አራት ግቦች ተቆጥረው በአቻ ውጤት ከተገባደደው ጨዋታ በኋላ ከአሠልጣኞች የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ተቀብለናል።
ኃይሉ ነጋሽ – ፋሲል ከነማ (ጊዜያዊ አሠልጣኝ)
የጨዋታው እንቅስቃሴ ባሰባችሁት መንገድ ሄዷል?
እንደምንፈልገው አልሄደም። ቀድሞ ጎል ተቆጥሮብን ስለነበር ተጫዋቾቼ ጎል ለማስቆጠር ፈልገው ስለነበር እንቅስቃሴው ይቆራረጥ ነበር።
ስለተሰጠባቸው የፍፁም ቅጣት ምት..?
በፍፁም ቅጣት ምቱ ደስተኛ አይደለሁም። እንዴት እንደሆነ ራሱ አልገባኝም። ምናልባት ምስሉን ካየሁ በኋላ በደንብ ሊገባኝ ይችላል።
ፋሲል አሁንም በዋንጫ ፉክክር ውስጥ አለ?.
አሁንም ፉክክር ውስጥ አለን። እኛ ስለሌላው ክለብ ሳይሆን ከፊት ለፊታችን ያለውን ተጋጣሚ እያሸነፍን ስለመጠጋት ነው የምናስበው።
ቡድኑ ውስጥ ስላለው አንድነት…?
ቡድኑ ውስጥ በጣም ህብረት አለ። የመጫወት ፍላጎትም አለ። ግን ካለማሸነፍ ጋር ተያይዞ በራስ መተማመንን ማጣት አለ እንጂ ይህ መተማመን እየመጣ ሲሄድ የተሻለ ነገር እንሰራለን ብዬ አስባለው።
ደምሰው ፍቃዱ – አዲስ አበባ ከተማ
ጨዋታው እንዴት ነበር?
ጨዋታው ጥሩ ነበር። ባለፈውን ከማሸነፍ ስለመጣን ተጫዋቾቹ የማሸነፍ ስነ-ልቦናቸው ጥሩ ስለነበር ጥሩ ተንቀሳቅሰናል።
በጨዋታው ያደረጋቸው የተጫዋች ቅያሪዎች?
ቅያሪዎቻችን ስኬታማ ናቸው። ተጫዋቾቹ ተቀይረው ከገቡ በኋላ የሰሩት ስራ አለ። ቢኒያም፣ አቤል እና መሐመድ በአጥቂ መስመሩ ጥሩ ተንቀሳቅሰዋል። ከዚህ መነሻነት ቅያሪያችን የተሳካ ነበር።
ስለ ቀሪ ጨዋታዎች..?
በቀሪ ጨዋታዎች የበለጠ ተዘጋጅተን ያለንበትን ደረጃ ለመቀየር ነው ሀሳባችን። የተሻለ ውጤት ለማግኘትም ጠንከር ብለን መዘጋጀት አለብን።