የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 1-2 ሀዲያ ሆሳዕና

ሀዲያ ሆሳዕና በራምኬል ሎክ የመጨረሻ ደቂቃ ጎል ሦስት ነጥብ ካሳካ በኋላ አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – አዳማ ከተማ

ስለጨዋታው

“በንፅፅር ሁለተኛው አጋማሽ ይሻላል። በመጀመሪያው እኛ ያሳብነውን ነገር መተግበር አልቻልንም ፤ ሙሉ ለሙሉ ብልጫ ወስዶብን ነበር ተጋጣሚያችን። በሁለተኛው አጋማሽ ያንን ለማስተካከል እና ወደ ጨዋታው ለመመለስ ሞክረናል። እንደአጠቃላይ ሳየው የተሻለው ቡድን አሸንፏል ፤ እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። ግን ያው ዞሮ ዞሮ ከዚህ ችግራችን ለመውጣት መስራት እና መጫወት ያልቻልንበትን ነገር ማጥራት ይጠበቅብናል።

መሀል ሜዳ ላይ ስለተወሰደባቸው ብልጫ

“መሀል ሜዳ ላይ በመጀመሪያው አጋማሽ በልጠውናል። አንድ ቁጥር ወደ ፊት በመጨመር እነሱን ወደኋላ ለመጎተት ነው የሞከርነው። በዛ መንገድ ተሳክቶልናል። ጎልም ማግባት ችለናል ፤ ተጭነንም ለማጥቃት ሞክረናል። መጨረሻ ላይ ጎል ማግባት ስለፈለግን የአደረጃጀት የአቋቋም ችግር ነበረብን። በእሱ ተጠቅመው ሁለተኛ ጎል ማግባት ችለዋል።

በሜዳቸው እስካሁን ስላለማሸነፋቸው

“እንደአሰልጣኝ አዝናለሁ። ደጋፊዎቻችንንን በሜዳችን ማስደሰት የሜዳ ተጠቃሚነታችንን ባለማረጋገጣችን እንደ አሰልጣኝ ደስ አይለኝም። ዞሮ ዞሮ ተጫዋቾቹን ከዚህ ችግር ለማውጣት የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን።”

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ሀዲያ ሆሳዕና

ስለጨዋታው

“ጨዋታው ቆንጆ ነው። በመሸናነፍ ውስጥ እንጂ እንቅስቃሴው ብዙም ማራኪ ባይሆንም ማሸነፋችን በጣም ጥሩ ነው። ከነበርንበት ከፍ ለማለት ሦስት ነጥብ ግዴታ ስለሚያስፈልገን እነሱም ያስፈልጋቸው ስለነበር ጨዋታው ከባድ ነበር። ግን እኛ የምንፈልገውን አሳክተናል።

ስለአማካይ ክፍሉ

“መሀሉን ማሸነፍ ከቻልክ ጨዋታውን መቆጣጠር ትችላለህ። ግን የቡድናችንን አሰራር ነው የሚወስነው። እያሸነፍን የመጣንበት ቡድን በ3-5-2 ስለነበር ዛሬም ከፊት ሁለት አጥቂ አድርገን ነው የጀመርነው። ከዚህ ቀደም ደግሞ አንድ አድርገን ነው የጀመርነው። ለእኛም አስፈላጊ ስለነበር የጨዋታው መበላለጥ ጎል ካገባን በኋላ ወረድ ለማለት ሞክረናል። የምንፈልገው ነጥብ ስለነበር ፤ እሱንም አሳክተናል።

ስለዑመድ እና ራምኬል የመጀመሪያ ጎል ስላለው አስተያየት

“ምንም አስተያየት የለኝም። አጥቂዎቼ ጎል ሲያገቡ ደስ ይለኛል። ለእኔ ብቻም ሳይሆን ለራሳቸውም ነገ ከነገ ወዲያ ላሉ ጨዋታዎች በራስ መተማመናቸው ጥሩ ይሆናል። ራምኬል ደግሞ ለእኛ እንግዳ ነው ፤ ዛሬ የመጀመሪያ ጎሉ ነው። የእሱ ማግባት ደግሞ በቀሪ ጨዋታዎች ይበልጥ ያግዘናል። ጎሎች ማግባታቸው ደስ ብሎኛል።”

ያጋሩ