜዳ በረጅሙ የተላከውን ኳስ ከተከላላዮች አፈትልኮ በመውጣት ከግብ ዘቡ ያሬድ በቀለ ጋር አንድ ለአንድ ቢገናኝም ተጫዋቹ በአስቆጪ ሁኔታ አጋጣሚውን አምክኖታል። ተመሳሳይ የ3-5-2 የተጫዋች አደራደር ቅርፅ በመጠቀም ጨዋታውን እየከወኑ የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች መሐል ሜዳ ላይ ኳስ ቶሎ ቶሎ በመነጣጠቅ የተመጣጠነ የኳስ ድርሻ ይዘው ታይቷል።

ከውሃ እረፍት መልስ ግን ጨዋታው መሪ አግኝቷል። በዚህም በ28ኛው ደቂቃ የተገኘን የቅጣት ምት ሔኖክ አርፊጮ ሲያሻማው በሩቁ ቋሚ የነበረው ፍሬዘር ካሣ ታግሎ በግንባሩ የገጨውን ኳስ ተከላካዩ አዲስ ተስፋዬ እና ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው በተዘናጉበት ጊዜ መሐላቸው ፈጥኖ የተገኘው ዑመድ ግብ አስቆጥሮ ሀዲያን መሪ አድርጓል። በርካታ ጨዋታዎች ላይ ቀድመው ግብ የሚያስተናግዱት አዳማዎች ዛሬም በተመሳሳይ በጊዜ ግብ ካስተናገዱ በኋላ ምላሽ ለመስጠት ሲቸገሩ ነበር። ቡድኑም መሐል ለመሐል ከሚደረጉ ጥቃቶች ውጪ ሜዳውን በመለጠጥ የዕድሎች ማግኛ አማራጮችን ማስፋት ተስኗቸው አጋማሹን እየተመሩ አገባደዋል።

ሁለተኛውን አጋማሽ በጥሩ ተነሳሽነት የጀመሩት ሀዲያዎች በ47ኛው ደቂቃ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ የሚያደርጉበት አጋጣሚ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት አግኝተው ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃም የተገኘው አጋጣሚ በተከላካዮች ተጨርፎ የመዓዘን ምት ሊሆን ሲል ጀማል ለማዳን ሲጥር የተሳሳተውን ኳስ አበባየሁ ዮሐንስ ደርሶት በቀጥታ ወደ ግብ ቢመታውም የግብ ዘቡን ስራ በሚፈቀድላቸው የሰውነት አካል ለመሸፈን መስመሩ ላይ ከተገኙት ቶማስ እና ደስታ መካከል ቁመታሙ ተከላካይ ቶማስ በግንባሩ ኳሱን ከግብነት ታድጎታል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም በድጋሜ ሀዲያ ጨዋታውን ለመግደል በአበባየሁ አማካኝነት ሌላ አጋጣሚ ፈጥረው ሌላኛው ተከላካይ ሚሊዮን በግንባሩ መልሶባቸዋል።

የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን በመቀየር ቅርፃቸውን የቀየሩት አዳማዎች በ59ኛው ደቂቃ ወደ ጨዋታው የተመለሱበትን ግብ አስቆጥረዋል። በዚህም የቀኝ ተከላካዩ ጀሚል መሬት ለመሬት ያሻገረውን ኳስ ፍሬዘር በአግባቡ መቆጣጠር ተስኖት ሲመልሰው በቦታው የነበረው አሜ መሐመድ ቡድኑን አቻ አድርጓል። ከግቡ በኋላም አዳማ በዮሴፍ ዮሐንስ እና ጀሚል ያዕቆብ የሩቅ ኳሶች ወደ መሪነት ለመሸጋገር ጥሮ ነበር።

በዚህ አጋማሽ እንደ አጀማመራቸው መዝለቅ ያልቻሉት ሀዲያዎች ዘለግ ካሉ ደቂቃዎች በኋላ በ81ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ለሳጥኑ ጫፍ ሆኖ በሞከረው ኳስ ጀማልን ፈትነዋል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ ሦስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ የማሸነፊያውን ግብ አስቆጥረዋል። በዚህም በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ዑመድ ፍጥነቱን ተጠቅሞ የደረሰውን ኳስ ተቀይሮ ለገባው ራምኬል ሎክ ሲሰጠው ተጫዋቹም ከኤፍሬም ዘካሪያስ አንድ ሁለት ተቀባብሎ ጀማል ጀርባ የሚገኘው መረብ ላይ ቀላቅሎታል። ጨዋታውም በዚሁ ውጤት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ሀዲያ ሆሳዕና ነጥቡን ከ22 ወደ 25 በማሳደግ ወደ ስድስተኛ ደረጃ ሽቅብ ወቷል። ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ሽንፈት ያስተናገዱት አዳማዎች በበኩላቸው በ24 ነጥቦች አንድ ደረጃ ሸርተት ብለው የደረጃ ሰንጠረዡን ወገብ ይዘዋል።